RSS

ፍልስፍና= ፍቅረ-ጥበብ= የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ቅኔ

-በካሣሁን ዓለሙ-
ታላቁ ሊቅ ሶቅራጥስ በአንክሮ መጠበብ (ፍልስፍና) እንደምትጀመር ተናግሯል አሉ፡፡ ግን ምን ስለሆነች ነው ጥበብ የምታስደምመን? ምን ስለሆነች ነው በፍቅር የምታሳብደው? ‹በቅድሚያ ማወቅ መተዋወቅ› ብሏል ዘፋኙ! ስለዚህ እንተዋወቃት፤ እኛም ብንሆን ታዲያ ‹ተይ! ማነሽ! ተይ! ማነሽ!› ብለን ልንጠይቃት፣ ልናውቃት ይገባል!፡፡
‹ወይ ጥብብ! ወይ ጥበብ!… አንቺን ያፈቀረ፣
ተብረክርኮ ቀረ!› አለ አድናቂዋ!
እንደኔ ግንዛቤ ጥበብን እንደተሸበበች በቅሎ በአንድ አቅጣጫ ብቻ መመልከት ሙሉ አይመስለኝም፤ እንደ ኢትዮጵያዊያን የአንድምታ ትርጓሜ በተለያየ አቅጣጫና ደረጃ ገጽታዋ ሊታይና ሊነገር ይገባዋል፡- በቻል አራት ዓይና መኾንን ትፈልጋለች፡፡ ለእኔ በጥቅል የተረዳሁት የመሰለኝ የጥበብ ምንነት ልግለጽ፤ ለእኔ ጥበብ በተዋህዶ የምትሠልስ ናት፤ ማለት የጥበብ ትርጉም ‹የእውነት፣ የዕውቀትና የመልካምነት ተዋህዶ (ቅኔ)› ነው፤ አንድም በኢትዮጵያውኛ እንግለጻት ካልን ‹ጥበብ ማለት ቅኔ ናት› (ግጥም አላልኩም)፤ ካሠራር ብልሃት አንጻር ካየናትም ‹ጥበብ ማለት ፊደል ናት›፤ አንድም በመንፈሳዊ ዕይታ ከተመለከትናት ጥበብ እግዚአብሔርን (ሥላሴ) ወይም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥርነት ፈክራ ታመሠጥራለች›፡፡ እንደ ጠቢቡ ሰለሞን ከሆነ ‹ጥበብ ሰባት አዕማዳት ያሏት ቤት› ነች፡፡ ስለዚህ ጥበብን በተለያየ ዕይታና አተረጓገም መቃኘት ይገባል፤ ግን መሠረታዊ ትርጓሜዋን መልቀቅ የለባትም፤ ያንኑ ማምጠቅ ወይም መወሰን ወይም የትኩረት አቅጣጫዋ መወሰን ወይም የአስተውሎት ልዩነት ነው ልዩነቱን የሚፈጥረው፤ አንድም የትርጓሜው ልዩነት የሚፈጠረው ከምትታይበት የአንግል መለያየት የተነሣ ይሆናል፤ ለማንኛው እነዚህን አንድማታዊ ትርጓሜዎች እንቃኛቸው፡- ቅኔነቷን እየፈታን፤ የላይ ቤትና የታች ቤት ምሥጢራዊ ትርጓሜዋን እየለየን እንያት፡፡ Read the rest of this entry »

Advertisements
 

መኑ ውእቱ ፍልሱፍ- ፈላስፋ ማን ነው?

(በካሣሁን ዓለሙ)

ፍልስፍናን እማራለሁ› ብዬ ት/ቤት ብገባ፣ መምህሩ ‹ፍልስፍና ምንድን ነው?› ብሎ መልሶ እኔኑ ጠየቀኝ፤ ‹ካወቅኩትማ ለምንስ ልማረው ብዬ ሒሳብ ከፈልኩ?› አልኩኝ፤

‹ታዲያ ፍልስፍናን በገንዘብ ልተገዛ ነው የመጣኸው?› ብሎ አፈጠጠብኝ፡፡

‹አይ! በመማር ለማወቅ ነው የመጣሁት› አልኩት፡፡

በዚህ መሃል ግን በክፍል ውስጥ አብረን ከነበርነው ተማሪዎች መካከል አንዱ ቀለብላባ ተማሪ ‹ፈላስፋ የሚባለው ራሱ ማን ነው?› የሚል ጥያቄ አንሥቶ ገላገለኝ፡፡

መምህሩም ‹ፈላስፋ ምን እንደኾነ ንገረኝና የፍልስፍናን ምንነት አስረዳሃለሁ፤ ይባላል› አለን፡፡ ወይ ጣጣ ማብዛት! ‹ከየትኛው ነው የሚጀመር? ፍልስፍናን ከሚያወቀው ሰው ወይስ ከፍልስፍና ምንነት? ማንም ይፈላሰፈው ፍልስፍናን ካወቅነው አይበቃንም? ደግሞስ ‹የፈላስፋን ምንነት ንገረኝ› ማለት ማንነቱን ከማወቅ ያነሰ፣ አሳቢውን ሰው ወደ ቁስነት የቀየረ አነጋገር አይኾንም?› የሚል ሐሳብ መጣብኝ፡፡ አላስችል ስላለኝም ‹የፈላስፋው ማንነት እንደ ቁስ ተቆጥሮ ለምን በምንነት ይገለጻል?› አልኩት!

እሱም ጥያቄውን ወደ እኔ በማዞር ‹ሐሳቢ ሰው ምንነት የለውም ልትል ነው?› ብሎ አፋጠጠኝ፡፡

‹አይ! በቁስነቱ እየተከራከርን ጊዜ ከምናባክን በማንነቱ ተወያይተን የፍልስፍናን ምንነት ብንረዳ ይሻላል ብዬ ነው› አልኩት፡- ነገር ለማብረድ፡፡

አስተማሪው ግን በማስጠንቀቅ መልክ የዘመኑን አባባል ተጠቅሞ ‹ሲጀምር ጊዜ ከሌለህ ፍልስፍና ጋር አትድረስ፤ ሲቀጥል በፍልስፍና ትምህርት የማትስማማበትም ነገር ቢኾን ይነሳል፤ ሲቀጣጠል የፈላስፋውን ምንነት ሳታወቅ እንዴት ከማንነቱ ላይ ደረስክ? ምንነት የለውም ልትል ነው ወይስ በምንነቱ ላይ ጥያቄ አይነሳም፤ ታውቆ አልቋል ለማለት ፈልገህ ነው? ሲጧጧፍ በምንነትና በማንነት መካከል ያለው ልዩነት ገብቶሃል? ከገባህ አስረዳን፤ ካልገባህ ለማወቅ ጠይቅ እንጂ ሳታውቅ ለጥያቄው ያልተመለሰ መደምደሚያ አትስጥ!› እያለ ወረደብኝ፡፡ Read the rest of this entry »

 

ምሲዮኖችና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ምንና ምን ነበሩ? ከአለቃ አያሌው ታምሩ ታሪክ የተቀነጨበ

‹‹የላይኛውን ዓይኔን ወስዶ የውስጡን አበራልኝ› የሚሉት አለቃ አያሌው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያ በሊቅነታቸው ከሚታወቁት ሊቃውንት አንዱና ግንባር ቀደሙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የእኝህን ታላቅ ሊቅ የሕይወት ታሪክ ልጃቸው ሥምረት አያለው አዘጋጅታ አሳትመዋለች፡፡ ከዚህ መጽሐፍ ውስጥም በዘመናዊ የከፍተኛ ትምህርት አጀማማር ውስጥ የምስዮኖች ተጽዕኖ ምን ይመስል እንደነበር ያሳያል ያልኩትን ቀንጭቤ እዚህ አቅርቤዋለሁ፡፡IMG_20150819_143156
‹‹አባቴ በግርማዊነታቸው ፊት ከተቀኘ በኋላ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የነሣውን የዘመኑን ወጣት ኢትዮጵያውያ ሁኔታ አስመልክቶ የሚከተለውን አቤቱታ ለጃንሆይ አሰማ፡፡
‹… ጃንሆይ! ሃይማኖት እየጠፋ ነው፡፡ ጀስዊቶች በገቡበት አገር ሁሉ ያልተገለበጠ መንግሥት፣ ያልተናወጠ አገር… ያልተለወጠ ሥርዓት ያለመኖሩን ከእኔ የበለጠ ጃንሆይ ያውቃሉ፡፡ ሁሉ እየተነሣ ኃይለ ሥላሴ ይሙት… ኃይለ ሥላሴ ይሙት እያለ የአባቱ ማሳረፊያ ቢያደርግዎ ምንም የሚጠቅም ነገር የለውም፡፡ ወጣቱን ትውልድ አዳሪ ትምህር ቤት ሰብስበው እያስተማሩ ነው፡፡ አስተማሪዎች ደግሞ የሌላ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ የራሳቸውን ታሪክ፣ እምነትና ባህል ከሚነግሩት በቀር የራሱን ታሪክ የሚያስተምረው የለም፡፡ እነዚህ ነገ ሲወጡ ጉድጓድ ውስጥ ያደገ የውሻ ግልገል መሆናቸው ነው፡፡ አንዳች ክፉ ነገር ቢመጣ እንኳን ደሙን የሚያፈስልዎ ውሃ የሚረጭልዎ አያገኙም…፡፡› በማለት ስለ ጊዜው ሁኔታ የነበረውን ሥጋትና ወደፊት ሊመጣ ይችላል ብሎ ልቡ የሰጋበትን ተናገሯል፡፡
ይህንን ንግግር ያደረገው ሥራዬ ብሎ በዓላማ ደረጃ ከያዛቸው የማስተማሪያ መንገዶች አንዱ ባለሥልጣናትን በጊዜው ስለነበረው ሁኔታ መምከርና ማንቃት ተገቢ ነው ብሎ ያምን ስለነበረ ነው፡፡ ይህን ሰያደርግ ደግሞ ከእነሱም ሆነ ከሌላው ‹የእኔ ዕውቀት ይበልጣል› በማለት ሳይሆን ከእግዚአብሔር በተሰጠው መንፈሳዊ ጸጋ የተነሣ ሌላው ሰው ከርቀት የማያየውን ነገር እርሱ በዓይነ ትንቢት የመገንዘብ ስጦታ ስለነበረው ጭምር ነው፡፡ በዚህ ዕለት አባቴ ያደረገው ንግግር ብዙዎች ከድፍረት ቢቆጥሩትም ንጉሠ ነገሥቱ ግን ችላ ብለው አላለፉትም፡፡ ይልቁንም ምን እንዲያደርጉለት እንደሚፈልግ ጠየቁት፡፡
እሱም ‹የዓለምን መጻሕፍት ለመመርመር የምችልበት፣ ዕውቀት የማገኝበት፣ እኔም በዐቅሜ ከአገሬ ዕውቀት የተማርኩትን ትምህርት ለዘመኑ ወጣቶች የማካፍልበት የመማርና የማስተማር ዕድል እንዲሰጠኝ ነው፡፡…› በማለት መለሰላቸው፡፡
ጃንሆይ ተጨማሪ ጥያቄዎች ነበሯቸው፡፡
‹ከየት ነው የመጣኸው?› ሲሉ ጠየቁት፡፡
‹ከጎጃም ክፍለ ሀገር ከሚገኘው ከታላቁ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡› በማለት መለሰ፡፡
‹የዓይንህን ብርሃን ባታጣ ኖሮ ምን ለመሆን ትመኝ ነበር?› ሲሉት፤
‹ምኞቴ ምናልባት ወታደር መሆን ነበረ፡፡› ሲል መለሰላቸው፡፡
‹እንኳን ዓይንህ ጠፋ፡፡› አሉ ጃንሆይ፡፡ Read the rest of this entry »

 

በደርግ አብዮታዊ አገዛዝ ዙሪያ የተደረጉ የደራሲያን ሥላቆችን ምንያህል ያውቃሉ?

ለአብነት ያህል የአለቃ እንባቆም፣ የአቤ ጉበኛ፣ የጳውሎስ ኞኞን እና የመንግሥቱ ለማን ሥላቆች እናስታውስ እስቲ፡፡ ሥላቃቸውን በተራ ንግግር ሳይሆን በግጥም ያቀረቡት አለቃ እንባቆም ናቸው፡፡ ግጥማቸው እንዲህ ይላል፡
‹ንገረው ለተጉለት ንገረው ለቡልጋ፣
አገሬን ወረራት የዝንጀሮ መንጋ፤
ይሠረዝ ይደለዝ መጽሐፈ-ኦሪቱ፣
ይደለዝ ይሠረዝ መጽሐፈ-ኦሪቱ፣
ሰው ከተፈጠረ ገና ሦስት ዓመቱ፡፡›
ይህ ሥላቃዊ ግጥም የተገጠመው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ወርደው አንድ መቶ ሃያ የደርግ አባላት ሥልጣን ያዙ በተባለበት ጊዜ ነበር፡፡ ገጣሚውም ግጥማቸውን በሬድዮ ካነበቡ በኋላ ሌላ ትርጉም እንዳይሠጥባቸው ‹አገሬን ወረራት ያልኩት የዝያድ ባሬን ወታደር ነው› ብለዋል፡፡ እውነታው ግን በአገራችን እንደተለመደው ባንድ ሰው መመራት ቀርቶ በአንድ መቶ ሃያ የደርግ አባላት መመራቷ ገርሟቸው የተቀኙት ቅኔ ነው ይባላል፡፡ የሁለተኛው ስንኝም ጉዳይ እንደዚሁ ነው፤ ሦስተኛውም የአብዮት በዓል ሲከበር አብዮቱን አሞገሰው ሰው በእግዚአብሔር ሳይሆን ኤንግልስ እንዳለው በሥራ የተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው እንዲናገሩ ስለታዘዙ ‹የአገራችን ሰው የተፈጠረው ከአብዮቱ በኋላ ብቻ ነው› በሚል አንድምታ ሰው በኦሪት ጊዜ ተፈጠረ የሚለውን እንደ ስህተት የቆጠሩት መስለዋል፡፡ ይህም ለሚገባው ሶሻሊዝምን ያመሰገኑ መስለው ኦሪትን ማወደሳቸው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ግጥሙም በባሕርዩ ንጽጽራዊ ሥላቅ ይባላል፡፡
ደራሲው አቤ ጉበኛ በመጨረሻ ዘመኑ ላይ ባሕር ዳር የድርና ማግ ንግድ ፈቃድ አውጥቶ ለጎጃም ነጋደዎች ያከፋፍል ነበር አሉ፡፡ አንድ ቀን ግን ድርና ማጉን ለጎንደር ነጋደዎችም ስለሸጠላቸው፤ ጎጃሜዎች ኮታችንን ለሌላ ሰጠብን በሚል ከሰሱት አሉ፡፡
እናም ደኛው ‹አቶ አቤ ይህንን ለምን አደረግህ?› ሲለው፤
‹ጌታየ የጎንደር ነጋደዎች ኢትዮጵያውያን መስለውኝ ነበር፤ ወደፊት አልሸጥላቸውም› አለ ይባላል፡፡
አቤ አሁንም እዚያው ባሕር ዳር እንዳለ ካድሬዎች እየተመለመሉ የካቲት አሥራ ሁለት ት/ቤት ይገባሉ፤ በሦስት ወራት ውስጥ ማርክሲዝም ሌኒንዝምን እየተማሩ ይመረቁና ባሕር ዳር ይመለሱ ነበር አሉ፡፡ እናም ‹ማርክስና ኤንግልስ ደደቦች ስለሆኑ ፍልስፍና ሲያጠኑ ሠላሳና ዐርባ ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡ የእኛ አገር ካድሬ ግን በሦስት ወር ውስጥ እየላጠው መጣ› ብሎ እንደተሣለቀ ይነገራል፡፡
አንድ ወቅት ላይ ጳውሎስ ኞኞ ‹ሠርቶ አደር ጋዜጣን ትወደዋለህ ወይ?› ተብሎ ተጠይቆ ነበር አሉ፤ ጋዜጣው ደግሞ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የበላይ ጠባቂነት የሚዘጋጅ ነው፤ ታዲያ ጳውሎስም ምሳሌ በመጠቀም ተሣልቆባቸዋል፤ እንዲህ አለ ‹አንድ ገዚ አንዱ ‹ማርያም ትወዳታለህ?› ተብሎ ሲጠየቅ ለምንድ አልወዳት ከግን የሚያላትም ልጅ እያላት አለ፤ እኔም ሠርቶ አደር ጋዜጣን አልወደውም ብል ከግንድ ጋር ስለሚያጋጨኝ እወደዋለሁ› ብሏል፡፡
ንግግራቸው ሁሉ በቀልድ የሚታጀበው መንግሥቱ ለማም ባህል ሚኒስቴር ውስጥ እያሉ አንድ የባህል መምሪያ ኃላፊ ‹ጓድ መንግሥቱ አርንጓደው ዘመቻ ተጀምሯል፤ በዚህ ዙሪያ ድርሰት ይጻፉ› ይላቸዋል፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ ስብሰባ ሲሄድ ጠርቶ ‹ድርሰቱ ከምን ደረሰ?› ይላቸዋል፡፡
መንግሥቱም ታዲያ ‹ወንድም ትቀልዳለህ ወይስ የምርህን ነው?› ይሉታል፡፡
ኃላፊውም ‹በአብዮትማ ቀልድ የለም› በማለት ትካሻውን ይነቀንቅባቸዋል፡፡
መንግሥቱም ‹አንተ ደደብ ደነዝ ነህ እኔ ድርሰት እንደ ልብስ ስፌት አድርስ ተብዬ ስለ አረንጓደው ዘመቻ አልጽፍም፡፡ ይህንን ከፈለግህ አራት ኪሎ ሄደህ ለአለቆችህ ንገራቸው፤ ስትነግራቸውም ከግንድ ጋር አስደግፈው በሣንጃ ይወጉኛል፤ ያን ጊዜ ስለ አረንጓደው ዘመቻ ሳይሆን ሳንጃው በመቀመጫዬ ስለመግባቱ ድርሰት እጽፋለሁ፤ ምክንያም ያመኛላ!› ብለውታል ይባላል፡፡
(ምንጭ፡- ታደለ ገድሌ፣ ቅኔና ቅኔያዊ ጨዋታ ለትዝታ)

 
 

መቀነትሽን አጥብቂ

IMG0193A

(የኮተቤው የሻው ተሰማ)
የዕድሜሽን ተውሳክ-ተቀጥላ፣ በመሐፀንሽ ስትቋጥሪ፣
ያበሳሽን ቀነ ገደብ፣ ስትቀንሽ- ሰትደምሪ፣
በትኩስ-በበራዱ፣ ቃር ማቅለሽለሽ… ስትጀምሪ፣
ዶሮ መረቁ ቢያርብሽ፣ ወጡ በቅመም ባይጥም፣
‹ቅሪት ያምራታል› ተብሎልሽ፣ ለደንታሽ ደንታ ባይሰጥም፣
ፍሪዳ ባይጣልልሽ፣ ዕድል ባይጥፍሽ ለቅልጥም፤
አቅበጥብጦ ሲያስፋሽክሽ…፣ ሲያስመልስሽ የበላሽው፣
ቃሪያ ጎመኑ… ውል ሲልሽ ያኔ ነበር የጀመርሽው፡፡
ከባጥ በላይ ፅኑ ፍዳ፣ በልጅ ስቃይሽን መቁጠር፣
በኪነ ጥበቡ ትንግርት፣ ቅጥያሽ ሆኜ ስፈጠር፡፡
በመዓልት-ሌሊት ተራክቦ፣ ሲኳኳል የአዋርኅ ቀመር፣
ቀናትን ሣንምት ውጧቸው፣ ሣምታትን ዘጠኝ ወር፣
በወርኀ ማዕዶት ሽግሽግ፣ ለዓመት ሦሰት ወር ሲቀር፣
እንደ ልሳኑ ስያሜ፣ ‹ቅሪት› ነበርሽ ቀደም ሲል፣
ነፍስ ስዘራ ስጠራቀም፣ ከ‹ፅንሰነት› ተብዬ ‹ሽል›፣
ከደምሽ ደም እየሞላሁ፣ እድገቴን ባንቺው ሳሻሽል፣
በዚያ የሸክም ወራት፣ ሲያበራይሽ የልብ ጋር፣
ነፍስሽ ሕቅታን ስትቃዥ፣ ተሠርታ በሞት አውታር፣
ላይ ቅጽበት እፎይታ አጥተሸ፣ ሲያባዝትሽ ሰቀቀኑ፣
በብጽዓት እየማለድሽ፣ በምልጃ በጧፍ- በጣኑ፣
ነገ የሰማይ ያህል- እየመጠቀ ቀኑ፣
ቁም ስቅልሽን እያሳየሁ፣ ‹ነፍሰጡር› ሆነሽ ተጦሬ፣
ባፍንጫሽ እያስቃተትሁ፣ ልክ ዘጠኝ ወር ቆጥሬ፣
በመጣሁ-ቀረሁ ሕማማት፣ የቀናት ለጠፍ ደምሬ፣
የአራስ ቤት ወግ ላሳይሽ፣ ስበቃ ለምስልሽ ፍሬ፤
ደሜን ከደምሽ በመድፈቅ፣ አጥንቴን ካጥንትሽ አጋጥሜ፣
‹የምጥ ማርያምን› ሲማልድ፣ ምጥሽን ሲያምጥ አዳሜ፣
አስደግድጌው እንደ ጃን፣ ወንድ ሴቱን አስቁሜ፣
ኮኮቤ ሲቃናልኝ- ፍካሬው ሲያምር ሕልሜ፣
በሽርት ውሃ ብሥራት-መርዶ፣ ተሸጋገርኩ ለሌላ ዕድሜ፡፡ Read the rest of this entry »

 
 

ጥንታዊቷ የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርሲቲያን

የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በደቡብ ወሎ ዞን ወረኢሉ ወረዳ የምትገኝ ናት፡፡ ከአዲስ አባባ 476 ኪ.ሜ. እንዲሁም ከደሴ ከተማ 76 ኪ.ሜ. ወረኢሉ ለመድረስ 15 ኪ.ሜ. ሲቀረው ሰኞ ገበያ ተብላ ከምትጠራ አንዲት ትንሽ ከተማ በስተምዕራብ በኩል አራት ኪ.ሜ. ርቀት ትገኛለች፡፡ በጂ.ፒ.ኤስ. መለኪያም በ10°44’57” የኬክሮስ መስመርና በ39°24’97” ምሥራቅ የኬንትሮስ መስመር ላይ ዐርፋለች፡፡

  1. የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ከታሪክ ጸሐፊዎች እይታ አኳያ

የታሪክ መዛግብቱም ሆኑ አፈታሪኮች እንደ ሚስማሙበት ከሆነ የጥንታዊቷ የመካነ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያ የተመሠረተችው በ1513 ዓ.ም ነበር፡፡ የቤተ ክርስቲያኗ የሕንፃ መሠረት የተጣለው በዓፄ ናዖድ ዘመነ መንግሥት /1489-1500 ዓ.ም/ ሲሆን አስገንብተው ያስጨረሱት ልጃቸው ዐፄ ልብነ ድንግል /1500-1533/ ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያኗ የምርቃ በዓል ላይ በ1513 ዓ.ም በሥፍራው በመገኘት ስለ ቤተ ክርስቲያኗ ያየውንና የሰማውን በመጻፍ ለትውልድ እንዲተላለፍ በማድረግ ግንባር ቀደሙ ፖርቱጋላዊው ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ነው፡፡ አልቫሬዝ ስለ ጥንታዊው ቤተ ክርስቲያ ሥነ ሕንፃዊ ጥበብ ያሰፈረው ሐተታ ከታሪካዊ መረጃነቱ በተጨማሪ ለአርኮዎሎጂና አርክቴክቸር ጥናትና ምርምር ጥሩ መነሻ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ አልቫሬዝ ስለ ቤተ ክርስቲያኗ ሥነ ሕንፃዊ አወቃቀር እንዲህ ሲል ጽፏል፡- ‹‹ግድግዳዎቹ በጥርብ ድንጋይ ተሠርተው በሐረግ አጊጠዋል… የዋናው በር መዝጊያ በወርቅና በብር ተለብዷል፡፡ በወርቁ ልባድ ውስጥ አንዳንድ የከበሩ ድንጋዮች… አሉ፡፡ ጣሪያዎቹ በስድስት ምሰሶዎች ላይ ዐርፈዋል፡፡ የውጭ ታዛውን 13 ረጃጅም ምሰሶዎች ደግፈውታል፡፡ … በሠገነቱ ዙሪያ እያንዳንዳቸው ከ16 ቅጽ ወርቀ ዘቦ ጨርቅ የተሠሩ 16 ተከፋች መጋረጃዎች አሉት፡፡ …›› Read the rest of this entry »

 

መኪናው ሥልጣን

(በካሣሁን ዓለሙ)
ሥልጣን መኪና ነው- የሕዝብ መገልገያ፣
አንዱ ትቶ ሲወርድ- ለአንዱ መሣፈሪያ፤
መሪውም ሹፌር ነው- መኪና እሚነዳ፣
መጠንቀቅ ያለበት- ሕዝብ እንዳይጎዳ፡፡
ተሣፋሪዎቹም- የመኪና ወንበር፣
በሥልጣን ማገልገል በሌላ እስኪቀየር፤
በመጠንከር ይሥሩ- ትተው መሰባበር፡፡ Read the rest of this entry »

 
Leave a comment

Posted by on January 22, 2015 in የግጥም ገበታ

 
 
%d bloggers like this: