RSS

Category Archives: ዐጫጭር መጣጥፎች

ይህ ክፍል ገጠመኞችና ትዝብቶች በወግ መልክ ተዋዝተው የሚጦመሩበት፤ እንዲሁም ዐጫጭር ልብወለዶች የሚቀርቡበት ነው፡፡

ምሲዮኖችና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርስቲ ምንና ምን ነበሩ? ከአለቃ አያሌው ታምሩ ታሪክ የተቀነጨበ

‹‹የላይኛውን ዓይኔን ወስዶ የውስጡን አበራልኝ› የሚሉት አለቃ አያሌው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያ በሊቅነታቸው ከሚታወቁት ሊቃውንት አንዱና ግንባር ቀደሙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የእኝህን ታላቅ ሊቅ የሕይወት ታሪክ ልጃቸው ሥምረት አያለው አዘጋጅታ አሳትመዋለች፡፡ ከዚህ መጽሐፍ ውስጥም በዘመናዊ የከፍተኛ ትምህርት አጀማማር ውስጥ የምስዮኖች ተጽዕኖ ምን ይመስል እንደነበር ያሳያል ያልኩትን ቀንጭቤ እዚህ አቅርቤዋለሁ፡፡IMG_20150819_143156
‹‹አባቴ በግርማዊነታቸው ፊት ከተቀኘ በኋላ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የነሣውን የዘመኑን ወጣት ኢትዮጵያውያ ሁኔታ አስመልክቶ የሚከተለውን አቤቱታ ለጃንሆይ አሰማ፡፡
‹… ጃንሆይ! ሃይማኖት እየጠፋ ነው፡፡ ጀስዊቶች በገቡበት አገር ሁሉ ያልተገለበጠ መንግሥት፣ ያልተናወጠ አገር… ያልተለወጠ ሥርዓት ያለመኖሩን ከእኔ የበለጠ ጃንሆይ ያውቃሉ፡፡ ሁሉ እየተነሣ ኃይለ ሥላሴ ይሙት… ኃይለ ሥላሴ ይሙት እያለ የአባቱ ማሳረፊያ ቢያደርግዎ ምንም የሚጠቅም ነገር የለውም፡፡ ወጣቱን ትውልድ አዳሪ ትምህር ቤት ሰብስበው እያስተማሩ ነው፡፡ አስተማሪዎች ደግሞ የሌላ አገር ዜጎች ናቸው፡፡ የራሳቸውን ታሪክ፣ እምነትና ባህል ከሚነግሩት በቀር የራሱን ታሪክ የሚያስተምረው የለም፡፡ እነዚህ ነገ ሲወጡ ጉድጓድ ውስጥ ያደገ የውሻ ግልገል መሆናቸው ነው፡፡ አንዳች ክፉ ነገር ቢመጣ እንኳን ደሙን የሚያፈስልዎ ውሃ የሚረጭልዎ አያገኙም…፡፡› በማለት ስለ ጊዜው ሁኔታ የነበረውን ሥጋትና ወደፊት ሊመጣ ይችላል ብሎ ልቡ የሰጋበትን ተናገሯል፡፡
ይህንን ንግግር ያደረገው ሥራዬ ብሎ በዓላማ ደረጃ ከያዛቸው የማስተማሪያ መንገዶች አንዱ ባለሥልጣናትን በጊዜው ስለነበረው ሁኔታ መምከርና ማንቃት ተገቢ ነው ብሎ ያምን ስለነበረ ነው፡፡ ይህን ሰያደርግ ደግሞ ከእነሱም ሆነ ከሌላው ‹የእኔ ዕውቀት ይበልጣል› በማለት ሳይሆን ከእግዚአብሔር በተሰጠው መንፈሳዊ ጸጋ የተነሣ ሌላው ሰው ከርቀት የማያየውን ነገር እርሱ በዓይነ ትንቢት የመገንዘብ ስጦታ ስለነበረው ጭምር ነው፡፡ በዚህ ዕለት አባቴ ያደረገው ንግግር ብዙዎች ከድፍረት ቢቆጥሩትም ንጉሠ ነገሥቱ ግን ችላ ብለው አላለፉትም፡፡ ይልቁንም ምን እንዲያደርጉለት እንደሚፈልግ ጠየቁት፡፡
እሱም ‹የዓለምን መጻሕፍት ለመመርመር የምችልበት፣ ዕውቀት የማገኝበት፣ እኔም በዐቅሜ ከአገሬ ዕውቀት የተማርኩትን ትምህርት ለዘመኑ ወጣቶች የማካፍልበት የመማርና የማስተማር ዕድል እንዲሰጠኝ ነው፡፡…› በማለት መለሰላቸው፡፡
ጃንሆይ ተጨማሪ ጥያቄዎች ነበሯቸው፡፡
‹ከየት ነው የመጣኸው?› ሲሉ ጠየቁት፡፡
‹ከጎጃም ክፍለ ሀገር ከሚገኘው ከታላቁ ዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡› በማለት መለሰ፡፡
‹የዓይንህን ብርሃን ባታጣ ኖሮ ምን ለመሆን ትመኝ ነበር?› ሲሉት፤
‹ምኞቴ ምናልባት ወታደር መሆን ነበረ፡፡› ሲል መለሰላቸው፡፡
‹እንኳን ዓይንህ ጠፋ፡፡› አሉ ጃንሆይ፡፡ Read the rest of this entry »

Advertisements
 

በደርግ አብዮታዊ አገዛዝ ዙሪያ የተደረጉ የደራሲያን ሥላቆችን ምንያህል ያውቃሉ?

ለአብነት ያህል የአለቃ እንባቆም፣ የአቤ ጉበኛ፣ የጳውሎስ ኞኞን እና የመንግሥቱ ለማን ሥላቆች እናስታውስ እስቲ፡፡ ሥላቃቸውን በተራ ንግግር ሳይሆን በግጥም ያቀረቡት አለቃ እንባቆም ናቸው፡፡ ግጥማቸው እንዲህ ይላል፡
‹ንገረው ለተጉለት ንገረው ለቡልጋ፣
አገሬን ወረራት የዝንጀሮ መንጋ፤
ይሠረዝ ይደለዝ መጽሐፈ-ኦሪቱ፣
ይደለዝ ይሠረዝ መጽሐፈ-ኦሪቱ፣
ሰው ከተፈጠረ ገና ሦስት ዓመቱ፡፡›
ይህ ሥላቃዊ ግጥም የተገጠመው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ወርደው አንድ መቶ ሃያ የደርግ አባላት ሥልጣን ያዙ በተባለበት ጊዜ ነበር፡፡ ገጣሚውም ግጥማቸውን በሬድዮ ካነበቡ በኋላ ሌላ ትርጉም እንዳይሠጥባቸው ‹አገሬን ወረራት ያልኩት የዝያድ ባሬን ወታደር ነው› ብለዋል፡፡ እውነታው ግን በአገራችን እንደተለመደው ባንድ ሰው መመራት ቀርቶ በአንድ መቶ ሃያ የደርግ አባላት መመራቷ ገርሟቸው የተቀኙት ቅኔ ነው ይባላል፡፡ የሁለተኛው ስንኝም ጉዳይ እንደዚሁ ነው፤ ሦስተኛውም የአብዮት በዓል ሲከበር አብዮቱን አሞገሰው ሰው በእግዚአብሔር ሳይሆን ኤንግልስ እንዳለው በሥራ የተፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው እንዲናገሩ ስለታዘዙ ‹የአገራችን ሰው የተፈጠረው ከአብዮቱ በኋላ ብቻ ነው› በሚል አንድምታ ሰው በኦሪት ጊዜ ተፈጠረ የሚለውን እንደ ስህተት የቆጠሩት መስለዋል፡፡ ይህም ለሚገባው ሶሻሊዝምን ያመሰገኑ መስለው ኦሪትን ማወደሳቸው መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ግጥሙም በባሕርዩ ንጽጽራዊ ሥላቅ ይባላል፡፡
ደራሲው አቤ ጉበኛ በመጨረሻ ዘመኑ ላይ ባሕር ዳር የድርና ማግ ንግድ ፈቃድ አውጥቶ ለጎጃም ነጋደዎች ያከፋፍል ነበር አሉ፡፡ አንድ ቀን ግን ድርና ማጉን ለጎንደር ነጋደዎችም ስለሸጠላቸው፤ ጎጃሜዎች ኮታችንን ለሌላ ሰጠብን በሚል ከሰሱት አሉ፡፡
እናም ደኛው ‹አቶ አቤ ይህንን ለምን አደረግህ?› ሲለው፤
‹ጌታየ የጎንደር ነጋደዎች ኢትዮጵያውያን መስለውኝ ነበር፤ ወደፊት አልሸጥላቸውም› አለ ይባላል፡፡
አቤ አሁንም እዚያው ባሕር ዳር እንዳለ ካድሬዎች እየተመለመሉ የካቲት አሥራ ሁለት ት/ቤት ይገባሉ፤ በሦስት ወራት ውስጥ ማርክሲዝም ሌኒንዝምን እየተማሩ ይመረቁና ባሕር ዳር ይመለሱ ነበር አሉ፡፡ እናም ‹ማርክስና ኤንግልስ ደደቦች ስለሆኑ ፍልስፍና ሲያጠኑ ሠላሳና ዐርባ ዓመት ፈጅቶባቸዋል፡፡ የእኛ አገር ካድሬ ግን በሦስት ወር ውስጥ እየላጠው መጣ› ብሎ እንደተሣለቀ ይነገራል፡፡
አንድ ወቅት ላይ ጳውሎስ ኞኞ ‹ሠርቶ አደር ጋዜጣን ትወደዋለህ ወይ?› ተብሎ ተጠይቆ ነበር አሉ፤ ጋዜጣው ደግሞ በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም የበላይ ጠባቂነት የሚዘጋጅ ነው፤ ታዲያ ጳውሎስም ምሳሌ በመጠቀም ተሣልቆባቸዋል፤ እንዲህ አለ ‹አንድ ገዚ አንዱ ‹ማርያም ትወዳታለህ?› ተብሎ ሲጠየቅ ለምንድ አልወዳት ከግን የሚያላትም ልጅ እያላት አለ፤ እኔም ሠርቶ አደር ጋዜጣን አልወደውም ብል ከግንድ ጋር ስለሚያጋጨኝ እወደዋለሁ› ብሏል፡፡
ንግግራቸው ሁሉ በቀልድ የሚታጀበው መንግሥቱ ለማም ባህል ሚኒስቴር ውስጥ እያሉ አንድ የባህል መምሪያ ኃላፊ ‹ጓድ መንግሥቱ አርንጓደው ዘመቻ ተጀምሯል፤ በዚህ ዙሪያ ድርሰት ይጻፉ› ይላቸዋል፡፡ በሌላ ቀን ደግሞ ስብሰባ ሲሄድ ጠርቶ ‹ድርሰቱ ከምን ደረሰ?› ይላቸዋል፡፡
መንግሥቱም ታዲያ ‹ወንድም ትቀልዳለህ ወይስ የምርህን ነው?› ይሉታል፡፡
ኃላፊውም ‹በአብዮትማ ቀልድ የለም› በማለት ትካሻውን ይነቀንቅባቸዋል፡፡
መንግሥቱም ‹አንተ ደደብ ደነዝ ነህ እኔ ድርሰት እንደ ልብስ ስፌት አድርስ ተብዬ ስለ አረንጓደው ዘመቻ አልጽፍም፡፡ ይህንን ከፈለግህ አራት ኪሎ ሄደህ ለአለቆችህ ንገራቸው፤ ስትነግራቸውም ከግንድ ጋር አስደግፈው በሣንጃ ይወጉኛል፤ ያን ጊዜ ስለ አረንጓደው ዘመቻ ሳይሆን ሳንጃው በመቀመጫዬ ስለመግባቱ ድርሰት እጽፋለሁ፤ ምክንያም ያመኛላ!› ብለውታል ይባላል፡፡
(ምንጭ፡- ታደለ ገድሌ፣ ቅኔና ቅኔያዊ ጨዋታ ለትዝታ)

 
 

ካምስተኛው ጉባዔ- ያባቶች ጨዋታ፡- ያለቃ የማነ ብርሃን ቅኔያዊ የጨዋታ ተረብ/ትችት

 

አበው የአገራችን ሊቃውንት በንግግር ለዛቸው የተካኑ፣ በጨዋታቸውም ተራው ሰው ሳያውቅ የሚተርቡና የሚተራረቡ፣ አባባላቸው በአእምሮ ላይ የሚጻፍ እንጂ የማይዘነጋ ነበሩ፤ ናቸውም፡፡ በተለይ የሚያዩትንና የሚታዘቡትን ነገር ሁሉ በጨዋታና በቀልድ እያዋዙ የሚገልጹበት ስልት ልዩ ነው፡፡ ይህንንም አለቃ ገብረ ሐና ‹አምስተኛው ጉባኤ› ብለው እንደሰየሙት መጋቤ አእላፍ መክብብ አጥናው (‹አምስትኛው ጉባኤ› የሚል ርእስ በሰጡት በመጀመሪያው መጽሐፋቸው) አብራርተው ገልጸውታል፡፡ ለማሳያም የሚሆኑ አለቃ ገበረ ሐናን የመሰሉ ሊቃውንት ሞልተዋል፤ ከነዚህም መካከል አለቃ የማነ ብርሃን አንዱ ናቸው፡፡

‹‹አለቃ የማነ ብርሃን በጎንደር ፊት በር ሚካኤል፣ በተለይ ፋኖ ተብሎ በሚጠራው አቋቋም ምስክር የነበሩ ናቸው፡፡ ታላቅ ሊቅና ንግግር አዋቂ ሲሆኑ በሰውነታቸው ቅርፅ ግን ብዙ ጉዳ የደረሰባቸው ነበሩ፡፡ እግራቸው የተቆለመመች አንካሳ፣ ጀርባቸው ላይ ደግሞ ጉብር ያለባቸው ሆነው፣ መዘዋወር የሚችሉት በበቅሎ ሲሆን ሰውም በመጫን ተሸክሞ ነበር ኮርቻ ላይ የሚያወጠቸውና የሚያወርዳቸው፡፡ እኝህ ሊቅ ከተተራረቧቸው ትንሽ የቅኔ ትችቶች የተወሰኑትን እንመልከት! Read the rest of this entry »

 

‹የዓለም የሥልጣኔ ምንጭ ኢትዮጵያ ናት›፤ ማንስ ነው አይደለችም የሚል?

የዓለም የሥልጣኔ ምንጭ ኢትዮጵያ ናት! please read this updated aricle in PDF

እንዳውም ‹ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ› ብላችሁ ካልተሳለቃችሁብኝ የዓለም ሥልጣኔ ምንጩ ኢትዮጵያ ናት የሚል አስተሳሰብ ከሰረፀብኝ ውሎ አድሯል፡፡ ምን ላድርግ የግብፅን የጥንት ሥልጣኔ ያጠኑ የግብፅ ጥናት ሊቆች(Egyptologists)  ‹የጥንቱ የዓለም ሥልጣኔ ከግብፅ ተነሥቶ እንደተስፋፋ ሞገቱኝ!› ተስማማሁ፡፡ ስስማማላቸው ነው መሰል ‹ግብፅ የተመሠረተችው እኮ በጥንት ኢትዮጵያውያን ነው› ብለው ማስረጃ አቀረቡ፡፡ አረ ተው ብላቸው ‹የጥንቱን ከአሁኑ ጋር እያነጻጸሩ እመን አሉኝ› እስቲ ቆይ ላስብበት ብዬ የሀገር ውስጡን ትውፊቱን፣ ተረቱንና ባህሉንና መልካችንን ‹የጥንት ግብፅ ሥልጣኔ ነው› ከተባለው ጋር ሳነጻጽር ቁርጥ የራሳችን ሆኖ አገኘሁት፡፡ ከዚያም ባሰብከው መሠረት ‹ውሳኔህ ከምን?› አሉኝ ‹አመንኩ ተጠመቅኩ› አልኳቸው፡፡ እናንተ ጥርጣሬ ይዟችሁ ‹የውሳኔ እጅህ ከምን? አስረዳ!› ብላችሁ ከላዬ ላይ አልወርድ ካለችሁ ‹ግራ ቀኙን ተመልክቼ የውሳኔዬን ማብራሪያ ላቀርብ ነው›! Read the rest of this entry »

 

ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ሀገር ናት?

1. የቀዳማዊ የሰው ልጅ (የአዳም) መገኛ

2. የጥንታዊ ታሪክ ባለቤት (ከዞንዶ ንጉሥ እስከ ነብር ሪፐብሊክ)

3. የጥንታዊ ሥልጣኔ ምንጭ (..የሱባ፣ የኬሜት፣የአዱሊስ፣የሮሃ፣ የአክሱም፣….)

4. የጥንታዊ ሃይማኖት መገኛ (ሐገ-ልቦና፣ ኦሪት፣… )

5. በዓለም ለዘመናት ያልተቋረጠ በትረ-መንግሥት የነበራት (ከኖህ እስከ ቀ/ኃይለ ሥላሴ ንግሥና)

6. ባንድረዋ በቀስተ-ደመና መልክ በሰማያት የተገኘ– ንግርት

7. እነ ሆሜር ‹የቆንጃጅት ሀገር› ብለው በጥንት ታሪክ ያወደሷትና መሰከሩላት

8. 18 ፈርኦኖችን ለምድረ ግብፅ ያበረከተች ሀገር

9. በዓባይ ሥልጣኔ ምንጭነት ምድረ-ግብፅ ድረስ ወርዳ ታሪካዊዎቹን ፒራምዶች እነ ሶፊንክስን በታሪክ ዓምድነት የተከለች ሀገር

10. በታሪክ መጀመሪያ የተመዘገበች ንግሥት (በሴት ንግሥት የተመራች) የተገኘችባት ሀገር

11. በዓለም ለመጀመሪያ የሥነ-ጽሑፍ ቋንቋ (ግእዝ) የተገኘባት ሀገር

12. ሳይንሳዊነቱ ተወዳዳሪያ የሌለው የምድሪቱ ቀዳማይ ፊደል ያላት

13. በዓለም ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተፈልፍሎ የተሠራ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ያላት (ምሳሌ የቅ.ላሊበላ ውቅር አቤያተ ክርስቲያናት) ሀገር፣

14. በዓለም ላይ የሚገኘው የአየር ጠባይ (ከውርጭ እስከ ከፍተኛ ሞቃታማ ሥፍራ) በሙሉ ተካቶ የሚገኝባት ብቸኛ ሀገር

15. ለሌላው ዓለም ያበረከተቻቸው እፅዋትና ተክሎች (ዝግባ፣ዋንዛ…)፣ እንስሳትና አራዊት (ዋልያ፣የሜዳ አህያ፣…)፣ እንደ ጤፍና ቡና ያሉ የተለዩ የተፈጥሮ ምርቶችን ያስገኘት

16. የግብርና ሥልጣኔ የተጀመረባት ሀገር፣

17. የድሞክራሲ ሥርዓትን ለግሪኮች ያስተማረች (ቤተ-ሕዝብ፣ ቤተ-ምልክናና ቤተ-ክህነት ሦስቱ የሥልጣን ክፍፍል፤ እንዲሁም የገዳ ሥርዓት ዲሞክራሲያዊ አሠራር)

18. የተፈጥሮ ፀረ-ቫይረስ የሆኑትን እነ ቁንዶን፣ እነ በርበሬን፣ ሚጥምጣን፣ ከአፅራረ ትላትል (ኮሶ፣ መተሬ፣ እንቆቆ፣..)በምድሯ አፍርታ የምትገኝ ሀገር

19. የዋህድ አምላክን ፅንሠ-ሐሣብ ለዓለም ያስተዋወቀች ሀገር

20. የአምላክን ግማደ-መስቀል፣ ተከርኦተ-ርዕስ በቅርስነት የያዘች፤ ተቦተ ፅዮንን ይዛ በመጠበቅ የኖረች ሀገር

21. የቅዱሳን አስደናቂ ቃልኪዳን ያላት (ለምሳሌ በአቡነ አሮን ቃልኪዳን ዝናብ ከአናቱ ባዶ ሆኖ ዝናብ የማያፈሰው ቤተ-ክርስቲያንና የዝንጆሮዎች አዝመራ አለመብላት…

22. በቅኝ ገዥዎች ያልተንበረከከች ሀገር፣ ነጭ ሕዝብን በማሸነፍ የጥቁርን አሸናፊነት ያሣየችና ነጮችን ያሳፈረች ሀገር፣ የነፃነት ተምሳሌት የሆነች ሀገር

23. የተባበሩት መንግሥታን ለመመሥረት ከአፍሪካ ሀገሮች አንዷና ብቸኛዋ የመጀመሪያ ሀገር፤ የአፍሪካ አንድነትን መሥራችና መቀመጫ ሀገር

24. በልዩ ልዩ አስደናቂ ጥበባት የሠለጠኑ ልጆች ያሏት ልመሳሌ ሌባ ሻይ፣ መፍትሔ-ሥራይ፣ ምላ-ሃብት፣…ታምር የሚሠሩት እነ መተት፣….

25. እንግዶችን በክብር በመቀበል ፍትሕን፣ እንግዳ ተቀባይነትን፣ ሃይማኖትኝነትን፣…መመሪያዋ መሆኑን ያስመሰከረች ሀገር፣

26. በእስልምና ሃይማኖት ትልቅ ሥፍራ ያላት (የመጀመሪያውን አዛን የተነገረው ቢላል፣…)

27. በሌሎች የዓለም አቤያተ ክርስቲያናት ያልተገኙ እንደ ኩፋሌ፣ ሄኖክ፣ ዮሴፍ ወልደኮሪዮስ፣… የብሉያት ኦርጅናል መጻሕፍት የሚገኙባት ሀገር

28. ዘመናዊ ህክምና ያልደረሰባቸውን በሽታዎች የሚፈውስ የፀበል ፀጋን የታደለች ሀገር

29. የመንፈስ አዛጦን የታደለች፡- የሥነ ነፍስን÷ የሀብተ መንፈስን (ሥነ-ልቦና)÷ የሥነ-ምግባር ሰናያት (ትዕግሥት፣ ትህትና፣ አፍቅሮ ሰብዕ፣ ንፅሐ-ኅሊና…) ÷ የምድሪቱ መልካም ባህላዊ እሴቶች (ጉድፈቻ፣ ማደጎ ልጅ፣ የነፍስ ልጅ…) ÷ የብዙ ዘመናት ድልብ ባለ መልካም ባለቅርስ (ይሉኝታ፣ ፈሪሃ-እግዚአብሔር፣ ይቅርባይነት፣ አትህቶ-ርዕስ…)…..

30. የቅዱሳት መጻሕፍት የሃይማኖት መርሆዎች በሕዝቦቿ አእምሮ ተፅፈው በተግባር የሚፈጸሙባት ሀገር፣

31. የዓለም ታላላቅ ሃይማኖቶች ተከባብረውና ተስማምተው በፍቅር የሚኖሩባሩት ሃገር ናት፤

32. በአጠቃላይ ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም ውስጣዊና ውጪያው ፀጋዎች፣ ረድኤቶችና ተዎህቦዎች ያሏት ሀገር፤ ..ናት፤ …….ኢትዮጵያ!!!

 

ወልዱ ዘምናለሽ ተራ

‹ምናለሽ ተራ ምናለሽ ተራ
‹በሌለ የለም› ታታሪነት
ሀገር የምታስጠራ
የመርካቶ ኩራት
የዓለም አውራ፡፡›
እያልሁ ሁልጊዜ እዘፍንላታለሁ፤ እዘምርላታለሁ፡፡ ምክንያም እናቴ ናታ!
እንደ! ተወልጄ ራሴን ያገኘሁት እኮ! መርካቶ ምን አለሽ ተራ ነው፡፡ አዎ! መርካቶ “ምናለሽ?” ስትባል እኔን በጭድ ተራ ማኽፀኗ ዱብ አድርጋ አቀረበች፡፡ እኔም በጭን ጎዳናዎቿ ላይ እየተንፈላሰስኩ ቤንዝን ጡቶቿን ጠብቼና ጎማዎቿን ሞቄ አደኩ፡፡ ምናለሽ ተራ “የሌለ የለም ብቻ ነው፡፡“ በሚለው ልዩ ‹ትምሮዋ›ና ምክሯም ቀረፀችኝ፡፡ ይህ ትምርዋም በውስጤ ሰረጸኝ፤ እንዳልለያትም ‹ፎንቃዋ› ያዘኝ፡፡ ስለኾነም የሌለው ነገር እንዲኖር አደርጋለሁ እንጂ ከእሷ መለየት ማለት ‹መደየም› ይመስለኛል፡፡
በእናቴ ቤት በምናለሽ ተራ እድሜዬ ለሥራ እንደደረሰም በመጀመሪያ በ‹ቅፈላ› ሽቀላ ተሠማርቼ ነበር፡፡ የተዋጣልኝ የልጅ ‹ቀፋይ› ሆኜ ነበር፡፡ ባቀፋፈሌም ስልተኛ ነበርኩ፤ በዋናነትም ፍቅረኛሞችን ብቻ እጠይቃለሁ፤ አቀፋፈሌንም ቢኾን አንጀት ይደርሳል እንጂ ጆሮ ጠልዞ በሰልቸት አይቀርም፡፡ ፍቅረኞችን ስቀፍልም በሴቷ በኩል ከኾነ “ቆንጅት! እናንተንስ አይለያችሁ፤ ስለ ፍቅር አምላክ?” እላታለሁ፤ ፍቅር ካላት በፍቅር አምላክ አትጨክንም፤ ‹ታሽረኛለች›፤ ‹ኮይን› ባይኖራት እንኳን በፍቅረኛዋ ‹ታስገጨኛለች› እንጂ ዝም ብላ ‹አትመርሽም›፡፡ በወንዱ በኩል ከኾነም “ስለ ቆንጅት? ስለ ፍቅር አምላክ?” እለዋለሁ፤ እሱም ወይ በውለታነት ቆጥሮ ወይም ‹ሸም ቆንጥቶት› ያለውን አውጥቶ ያሽረኛል፡፡ ምክንያቱም ፍቅረኛሞችን “ስለ ማርያም ፣ ስለ ገብርኤል…” ብሎ መቀፈል መሰልቸቱን ነቄ ብያለኋ! ፍቅረኛሞች ከኾኑ የሚያመልኩት የፍቅርን አምላክ ነው፡፡
ያኔ! በ‹ቅፈላ› ማንም ተፎካካሪ አልነበረኝም፤ ምክንያቱም አቀፋፈሌ ነዋ! ኾኖም በቢዝነሱ ብዙ መቀጠል አልቻልኩም፡፡ አብረውኝ የሚኖሩ ቋንጣ፣ ዶዮና ባሪያው የሚባሉ ‹ጀለሶች› ነበሩኝ፤ እነሱም መቀፈል ሲያቅታቸው እኔን የ‹ጨብሻ›ና “የኡፋ” ቀላቢያቸው አደረጉኝ፡፡ በረጃጅም እጆቻቸው እየሰበሰቡ በሰፋፊ ጉሮሯቸው የሚያስገቡትን የ‹ቡሌ› መጠን አልቻልኩትም፤ እነሱንም እያደነቅኩ መኖርም ሰለቸኝ፡፡ ለምሳሌ ዶዮ አንድ ፌስታል ኡፋ ብቻውን ‹ሲጥ› ያደርጋል፡፡ ቅፈላ ደግሞ አይኾንለትም፤ ከቅፈላ ይልቅ ‹እንክብክብ› ይችላል፡፡ ክፋቱ በእንክብክብ ያገኘውን ‹ሳቢ› ‹እብስ› አድርጎት ይመጣል፡፡ የተገኘውን እኩል ተሰልፎ ለማጥቃት ግን ማንም አያህለውም፡፡
ቋንጣ ቡሌ ሲደፍቅ እጁ አይበቃውም፤ መቀፈል ደግሞ ብዙም አይችልም፡፡ ቡሌ ቅፈላ ግን የእጁ ነው፤ ወይ ከምግብ ቤቶች በኮንትራት ቆሻሻ በመድፋት ኡፋውን ይሰበስባል ወይም ከእኔ ‹ኮይን› ተቀብሎኝ አንድ ወይም ኹለት ፌስታል ይሸምታል፡፡ ኮይን ለመቀፈል ከተሠማራ ግን ቅፈላውን ትቶ ‹ቺኮችን› መጥበስ ይወዳል፡፡ በዚህም ብዙ ጊዜ ‹ተቦቅሷል›፡፡ ‹ጋያ› ሳይነፋ እና ‹በርጫ› ሳያደርስ አይውልም፡፡
ባሪያው ቅፈላም፣ ኡፋ መሰብሰብም አይኾንለትም፡፡ የሚኾንለት ድርቶ መስፋት ነው፤ ለኹላችንም አንዳንድ ድርቶ ሰፍቶልናል፡፡ ኹላችንም እሱ የሠፋልንን ድርቶ አንድ ላይ በመደራረብ ለብሰን እናድር ነበር፡፡ ቡሌ በመድፈቅ ግን ከዶዮ አያንስም፤ በተለይ ኡፋው ካነሰ የጎረሰውን በግራ እጁ ለመዋጥ እየገፋ በቀኙ መዳፉን ሞልቶ ይሰበስባል፡፡ በዚህ የተነሣ ከእሱ ጋር ‹ሻሞ› ለመሰለፍ የሚፈልግ አልነበረም፡፡
ቅፈላን በደንብ የምችል እኔ ስለነበርኩ ለ‹ጀለሶቼ› የ‹ኮይን› ምንጫቸው ነበርኩ፡፡ በቀን ሁለትና ሦስት ጊዜ ፊልም የምንመለከትበትን ሒሣብ የማወራርደው፤ ኡፋ ሲጠፋ የእናት ጉርሻ ‹ኮይን› የምዘጋው፤ የሲጋራ፣ የጨብሲ፣ የበርጫና የሌሎችን ወጪዎች ሳቢ የምዘጋው እኔ ነበርኩ፡- በተለይም በ18 ቀበሌ የምንመለከተውን እስፔሻል፣ የሕንድና የአሜሪካ ፊልም በእኔ እጅ ነበር፡፡ እያደር ግን የነሱ ሳቢ ዘጊ እኔ ብቻ መኾኔ ድብርት ለቀቀብኝ፡፡ በተለይም እነሱ እስፔሻላቸውን እየኮመኮሙ ‹አንቺ ቀፍይ› እያሉ ‹ሸም የማይቆነጥጣቸው› ስለኾኑ አስደበሩኝ፡፡ “ፋራያችኹን” ፈልጉ ብዬ ከዚያ አካባቢ ‹መርሽሁባቸው›፡፡ ለጊዜውም እናቴን ምናለሽ ተራን ትቼ ወደ ሰባተኛ ሰፈር ለመሰደድ ተገደድኩ፡፡
እዚያም ሰው መኾን አምሮኝ ሊስትሮ ጀመርኩ፡፡ ሰው መኾን ግን አልቻልኩም፤ ሰው መኾን ከባድ ነው፡፡ ምክንያቱም የሊስትሮ ወንበሬን ወንዶች የ‹ሸሌ› ቤት ወረፋ መጠበቂያና ማስቀየሻ አደረጉት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ የሽንት መጣጭ መኪና መሰልኳቸው መሰለኝ ቦርሽልን በማለት የሸኖ ቤታቸውን በጫማቸው ይዘው መጥተው አፍንጫዬን ከማሽተት አስኮረፉት፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ እዚያ አካባቢ ጉልቤ ሊስትሮዎች ተፎካከርከን ብለው ቡርሽ መለማመጃ አደረጉኝ፡፡ ከዚያም ‹ሰፈሬ ማሪኝ› በማለት ምናለሽ ተራ ተመልሼ ‹ከች› አልኩ፡፡ በምናለሽ ተራ እኮ ከጀለሶቼ ማስመረር ውጭ ማንም ዝንቤን እሺ አይለውም፡፡ ከዚያም ሥራ ቀይሬ መሥራት ጀመርኩ፡፡
በልጅነቴ ስቀፍል ብዙውን ጊዜ የ‹ቺኮች›ን ቦርሳ ‹መከለም› አበዛ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን አንዷ ቦርሳዋን ለመያዝ ተጠይፋው ስታሰቃየው አይቻት አላስችል ቢለኝ “ልያዝልሽ” አልኳት፡፡ “‹ድክሞ› ብሎኛል” ስትለኝ ጊዜ ተቀበልኳት፡፡ በቦርሳዋም ጥሩ ሳቢ አገኘሁ፤ እንደልቤም በአሜሪካና በሕንድ ፊልም፣ በበርጫና በጨብሲ ተዝናናሁ፡፡ አንድ ቀን ደግሞ አንዷ ‹ጩባ› በአንገቷ ላይ ተሸክማ ታወዛውዘዋለች፤ ‹መንጩ› አድረኳት፡፡ ከዚያ በኋላ በምናለሽ ተራ ታዋቂ “ላቦሮ” ኾንኩ፡፡
“የላቦሮነት” ሥራ በፊት በፊት ያበላ ነበር፡፡ ዛፓም አያስቸግርም ፤ ተቀናቃኝም አልነበረበትም፡፡ ትንሽ ቆይቶ ግን ‹ጉልቤዎቹ› እነ ቋንጣ፣ ዶዮና ባሪያው አስቸገሩኝ፡፡ አንዲት ቦርሳ ይዤ “ተቄ” ስል እየተከታተሉ ይቀበሉኝ ጀመር፡፡ ጭራሽ እኔን እየተከተሉ ‹በጋቢና ተሣፈር›፣ ‹የኋላ ወንበር ተቀመጥ› እያሉ በየትኛውም ሰው ኪስ ዘው እንዲል ‹አጃኳሚዎች› ኾኑ፡፡ በዚህም ‹ሙዳችን› አብሮ ሊሔድ አልቻለም፡፡ ምክንያቱም የእኔ ደንበኛች ‹ቺኮች› ናቸዋ! እነሱ ግን እኔ እንቢ ስላቸው ራሳቸው የኹሉንም ወንድ ኪስ እንደፍራለን ብለው ጥርሳቸውን አጡ፤ ፊታቸውም ታርሶ፣ ታርሶ ላቦሮነታቸውን ገጠሬ ሳይቀር አወቀባቸው፡፡ ‹መንጩ ማድረግ› ሲያቅታቸውም እኔ አንዲት ቦርሳ ይዤ ‹ተቄ› ስል ወይም ‹ጩባ› ላፍ አድርጌ ‹ሽል› ስል ተከትለው ‹ቴባ! ቴባ!› እያሉ በመካፈል አሠለቹኝ፡፡
ለምሳሌ አንድ ቀን የተቀመመች ምግብ ቤት አጠገብ የአንዷን ‹ቺክ› ቦርሳ ‹መንጩ አድርጌ› ተቄ ስል ለካ ከኋላዋ ልጁቱን የተከተላት ልጅ ኖሮ አሯሯጠኝ፡፡ እኔም የምገባበት ሳጣ በሞሰብ ተራ ወረድ ብሎ ያለው የብረት ተራ ሸኖ ቤት ወረፋ የያዙትን ‹ተቅማጥ›፣ ‹ተቅማጥ› ብዬ አንዱ የሸኖ ክፍል ዘው አልኩኝ፡፡ የሸኖ ሰልፈኞችም ስለገባቸው የሚያሯርጠኝ ልጅ እንዳይገባ ‹ወረፋ ያዝ› ብለው አስቆሙልኝ፤ በዚህ አጋጣሚም ልጁ ከሰልፈኞች ጋር ሲጨቃጨቅ ከሸኖ ቤቱም በጓሮ በኩል በመዝለል በወንዙ ‹ተቀነጠስኩ›፡፡
ከዚያም ዘወር ብዬ ቦርሳውን ክልም ሳደርገው ‹አመዱን›፣ ‹ቸንቶውን›፣ ‹ደቹን›፣ ‹ቢጫውን› ሳቢ አጭቋል፤ ‹ፈንዱ› አልኩኝ፡፡ ይኹንና እነ ዶዮ በጎን ተከታትለውኝ ኖሮ ‹ቴባ› ብለው ተካፈሉኝ፤ በሸኖ ቤት ላስቀየሱኝም ‹ስቦጭቅ› አንድ ‹አመድ› ከምናምን ብቻ ተረፈኝ፡፡ ልክ እንደዚህ እኔ ስንት ተሰቃይቼ ያገኘሁትን ሳቢ እየተቀበሉ ሲያስቸግሩኝ ሥራው ራሱ እያስጠላኝ መጣ፡፡ በተጨማሪም በምናለሽ ተራ “ላቦሮነት” የሚሠሩ “ጮካዎች” በዙ፡፡ በዚህ የተነሣ ቺኮችም የቦርሳ መያዢያቸውን ቀየሩ፡፡ በግልገል ሱሪያቸው ውስጥ እየቀረቀሩ ለሚገዙት እቃ ዋጋ ለመክፈል ሲቸገሩ ብዙዎችን አየኋቸው፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ማንም በሞጨለፈው “ዛፓ” ኹሉ እኔን “ውለድ” እያለ ባልወለደ አንጀቱ የገረፋ መሰልጠኛው አደረገኝ፡፡ ስለዚህ “ላቦሮነት” እርም ብዬ ተውኩት፡፡ እሱን ትቸም በድንችና ሽንኩርት ተራዎች ‹የጉርጎራ› ሥራን ጀመርኩ፡፡
እኔ ድንችና ሽንኩርት ተራዎች በመሄድ የጉርጎር ሥራን ሳልጀምር በፊት በየተራዎቹ ብስባሽ መንገድ በመዝጋትና በመሸተት ሻጮችንና ገዥዎችን አስቸግሮ ነበር፡፡ ምክንያቱም ገዥዎችም ኾኑ ሻጮች አንድ ድንች ወይም ሽንኩርት አምልጧቸው መሬት ከወደቀ በይሉኝታ አያነሱትም ነበር፡፡ አንድ ቀን ግን እኔ በዚያ አካባቢ ‹ሳንዣብብ› ነጋዴዎቹ አዋጥተን እንገጨኸለን ጥረገው አሉኝ፡፡ እኔም ቆሻሻውን ኹሉ ከአካባቢው ፀዳ ፀዳ ካደረኩ በኋላ የሚወድቁ ድንቾችንና ሽንኩርቶችን እየጠበቅኩ በመልቀም አጠራቀምኳቸው፡፡ ከዚያም ወደ ማታ አካባቢ ዋናው አስፋልት ላይ ወስጄ በመዘርገፍ በቅናሽ ዋጋ ሸቀልኳቸው፡፡ ከዚያ በኋላማ! ሸቀላው ጣመኝ ሽንኩርትና ድንችም እንኳን በመሬት ወድቀው ሊሰበስቡ ይቅርና መሬት መንካትም አቃታቸው፡፡ ከአየር ላይ እየቀለበኩ ሸቅልኳቸዋ! በዚህም ድንችና ሽንኩርት ገዝተው መመገብ የማይችሉ ሰዎች ከእኔ በርካሽ በመግዛት ጥፍጥናውን ለመዱት፡፡ ገና የመሸጫ ሰዓቴ ሳይደርስም በአስፋልት ላይ ሰልፍ ለመያዝ ይጠብቁ፤ ሰዓቱ ሲደርስም ለመግዛት በሻሞ ይቧቀሱ ጀመር፡፡
በተለይ ሳቢዬ እየጎለመሰ ከሄደ በኋላ በጉርጎራ ሰበብ ኹለት ዓይነት ሥራዎችን መሥራት ጀመርኩ፡፡ በሌሊት ተነሥቼ ለድንችና ሽንኩርት አውራጆች ሲጋራ እሸቅላለሁ፡፡ አውራጆቹም ለሲጋራቸው ሲሉ ከተሸከሙት ላይ እያሾለኩ ወይም በአይሱዙ መኪናዎቹ ላይ የፈሰሰውን እየለቀምኩ ስወስድ ‹እስታ› ይላሉ እንጂ ‹አይገግሩብኝም›፡፡ እኔም እየተከታተልኩና እየተንጠላጠልኩ የጎረጎርኩትን ድንችና ሽንኩርት በአሠርኳቸው እጅጌዎቼና በታጠቅኩት ወገቤ ዙሪያ እያስገባሁ እቀረቅራለሁ፡፡ ከዚያም በከረጢት በመቆጠር ከአንዱዋ ቸርቻሪ ጋር አስቀምጣለሁ፡፡ ትንሽ ቆይቼም ከአውራጅ ወዛደሮቹ የሲጋራ ኮይኔን እሰበስባለሁ፡፡ ስለዚህ ሲጋራ የጉርጎራ ሥራዬን በአግባቡ ለማከናወን፤ ጥሩ ሳቢ ለማግኘትም አስችሎኛል፡፡ በዚህም የጉርጎራ ሥራዬን ተዝናንቼ መሥራት ችዬ ነበር፡፡
ዶዮ፣ ቋንጣና ባሪያው ደግሞ በጉርጎራ ሥራዬ ጥሩ ኮይን ማግኘቴን ሲሰሙ ቅናት አቃጠላቸው፡፡ በየቀኑ እየመጡም ‹የሲጋራ ግጪን›፣ ‹የኡፋ ቻይን›፣… እያሉ መቀፈል ‹አሪፊነት› አደረጉት፡፡ እንቢ ስላቸውም ለአካባቢው የሽንኩርትና ድንች ነጋዴዎች የበፊቱን ‹የላቦሮነት› ሥራዬን እየቀደዱ አስፎገሩኝ፡፡ በዚህ የተነሣ ቸርቻሪዎቹ እንዳልጠጋቸው ‹ገገሩብኝ›፡፡ በዚያ ላይ ብዙ ጎርጓሪዎች ስለተፈጠሩ ተፎካከሩኝ፡፡
በፊት ድንችና ሽንኩርት ሻጮች የወደቀውን ለማንሳት ተጠይፈው በብስባሽ ሽታ ተቸግረው እንዳልነበር እኔ የፈጠጠውን እየጎረጎርኩና የወደቀውን እየለቀምኩ በወረፋ ስሸቅለው ሲያዩ ጊዜ አንዲት ድንች ወይም ሽንኩርት ለመውደቅ ከጆንያው ብቅ ስትል ወይም ከወደቀች ለመውሰድ በሻሞ መጣላት አበዙ፡፡ ከእኔ ይገዙ የነበሩ ድሆችም ድንችና ሽንኩርት መመገብ ሲለምዱ ጊዜ ጣማቸው፤ በጉርጎራ ሥራም ላይ ተሰማሩ፡፡ ጭራሽ ይባስ ብለው የሕጻን ልጆቻቸው ጥርስ ማብቀያ አደረጉት፡፡
ሕጻኖቻቸው ገና ቆመው መሄድ ሲጀምሩ የተቀቀለ ድንች ያቀምሷቸዋል፡፡ ማውራት ሲጀምሩ የጉርጎራን ዝና እያወደሱ ይቀዱላቸዋል፡፡ በዚያውም ድንችና ሽንኩርት ተራ በማምጣት ለቀማና ጉርጎራ ያስከልሟቸዋል፡፡ በዚህ የተነሣ ልጆቹ በአይሱዙ የጭነት መኪናዎች ላይ እየተንጠለጠሉና በተጫኑ ኩንታሎች መካከልም እየተሸለከለኩ በመጎርጎር አከፋፋይ ነጋዴዎችን አስመረሩ፡፡ በእነሱ ድርጊትም የእኔ የጎርጓሪነት ስሜ ጠፋ፡፡ በአካባቢውም ‹ውር!› እንዳልል ተወሰነብኝ፡፡ በዚህ የተነሣ የድንችና የሽንኩርት ተራ የጉርጎራ ሥራዬን ለመተው ተገደድኩ፡፡
ከዚያ በኋላ ‹ምን አዳረቀኝ› በማለት ምንም ተቀናቃኝ የሌለበትን የእንክብክብ ሥራ ጀመርኩ፡፡ በመርካቶ ውስጥ በመሽከርከር የተለያዩ እቃዎችን እንደ ዶዮ ማንከብከብ ሥራዬ ኾነ፡፡ የእንክብክብ ሥራም በፊት በፊት ያዋጣ ነበር፡፡ በቀን ቢያንስ አራት ወይም አምስት ‹ወረቀት› አይጠፋውም፡፡ ይህን ያህል ሳቢ ካገኘሁም አልቸገርም፡፡ ምክንያቱም ባገኘኋት ኮይን ቁርሴን ሁለት ሽልጦ ‹በቸላ› እገዛና በሚጥሚጣ እነፋለሁ፡፡ ከዚያም ሠራ ሠራ አድርጌ ምሣ ሰዓት ሲደርስ ‹በቸላ› ምናለሽ ተራ ከምትገኘወቅ እናት ቤት በእጄ ሣህንነት አምስት ጉርሻዎች እቀበላለሁ፡፡ ያ ማለት በቃ! ዝግ ነው፤ እንክብክብ ራሱ ይቀላል፡፡ ማታም ቢኾን ‹አንቡሌ ቤት› ‹ቅንጥብጣቢ› ስላለ ‹በየካ› አወራርዳለሁ፡፡ በዚያውም የሁለት ሦስቷን ብርሌ አንገት በመያዝ እሞጨሙጫለሁ፤ እንሳሳማለን፡፡ ኤዲያ! እርካታ ያለ እዚያ ነው እንጂ! አዳርም ቢኾን ‹በቸላ› በሽበሽ ነበር፡፡ ከፈለኩ ጎጃም በረንዳ ወይም አሜሪካ ግቢ ትኋንና ቁንጫ ‹እቅፎ አድርጌ› ሞቆኝ ደቀሼ አድር ነበር፡፡
ጎጃም በረንዳና የአሜሪካ ግቢ አድር የነበረበትን ጊዜም ሳስታውሰው ልዩ ትዝታ አለው፡፡ ያን ጊዜ እኔ ከምናለሽ ተራ በረንዳ አዳሪነት አልፌ ቤት የገባሁበት ወቅት ነበር፡፡ ጎጃም በረንዳም መሬት ላይ ‹ቸላ› እየከፈልኩ በማደር ቤተኛ የኾንኩበት ቤት ነበር፡፡ እዚያ ቤት የምናድረውም መጀመሪያ ከባሉካዎቹ ሽቦ አልጋ ሥር እስከ በሩ ድረስ ‹ቸላ› ‹ቸላ› የዘጋነው ገብተን በአንድ ጎናችን ብቻ ትንኋንና ቁንጫ ሾልከው እንዳያልፉ አድርገን እንተኛለን፡፡ በዚህ መኝታችን ተባዮች መብላት የሚፈቀድላቸው ከአንድ በኩል ብቻ ነው፤ ተከላካይም የለባቸውም፡፡ ምክንያቱም እጅን አሾልኮ ማከክም ኾነ መዳጥ ስለማይቻል የፈለጉትን ያህል መቦጨቅ መብታቸው ነው! ተባዮቹ ግን መተላለፊያ በማጣት መንገድ እየጠበባቸው የሸዋዚንገርን፣ የቻርኖሪስን፣ የሬንቦን የጦርነት ፊልም ይሠሩብናል፡፡ እዚያ ቤት የሚያድሩት ደግሞ አብዛኞቹ ‹ጮካ›፣ ወዛደር፣ ‹ቁጭ በሉ›ና ቀፋይ የሆኑ ሰካራሞች ስለነበሩ እንቅልፋቸው ወፍራም ነበር፡፡ ትንፋሻቸውም ብርድን ከቤት ጠርጎ ያስወጣል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የሚያስወጣ ሰካራምም ያጋጥማል፤ ሆኖም እሱኑ ራሱን እናስወጣዋልን እንጂ ዝም የሚለው የለም፡- መበከሉ ግን አይቀርም፡፡ እያደር ግን መኝታው ለእኔ ‹ሙድ› የሌለው ኾነብኝ፡፡
ትንሽ ቆይቶም የመደቀሻ ደረጃዬን በማሻሻል ቆጥ ላይ ወጣሁ፡፡ ይኹንና የቆጥ መደቀሻ፡-
 አንደኛኛ የሣር ፍራሽ ስለኾነ የቁንጫ፣ የቅማልና የትኋን አፎች ይጨምርበታል፤
 ሁለተኛኛ ሣሩም ቢኾን ወፋፍራምና በስሱ የተጎዘጎዘ ስለኾነ ቆዳ ይልጣል፤
 ሦስተኛ በቆርቆሮውና በግድግዳው መጋጠሚያ የሚገባው ብርድ ከፍተኛ ስለኾነ አይቻልም፡- ይፎደፉዳል፤
 አራተኛ በቆጥነት የተረበረበው አጠና ቀጫጭን ስለኾነ እየተልመጠመጠ ከአኹን አኹን ተሠብሮ ሾለኩ የሚል ፍርሀትን ያመጣል፤
 በተጨማሪም ዋጋው ‹የካ› ስለኾነ ከመሬቱ ይወደዳል፡፡
ስለዚህ ቆጥ ላይ ማደርን ትቼ ከባሉካዎቹ አልጋ ጠርዝ ላይ ተደርቤ እንድደቅስ ተፈቀደልኝ፡- ጠባይ ነዋ!፡፡ ከዚያ ግን በወዲያ በኩል የአልጋ ጠርዝ ትተኛ የነበረች የባሉካዎቹ ልጅ ‹ከእሱ ጋር ካልኾነ› ብላ አቅጣጫ በመቀየር መጣችና እኔ ጋር ተወሽቃ መደቀስ ጀመረች፤ ‹ãኸ! ልትደፍሪኝ ነው› ብዬ ከቤቱ ጠፋሁ፡፡ እሷ እንዳታገኘኝም ለጊዜው ወደ አሜሪካ ግቢ ተቀየስኩ፡፡ ከተረሳሳልኝ በኋላም ግን ጎጃም በረንዳዬ ተመለስኩ፡- ምን ታመጣለች?
እዚህ ላይ ከተወሰነ ጊዜ ቆይታ በኋላም ጎጃም በረንዳ ሳድር ያጋጠመኝን ሳስታውስ የቺኮችን ቀልብ የመሳብ ኃይል እንዳለኝ አሳውቆኛል፡፡ በዚያን ጊዜ እንክብክብ ጥሩ ኮይን ይገኘው ስለነበር የአስተዳደር እድገቴን በማሻሻል ‹ዱ ወረቀት› እየከፈልኩ አልጋ ለማየት ፈለኩ፡፡ አስቤም አልቀረሁ አንድ ሰው ብቻ የምታስተኛ አልጋ ያለችበት ጠባብ ቤት ውስጥ ገባሁ፡፡
ስለ አልገዋ አከራዬ እንደነገሩኝ ከኾነ በፊት በቁንጅናቸው ጊዜ ቢዝነስ ይሠሩባት ነበር፡፡ በቢዝነስ ሥራቸውም አኹን እቤት ያለችውን ቺክ ወለዷት፡፡ ልጅቱ እያደገች ስትመጣ ግን የአልገዋ ቢዝነስ እየቀዘቀዘ፤ መጠኗም እየጠበበ መጣ፡፡ በዚህም እናትና ልጅ ችግር ገጠማቸው፡፡ ችግራቸውን ለመቋቋም ግን አንድ ዘዴ ቀየሱ፡፡ ይኸውም ከልጃቸው ጋር ተስማምተው ቀን ቀን እነሱ በየተራ ሊደቅሱባት ማታ ማታ ደግሞ ሊያከራዩዋት ወሰኑ፡- ቀን የሚከራይ ስለማይኖር፡፡ በዚህ ሰዓትም ከእኔ ጋር ተገናኝተን አከራዩኝ፡፡ ኾኖም እናትና ልጅ ውጭ ለማደር ተገደዱ፡፡
እኔም ታሪካቸውን ስሰማ ስላሳዘኑኝ ሴትዮዋን ‹አልገዋ ከበቃች ልጅቱ ከእኔ ጋር ተደርባ ትተኛ፡፡› አልኳቸው፡፡ ይህንን ያልኩት ስላሳዘነችን ነው እንጂ ከቺክ ጋር መደቀስ አለመድኩ?
እሳቸውም ተደስተው ‹እንዳውም ከወንድ ጋር መተኛት ትለምድልኛለች፡፡› ብለው ተስማሙ፡፡ አልጋዋን ስንሞክራት እውነትም በቃችን፡፡ ከዚያም ከልጅቱ ጋር ስንደቅስ! ስንደቅስ! እናትዋን ሳይቀር አስቀናናቸው፡፡ ችክ ‹እቅፎ› አድርጎ ማደር መጣሙን ያወቅኩት ያን ጊዜ ነው፡፡ እያደር ግን እናቷ በቅናት ነቀሉ፡፡ እሳቸውም ‹እኔ ብቻዬን ሁልጊዜ ውጭ ከማድር እየቀየርሽኝ አንዳንድ ቀን እኔም አብሬ ልደር› አሏት፡፡ ልጅቱ ግን ከእኔ ጋር ከደቀሰች በኋላ መነሳት ያቅታት ጀመር፡፡ ትንሽ ቆይቶማ እኔው ራሴ ‹ፎንቃ› ይዞኝ ቁጭ!፤ ከልጅቱ? በእሷ ‹ፎንቃ› የተነሣም በአካባቢው እያንዣበብኩ እስከመዋል ደረስኩ፡፡ እናቷ ግን በአካባቢው ‹ውር› እንዳላል በሰፈሩ ጉልቤዎች አስወቁኝ፤ ጭራሽ ጉልቤዎቹ አጅበዋት እንዲዞሩ አደረጓት፡፡ እኔም በእሷ ፎንቋ ተለክፌ የለ? እንክብክብ እንዴት ልሥራ?
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማንከብከብም አላዋጣ አለኝ፡- ፈላጊው በዛ፡፡ በፊት በፊት ዕቃ ለመሸከም ‹ቅብርር›፣ ‹ጅንን› እንዳላልኩና እንዳላማረጥኩኝ እንኳን ተንቀባርሬ ልተወው ይቅርና የማንከበክበውም አጣሁ፡፡ ምክንያቱም ወደ መርካቶ ዕቃ ለመግዛት የሚመጡ ሰዎችን ገና ከታክሲ ሳይወርዱ ‹እኔ ልያዝላችሁ› የሚሉ ወዛደሮች በዙዋ!፡፡ እነ ዶዮ፣ ቋንጣና ባሪያውም እንደ እኔ ወዛደር መስለው ‹የማስቀየስ ላቦሮነትን› አጧጧፉት፡፡ የእናት ቤት ጉርሻም ሽሚያው በዛበት፡፡ በፊት “በቸላ” ዝግ እንደዘጋሁበት “የካ” የሚከፈለው ለሽታ ኾነ፡፡ ለሽታ ለሽታማ! በሸራተን አላልፍም ብዬ ተውኩት፡፡ አንድ ቀንም ‹የጥሩ ምግብ ሽታማ! ሸራተን ‹ጥግቦ ብዬ› እመጣለሁ› ብዬ በሆቴሉ በር ባልፍ፣ ብመላለስ ሸራተን መዓዛ አልባ፤ ሽታ የለሽ ሆኗል፡፡ ኋላ ስሰማ የምግብ ሽታው ኮይን ማስገባት ስለቻለ እዚያው በግቢው መሸቀሉን ሰማሁ፡፡ ጊዜ ማረሳሻ የሚኾነኝ አንቡላም ቢኾን ተወደደ፡፡ እሱንም ቢኾን በ“ቸላ” አንገት እንዳላጫወትኩበት ማሩ በአፌ እንዳልዘነበ፤ ወለላው በጉሮሮዬ እንዳልተንቆረቆረ፣ በቂጥ የለሽ ጆሯም ብርጭቆ ስኳር በጥብጠው “ብር ከቸይ” አስገቡት፡፡ ማር የነካው አንቡላም ማግኘት ትዝታና ምኞት ኾነ፡፡
(ይቀጥላል…)

 
1 Comment

Posted by on February 29, 2012 in ዐጫጭር መጣጥፎች

 

አበሳ መምህር

ብዙውን ጊዜ ስለመምህር  ሲነሳ የሚጠቀሰው

“አዬ የመምህር ያለበት አባዜ፣

አስተዋይ ተማሪ ባጋጠመው ጊዜ”

የሚለው የከበደ ሚካኤል ግጥም ነው፡፡ እኔን  ያጋጠመኝ ግን ሌላ አበሳ ነው፡፡ እስቲ ለማሳያ እንዲኾነኝ በፊዚክስ ትምህርት ተመርቄ ማስተማር የጀመርኩበትን የመጀመሪያዋን ክፍለ ጊዜ ኹኔታ ብቻ ልጥቀስ፡፡

ገና ክፍል ውስጥ ስገባ ጨነቀኝ ቢኾንም እንደምንም ራሴን አረጋግቼ የዕወቁኝ ሰላምታ “Good Morning!” ማለት፡፡

መልስ ታዲያ ምን ኾነ “ከጉድ ያወጣን!”

እኔም ገና በመጀመሪያ ቀን ክፉ አልናገርም በማለት ችዬ ዝም አልኩኝ፡፡ ባይኾን ትምህርት ከመጀመሬ በፊት አንዳንድ የሥነ-ሥርዓት ሕጎችን ላሳውቃቸው “Abcent is not allowed” ብዬ ጻፍኩኝ፡፡

ወዲያው አንዱ ተማሪ እጁን አውጥቶ “ቲቸር!” አለኝ

“አቤት!”

“ሥዕል ነው ጽሑፍ?”

እርር! ነው ያልኩት እርር! “ጽሑፌ ለእኔ ይነበበኛል እንዴት ሥዕል ያደርገዋል” ብዬ፡፡ ኾኖም መቼስ ምን አደርጋለሁ ስጠየቅ መመለስ አለብኝ እንጂ በማለት “ኧረ! ጽሑፍ ነው “ማንም ተማሪ እንዳይቀር ለማለት ነው፡፡” አልኩኝ፡፡

“እሺ! ጽሑፍ ከኾነ በአማርኛ ነው የተጻፈው በእንግሊዘኛ?” ብሎኝ ቁጭ!

“ኧረ! በእንግሊዘኛ ነው!”

“እሺ! እስፔሊንጉን ንገሪን የመጀመሪያው ምንድ ነው?”

“A”

“ቀጥሎስ”

“B”

“ከዚያስ?”

“C”  ኾኖም “ስፔሊንጉን”ን መሳሳቴን አወቅኩ፡፡

ነገር ግን በዚህ ጊዜ ከጎኑ የተቀመጠው ልጅ እጁን አውጥቶ “በቃ! በቃ! ቲቸር እያንዳንዱን ስፔሊንግ በመዘርዘር ከምትለፊ ከ”A” እስለ “Z” በራሳችን እንጻፍ?” አለኝ፡፡

በዚህም ቢኾን እርር! ነው ያልኩት እርር! “እኔ የ10ኛ ክፍል የፊዚክስ መምህርት እንጂ የመዋዕለ ሕጻናት  A, B, C, D አስቆጣሪ አደረገኝ እንዴ?” ብዬ፡፡ ነገር ግን ምን አደርጋለሁ መልስ ከመስጠት ውጭ! “የተጻፈው A, B,C, D ሳይኾን ” “Absent is not allowed” የሚል ነው አልኩት እስፔሊንጉንም አስተካክዬ፡፡ እነሱም እግዜር ይስጣቸው ይኹን! ይኹን! ብለው ተስማማን፡፡

ከዚያም ያንን አጥፍቼ የእለቱን ትምህርት መጻፍ ጀመርኩ፡፡ ይኹንና ወሬያቸው አላጽፍ አለኝ፡፡ በተለይም ከኋላ ጥግ ከዳርና ዳር አካባቢ ጨዋታው ደራ፡፡ ከቀኝ ጥግ በኩልም አንድ ተማሪ “ተቀበል!” አለ፡፡

“እሺ! ጀምር” አለው ከግራ ጥግ በኩል የተቀመጠ ተማሪ፡፡ እኔም “ምንድነው?” ብዬ ዘወር ስል ተቀባዩ ተማሪ እየተዘጋጀ “ቆይ! አንዴ ቲቸር!” አለኝ፡፡

“ና ውጣ ና ውረድ ሲል እየሰማነው” አቀባዩ

“ና ውጣ ና ውረድ ሲል እየሰማነው” ተቀባዩ፡- በዜማ

“ወደ ላይ ወደ ታች አርሶት አገኘነው በለውማ!”

“ወደ ላይ ወደታች አርሶት አገኘነው፡፡”

ነገሩ ገባኝ፤ ቢገባኝስ ምን አደርጋለሁ እርር! ድብን ከማለት ውጭ! ጸሑፌ መስመሩን ስቶ ወደ ታች መውረዱን መንቀፋቸው ነውና፡፡ በዚህም ክፍሉ በሣቅና በጭብጨባ ቀውጢ ኾነ፡፡ እኔማ ምን እላለሁ? አፍሬና ደንግጬ ዝም ነው እንጂ! ይባስ ብሎ ሌላ ጉድ አጋጠመኝ የተወሰኑት እየሣቁ በመኸከለኛው እረድፍ ከኋላ ወንበር የተቀመጡት ሴትና ወንድ ተማሪዎች ጨዋታ ጀምረዋል፡- የሴትና የወንድ የከንፈር ጨዋታ! የሚገርመው ደግሞ ፊት ለፊታቸው ተገትሬ እንደፊልም ቀራጭ ቆጠሩኝ መሰለኝ ወይ እፍር! ወይ ድንግጥ!

ቢቸግረኝ እኔ አፍሬ ፊቴን ወደ ብላክቦርዱ አዞርኩኝ፡፡ ግን ደግሞ የክፍሉን ሥነ-ሥርዓት የማስከበር ኃላፊነትም አለብኝ፡፡ ስለዚህ ኮስተር ብዬ ወደ ተማሪዎቹ ዞርኩኝ፡፡ ሁለቱ ልጆች ጨዋታቸውን አድርተውታል፡፡ የተጋባባቸውም ጀማምረዋል፡፡ ገርሞኝ ዝም ብዬ እመለከታቸው ጀመር፡፡ እነሱ ግን “ማፈርና መደንገጥ ድሮ ቀረ” ያሉ ይመስላሉ፡፡

ይባስ ብሎ የጀመረው ልጅ “ቲቸር ምን ያስፈጥጥሻል ከፈለግሽ አንቺም ከአንዱ ጋር ተጫወቺ ወይም ዘወር በይልን ሙዳችንን አታጥፊው” ሲለኝ ድንግጥ ነው ያልኩት ድንግጥ! ብልስ ምን አመጣለሁ አልመታው ቢያንስ ይበልጠኛል፡፡ እንዲሁም የተማሪን ዝንብ “እሽ!” ያለ መምህር ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ ከሥራ ውልቅ፡- ልብሱን የነካ ወደ እስር ቤት፤ አካሉን ያቆሰለ ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ….” የሚል ማስጠንቀቂያ አለ ሲባል ስለሰማሁ ችዬ ዝም!

ግን ደግሞ የክፍሉን ሥነ-ሥርዓት የመቆጣጠር ኃላፊነቴንም መወጣት አለብኝ፡፡ ባይኾን እስቲ ከሰሙኝ ልምከራቸው በማለት በጥያቄ መልክ “ይህ ዘመን ጥሩ እንዳልኾነ ታውቃላችሁ አይደል? ” ማለት፡፡

“በትክክል እንጂ “HIV/AIDS ወጣቱን እየቀጨው ይገኛል” የሚለውን ስብከት ልትነግሪን አይደል? ” አለኝ አንዱ ተማሪ እጎኑ ከተቀመጠችው ተማሪ እንብርት በኩል የሰደደውን እጁን ለመሰብሰብ እየሞከረ፡፡

“እሺ ሌላው ኹሉ ይቅርና  HIV/AIDS በምን በምን እንደሚተላለፍ ታውቃላችሁ?” አልኩኝ እኔን እንኳን ባያፍሩና ባይፈሩ አጅሬን እንዲጠነቀቁ ልመክራቸው፡፡

ለካ ልጅቱ ተናዳ ኖሮ “እስከ ዛሬ ድረስ ” HIV/AIDS መተላለፉን የማውቀው በቴሌቪዥንና በሬዲዮ ነው፡፡ እሱም ስልችት ብሎኛል፡፡” አለችኛ! በዚህም መምህር የኾንኩበትን ቀን ብቻ ሳይኾን የተወለድኩበትንም ቀን ልረግም ፈልጌ ነበር፡፡ ግን ባልወለድና መምህር ባልኾን መቼ ይህንን ጉድ እሰማና ዐይ ነበር ብዬ ቻል!

መቼስ ምን አደርጋለሁ ቢቸግረኝ ሣቅ ብዬ ወደ እነሱ በመመልከት ሥነ-ልቦናቸውን ለመማረክ እየሞከርኩኝ “እሺ!” አኹን ወደ ዋናው ትምህርታችን እንመለስ!” አልኩኝ፡፡

ኾኖም ሣቅ ብዬ ወደ ተማሪዎቹ መመልከት ሳበዛ ነው መሰለኝ ከፊት ለፊት ብቻውን የተቀመጠው ደህና የሚመስል ልጅ “ይመችሽ! ክፍሉን እኮ ፍቅር በፍቅር አደረግሽው”  ብሎ በዓይኑ አይመታኝም! “ወከክ!” ነው ያልኩት ወከክ!፡፡ ከመደንገጥ ሌላ ምን አደርጋለሁ? እንዳው ድንግጥ ነው እንጂ ዝም ብሎ ድንግጥ!

ይኹንና እንደምንም ድንጋጤዬን በመቋቋም “ከቻልኩ እስቲ ልምከራቸው”  ብዬ “አረ ተዉ እባካችሁ የድሮ ተማሪ እኮ እንዲህ አልነበረም፡፡ መምህሩን ያከብራል፡፡ ነውርም አይሠራም፡፡” ማለት፡- ታሪክ ልጠቅስ ፈልጌ፡፡

“አዬ!” አለኝ የዘንዶ ምስል በዩኒፎርሙ ላይ የሣለው “ድሮ ባህዮቹ ዘመን ነው? በዚያን ጊዜ ‹ተማሪ ለመምህሩ ባሪያው ነበር› ሲሉ ሰምተናል፡፡ አኹን ዘመኑ ተቀይሯል፡፡ መምህሩ እንቢ ካለ ያው ነው፡፡” ብሎ ቀበቶው ውስጥ የሰካትን ሴንጢ አያሳየኝም! የምገባበት ጠፋኝ፡፡ ምን ላድርግ ክፍሉን ትቼ እንዳልወጣ ክፍለ ጊዜው ገና አላለቀም፡፡ ፍርሃቴ  በጥፍ ቢጨምርም ችዬ ዝም!

“ቲቸር ምነው ፊትሽ ከቾኩ ጋር ተመሳሰለ? ” አለኝ ሰንጢ ከያዘው ልጅ ጎን የ2PAC ቲሸርትን ለብሶ የተቀመጠው ልጅ ፊቴ ሲነጣ አይቶ ፍርሃቴን አውቆብኝ ነው መሰል፡፡

ሱሪው ላይ የጊንጥ ምስል የሳለው ልጅ ደግሞ እግሮቹን አነባብሮ ከዘረጋበት ዴስክ ላይ ሰበሰበና “ይህ ዴስክ እንኳን ሲመቱን ይናገራል አንቺን ምን ይዘጋሻል?” ብሎኝ ሲነሳ ተደወለ፡፡ ልጁም ወደ ውጭ ወጣ፡፡ ሌሎችም ተከትለውት ሲወጡ ገርሞኝ፡- ‹አዬ! የመምህር ያለበት አበሳ› አልኩኝ፡፡

“አዬ! የመምህር ያለበት አበሳ

ሆ!ሆ!

ይቅር አይነሳ ይቅር አይነሳ

ሆ!ሆ!

ይቅር አይነሳ ይቅር አይነሳ

ሆ!ሆ!… ”

እያሉ ዳንስና ጭፈራውን አቀለጡት፡፡

መቼስ ምን አደርጋለሁ ቀስ ብዬ ሽልክ ብዬ ወጣኋ!!!

 
Leave a comment

Posted by on February 23, 2012 in ዐጫጭር መጣጥፎች

 
 
%d bloggers like this: