RSS

መኑ ውእቱ ዘፍልሱፍ- ፈላስፋ ማን ነው?

19 Oct

(በካሣሁን ዓለሙ)

‹ፍልስፍናን እማራለሁ› ብዬ ት/ቤት ብገባ፣ መምህሩ ‹ፍልስፍና ምንድን ናት?› ብሎ መልሶ እኔኑ ጠየቀኝ፤ ‹ካወቅኳትም ለምንስ ልማራት ሒሳብ ከፈልኩ?› አልኩኝ፤
‹ታዲያ ፍልስፍናን በገንዘብ ልተገዛ ነው እንዴ የመጣኸው?› ብሎ አፈጠጠብኝ፡፡
‹አይ! ገና ለማወቅ ነው የመጣሁት› አልኩት፡፡
በክፍል ውስጥ አብረን ከነበርነው ተማሪዎች መካከልም አንዱ ቀለብላባ ተማሪ ‹ፈላስፋ ማን ነው?› የሚል ጥያቄ አንሥቶ ገላገለኝ፡፡
መምህሩም ‹ፈላስፋ ምን እንደኾነ ንገረኝና የፍልስፍናን ምንነት አስረዳሃለሁ፤ ይባላል› አለን፡፡ ወይ ጣጣ ማብዛት! ‹ከየትኛው ነው የሚጀመር? ፍልስፍናን ከሚያወቀው ሰው ወይስ ከፍልስፍና ምንነት? ማንም ይፈላሰፋት ፍልስፍናን ካወቅናት አይበቃንም እንዴ? ደግሞስ ‹የፈላስፋን ምንነት ንገረኝ› ማለት ማንነቱን ከማወቅ ያነሰ፣ አሳቢውን ሰው ወደ ቁስነት የቀየረ አነጋገር አይኾንም?› የሚል ሐሳብ መጣብኝ፡፡ አላስችልም ስላለኝ ‹የፈላስፋው ማንነት ለምን እንደ ቁስ ተቆጥሮ በምንነት ይገለጻል?› አልኩት ለመምህሩ!
እሱም ጥያቄውን ወደ እኔ በማዞር ‹ሐሳቢ ሰው ምንነት የለውም ልትል ነው?› ብሎ አፋጠጠኝ፡፡
‹አይ! በቁስነቱ እየተከራከርን ጊዜ ከምናባክን በማንነቱ ተወያይተን የፍልስፍናን ምንነት ብንረዳ ይሻላል ብዬ ነው› አልኩት፡፡
እሱም በማስጠንቀቅ መልክ የዘመኑን አባባል ተጠቅሞ ‹ሲጀምር ጊዜ ከሌለህ ፍልስፍና ጋር አትድረስ፤ ሲቀጥል በፍልስፍና ትምህርት የማትስማማበትም ነገር ቢኾን ይነሳል፤ ሲቀጣጠል የፈላስፋውን ምንነት ሳታወቅ እንዴት ከማንነቱ ላይ ደረስክ? ምንነት የለውም ልትል ነው ወይስ በምንነቱ ላይ ጥያቄ አይነሳም፤ ታውቆ አልቋል ለማለት ፈልገህ ነው? ሲጧጧፍ በምንነትና በማንነት መካከል ያለው ልዩነት ገብቶሃል? ከገባህ አስረዳን፤ ካልገባህ ለማወቅ ጠይቅ እንጂ ሳታውቅ ለጥያቄው ያልተመለሰ መደምደሚያ አትስጥ!› እያለ ወረደብኝ፡፡
በመሃል ግን ቀድሞ ጥያቄ ያነሣው ልጅ ገብቶ ገላገለኝ፤ ‹እኔ ጥያቄውን ያነሣሁት ፈላስፋ ልንለው የምንችለው ሰው ከሌሎች ሰዎች መካከል ምን ዓይነት ዕውቀት፣ አኗኗር እና ስብዕና ያለው ነው?› ለማለት እንጂ ስለምንነቱም አንስተን እንድንከራከር አልነበረም፤ ምክንያቱም ‹ስለ ፋላስፋ ምንነት› የምናነሣ ከኾነ ስለ ሰው ልጅ ምንነት ቀድመን ማንሳት ይገባናል እንጂ ‹ፈላስፋ!› ስለምንለው ሐሳቢ የማንነቱ መለያ ብቻ መኾን አይኖርብትም፤ ክርክራችን በዚህ መልክ ከኾነም ስለፍልስፍና ምንነት ሳይኾን የምንጋገረው ስለሰው ልጅ ተፈጥሮ ሊኾን ነው፤ ይህም ከሐሳባችን ክበብ ውጭ ያለ ክርክር ያደርግብናል› አለናም ‹ፈላስፋ የምንለው ፍልስፍናን ያወቀውን ነው ወይስ ለማወቅ የሚጥረውን ሰው?› የሚል መንታ ጥያቄ አስከተለ፡፡
ጥያቄዋ ለመምህራችንም የተመቸችው ትመስላለች፤ ‹እስቲ ጥያቄህን በደንብ አብራራው› ብሎ ዕድሉን ሰጠው፡፡
ቀጠለ ተማሪው ‹‹ፈላስፋ የምንለው ፍልስፍናን የሚያውቅ ከኾነ የፍልስፍና ምንነት በፈላስፎች ታውቋል፤ የማትታወቀው መፈላሰፍ በማይችሉት ወይም ባልተፈላሰፉ ሰዎች ነው ማለት ይኾናል፤ ይህ ደግሞ ‹ፍልስፍና ጥበብን ማፍቀር ወይም መሻት ነው› ከሚለው ትርጉም ጋር አይስማማም፤ ፈላስፋ ከተባለ በኋላ ምን ዓይነት ጥበብን ለማወቅ ይፈልጋል? አይ! ፈላስፋ የሚባለው ፍልስፍናን ለማወቅ የሚጥርና የሚተጋ ነው ከተባለ ደግሞ የፍልስፍና ምንነት ገና አልታወቀም ማለት ይኾናል፤ ይህ ከኾነም ‹ፍልስፍና ማለት እንደዚህ ነው› በማለት መተርጎም አንችልም፤ ገና ምንነቷ በሐሳቢዎቿ መች ታወቀና!›፡፡
መምህሩ ተማሪውን ትኩር ብሎ እየተመለከተው ‹ፈላስፋ ማለት አንተ ነህ!› አለዋ!
ተማሪውም ጥያቄውን አስከተለ ‹በየትኛው አፈራረጅ!›
‹በጥያቄህ!›
‹ፈላስፋ ማለት ጠያቂ ማለት ነው?›
‹በትክክል! ግን ጥያቄዎቹ መሠረታዊና አመክንዮአዊ መኾን አለባቸው› ሲለው ተማሪው የዋዛ አልነበረምና!
‹መሠረታዊ ጥያቄን መጠየቅ የሚያበዛ ሕፃን ልጅ ነው፤ ስለዚህ ‹ፈላስፋ ስትል እንደሕፃን የኾነ› ማለት ይመስልብሃል› አለው፤ ‹ሕፃን ካልኾናችሁ መንግሥተ ሰማያትን አትወርሷትም ሚለውን የወንጌል ሐሳብ ወደ ፍልስፍና ጎትቶ ያመጣው ይመስላል፡፡
መምህሩም ‹የሕፃናት ጥያቄ ተራ ነገሮችን ለማወቅ የሚያነሱትና እንዳመጣላቸው የሚጠይቁት ተጠየቃዊነትን የማይጠብቅ ነው› አለው፡፡
‹አልስማማም ሕፃናት የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ተራ ይመስላሉ እንጂ በጣም ጥልቅ ናቸው፤ ለዚህም የራሴን ልጅ እንደምሳሌ ማንሳት እችላለሁ፡፡› በማለት ቀጠለ፡፡
‹አንድ የሦሰት ዓመት ልጅ አለኝ፤ ቤት ስገባ ጀምሮ በጥያቄ ያፋጥጠኛል፤ ለምሳሌ ትላንትና ማታ የእንግሊዘኛ ፊልም እየተለመከትን ‹ምንድን ነው የሚለው?› አለኝ፡፡
እኔም ‹እንግሊዘኛ ነው የተናገረው› አልኩት፡፡
‹እንግሊዘኛ ምንድን ነው?›
‹ቋንቋ!›
‹ቋንቋ ምንድነው?›
‹ሰዎች አንዱ ከሌላው ጋር በመነጋገር የሚግባቡበት›
‹ተግባብተውስ?›
‹ይጠቀማሏ!› ጥያቄው ማቆሚያ ስለመይኖረው፤ ‹በቃ! ጥያቄ አታብዛ!›
‹እሽ!› አለና ቀጠለ፤ ‹እኛ የምናወራው ምንድን ነው?›
፣አማርኛ!›
አማርኛ ምንድን ነው?›
‹ቋንቋ!›
‹እንቢ! እንግሊዘኛ ቋንቋ ነው ብለኸኝ አልነበር?›
‹አዎ! ብየኸለሁ፤ ኹለቱም እንግሊዘኛም፣ አማርኛም ቋንቋ ናቸው፡፡›
‹ቋንቋ ማለት እንግሊዘኛና አማርኛ ማለት ነው?›
‹አዎ! ግን ሌሎችም ቋንቋዎች አሉ፡፡›
‹ሌላ ምን?›
‹ብዙ ናቸው፡፡›
‹በቃ ቋንቋ ማለት ብዙ!! ማለት ነው፡፡›
‹አይ! ቋንቋ ማለት መግባቢያ ነው፤ ግን ብዙ ዓይነት አለው፡፡›
‹ለምን እውነተኛውን አትነግረኝም? መጀመሪያ እንግሊዘኛ ቋንቋ ነው አልከኝ፤ ከዚያም አማርኛም ቋንቋ ነው አልከኝ፤ ከዚያም ቋንቋ ብዙ ነው አልከኝ፤ ከዚያም መግባቢያ ነው አልከኝ፤ ለምን ታታልለኛለህ? እንቢ በቃ እውነተኑን ንገረኝ፡፡›
‹አላታለልኩህም! በቃ ጥያቄ አታብዛ ብየሃለሁ› ብዬ ተቆጣሁት
‹አትዋሸኛ!› ብሎ ተነጫነጨና እንደገና ‹አሁን ግን ጥያቄ ቀንሻላሁ አይደል?› ብሎ ሌላ ጥያቄ ቀጠለ››
ይህን ምሳሌ ከጠቀሰ በኋላም ‹አሁን ይህ ጥያቄ መሠረታዊ የማይኾነው በምኑ ነው? ተጠየቃዊስ አይደለም? ለምሳሌ ለመጀመሪያው ጥያቄ የእኔ መልስ የተሳሳተ ነበረ እንጂ እሱ የጠየቀው በፊልሙ ውስጥ የሰማው ምን ማለት እንደኾነ እንድነግረው ነው፤ ስለ ቋንቋም አትዋሸኝ ብሎ የተነጫነጨውም ‹አታጣርስ› ማለቱ ነው› ብሎ ተከራከረ፤ ክርክሩን ሲያዩት ከሕፃን ልጁ ጥያቄ መጠየቅን የተማረና የለመደበት ይመስላል፡፡
መምህሩም ‹አልፎ አልፎ ያጋጥማል› በማለት ክርክሩን መዝጋት የፈለገ መሰለ፡፡
እኔም አንድ ጓደኛዬ ያጫወተኝ ትዝ አለኝና ከቀረበው ክርክር ጋር በማገናኘት ፈገግ አልኩኝ፡፡ ይህንን ያጫወተኝ ጓደኛዬ የእሱ ጓደኛ የሕግ ሰው ነው! አነጋገሩ ኹሉ ‹ይኸ ከኾነ ይኸ› ዓይነት ተጠየቃዊነትን የተከተለ ነው፤ እሱም አንድ የአምስት ዓመት ልጅ አለው፤ እናቱ ልታስጠናው ስትሞክር አይግባቡም፤ እንደ አባቱ ‹ይኸ ከኾነ ይኸ› ዓይነት ጥያቄውን እያሽጎደጎደ ያስጨንቃታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ቀን ሕይወት ያላቸውና ሕይወት የሌላቸው ነገሮችን ልታስረዳው ስትሞክር፤ ‹ሕይወት ያላቸው ነገሮች ይወለዳሉ፣ ያድጋሉ፣ ይራባሉ፣ አንዳንዶቹም ይንቀሳቀሳሉ፤ ከዚያም ይሞታሉ፤ ሕይወት የሌላቸው ነገሮች ግን አይዋለዱም፣ አያድጉም፤ መንቀሳቀስ አይችሉም፤ አይሞቱም…› እያለች ለማብራራት ትሞክራለች፡፡
‹እሽ! እንደዚያ ከኾነ መኪና ሕይወት አለው ማለት ነው?› ብሎ ጠየቃት፡፡
‹የለውም!› ስትለው ከልጁ ጋር ተጣሉ ‹ሕይወት ያላቸው ነገሮች ይንቀሳቀሳሉ ብለሽኛል፤ መኪና ደግሞ ይንቀሳቀሳል› አላት፤ ሊግባቡ አልቻሉም፡፡ ከዚያም እናቱ ‹ኹለተኛ አሳይኝ እንዳትለኝ፤ አባትህን ጠይቅ፤ ያበላሸህ እሱው ስለኾነ ራሱ ይወጣው› አለችው፡፡ ‹ታዲያ ሳታውቂ ለምን ልታስረጂኝ ትፈልጊያለሽ ኤክስ ልታስገቢብኝ ነው› ብሎ ልጁም ተቆጣ ብሎ አጫውቶኛል፡፡
ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የኾነ ታሪክ በአውራምባ ማኅበረሰብ መሥራች በዙምራም የልጅነት ታሪክ እናገኛለን፡፡ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ‹ፍልስፍና ፪› በሚል መጽሐፉ ‹በሕይወት፣ በሰው ልጆችና በእግዚአብሔር መሃከል ያሉ ጥያቄዎችን ማንሳት የጀመርከው መቼ ነው?› ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ የሰጠውን መልስ በምሳሌነት ወስዶ መመልከት ዙምራ በሕፃንነቱ የነበረውን የአስተውሎት ምጥቀት ለመገምገም ይረዳል፡፡ ዙምራ ለተጠየቀው ጥያቄ እንዲህ ነበር የመለሰው፡-
‹‹እኔ ራሴ አላውቀውም፡፡ ራሴን ሳውቅ ጀምሮ እጠይቃለሁ፡፡ መጠየቄ ተቋርጦም አያውቅ፡፡ እናቴ ስትናገር ‹ስለ ሰው ልጆች ማኅበራዊ ሕይወት መጠየቅ የጀመረው በአራት ዓመቱ ነው፤ ስለ እምነት የጠየቀው ደግሞ በሁለት ዓመቱ ነው› ትላለች፡፡ እንግዲህ ከእናቴ የሰማሁትን ነው የምናገር፡፡ የእኔ ወላጆች እምነታቻው እስልምና ነው፡፡ ክርስቲያን ዘመዶች አሏቸው፡፡ አንድ መንደር ነው የተቀመጡ፡፡ ቡና በአንድ ይጠጣሉ፤ ሥራ በወንፈል አብረው ይሠራሉ፡፡ እኛ ልጆቹም አብረን እንጫወታለን፡፡ አሁንም እናቴ ስትናገር ‹ተወልዶ በስድስት ወሩ ቆሞ ሄዷል፤ በሁለት ዓመቱ ደግሞ ስለ እምነት መጠየቅ ጀምሯል› ትላለች፡፡ ልለይበት የቻልኩትን ልናገርና በሁለት ዓመቴ ክርስቲያን ዘመዶቼ ቤት ሄጃለሁ፡፡ ተዚያ ስሄድ ወላጆቻቸው የሉም፡፡ ልጆቹ ምግብ ይበላሉ፡፡ ምግቡ የሥጋ ምግብ ነው፡፡ እኔን ሙስሊም ነህ ብለውኛል፡፡ እነሱ ክርስቲያን ናቸው ብለዋል፡፡ ብለዋል ነው የምል፡፡ ወላጆቻቸው ቢኖሩ የሥጋ ምግብ ስለሆነ፤ አይሰጡኝም፡፡ ልጆቹ ያው እንደኔው ናቸውና ሰጡኝ፡፡ ምግቡ ስለጣመኝ ግጥም አድርጌ በልቼ ትራፊዬን ተቤቴ! እናቴ ሥጋውን ስታይ፡
‹እሱን ሥጋ ተምን አገኘኸው?› ትለኛለች፡፡
‹እነ አተዋ ልጆቹ ሰጥተውኝ ነው› እላለሁ እንደኔው ይጥማታል ብዬ፡፡
‹የክርስቲያን ሥጋ በላህ?› ትልና ትቆጣለች፡፡ ያ ብቻ አልበቃትም፡፡ ሥጋዋ እየጣመችኝ በእጇም እንዳትይዘው ተጠይፋ በእንጨት ይዛ አውጥታ ትጥለዋለች፡፡ ዓይኔ ሥጋዋ ላይ ቀርቷል፡፡ የክርስቲያን ሥጋ ነክቼ ዕቃ እንዳልነካበት እጄን ታጥባለች፡፡ እየታጠብኩ ሥጋዬ መውደቁ ስለቆጨኝ፤
‹እማዬ ሥጋዬን የቀማሽኝ ለምን ነው?› ብዬ ጠየቅኳት፡፡ (ያው እንግዲህ እሷ የነገረችኝን ነው የምነግርህ)
‹የክርስቲያን ሥጋ ሆኖ ነው› ትላለች፡፡
‹ከክርስቲያኖች ቤት ስለታረደ ነውዪ ሥጋውማ የበግ ነው› አልኳት፡፡
‹ሥጋው የክርስቲያን ነው›
‹ክርስቲያን ማለት ምንድነው?›
‹ሰው› ትላለች፡፡
‹ዛዲያ እኛ ምንድነን ሰው አደለንም ማለት ነው?›
‹እኛማ ሙስሊሞች ነን›
‹ሙስሊም ሰው አይደለም?›
‹ነው እንጂ፡፡ ሰው ነው›
አሁን ሁላችንም ሰው ሁነናል ማለት ነው፡፡
‹ዛዲያ እኔስ ሰው የበላውን አይደለ የበላሁ? ለምን ሥጋዬን ቀማሽኝ?› አልኳት፡፡
‹አንተ! የክርስቲያን ሥጋ አይበላም› ትላለች ቆጣ ብላ፡፡
ሃሳቤን ቀየርኩና እንደገና ጠየቅኳት፡፡
‹ክርስቲያን የምን ሥጋ ነው የሚበላ?›
‹የከብት›
‹ሙስሊምስ የምን ሥጋ ነው የሚበላ?›
‹የከብት›
‹ሁላችንም እኩል ሰው ተሆንን፤ ሁላችንም የከብት ሥጋ ተበላን ዛዲያ ለምን ቀማሽኝ› እናቴ መልስ የላትም፡፡
በስንት ዓመቴ እንደሆነ ባላውቅም በሰው ልጅ ፍጥረት ላይ ሌላም ጥያቄ አንስቻለሁ፡፡
‹መጀመሪያ ክርስቲያን ሲፈጠር ተምን ተፈጠረ?›
‹ተአዳምና ተሄዋን›
‹ሙስሊምስ?›
‹ተአደምና ተሃዋ› ይሉኛል፡፡
‹ሁለት ሴቶችን ሁለት ወንዶች ናቸው ማለት ነው መጀመሪያ ሰው ሲፈጠር የተፈጠሩ?›
‹አይደለም፡፡ የሀገር ቋንቋ ነው ባጠራር አራት ቢመስሉም ሁለት ናቸው› አሉኝ፡፡
ክርስቲያኖች እግዜር፤ ሙስሊሞች ደሞ አላህ ሲሉ እሰማለሁ፡፡
‹አላህና እግዚአብሔር ሆነው እየተማከሩ በጋራ ይቺን ዓለምና እኛን የፈጠሩ?› እላለሁ፡፡
‹ፈጣሪማ አንድ ነው›
‹እንግዳው ስሙ ለምን ሁለት ሆነ?›
‹እሱ ያገር ቋንቋ ነው እንጂ ፈጣሪ አንድ ነው› ይላሉ፡፡ ሁላቸወም በአንድነቱ ይስማማሉ፤ የማይስማሙት በስሙ ነው፡፡
ፈጣሪ አንድ ተሆነ፤ እኛ ሁላችን የአዳምና ሄዋን ዝርያዎች ተሆንን እምነት የሚገለጠው በምንድነው? እምነት ጥሩ ማሰብ፤ ጥሩ መሥራት ነው፡፡ እኛ የምናምን ፈጣሪ አንድ ነው፤ እንደ ዳቦ አይቆረስም ብለን ነው፡፡ ሰዎች ግን ስሙን እየሸነሸኑት እምነቶች ተሺህ በላይ ደርሰዋል፡፡››
ፈላስፋ ማለት ተጠየቃዊ ጥያቄዎችን የሚያነሣ ከኾነ በዚህ ጥያቄው ዙምራ ገና በሕፃንነቱ ፈላስፋ ነበር ማለት ነው፤ ይህም ‹ፈላስፋነት ከሕፃንነት የሚጀምር ነው› ያስብላል፡፡
መምህሬም የፈላስፋን ማንነት በራሱ ትርጓሜ ተነሥቶና ወደ ሌላ ትርጉም ቀይሮ ለማብራራት ሞከረ፡፡ ‹ፈላስፋ ለመኾን ወሳኙ ነገር ጊዜ ነው፤ ጊዜ የሌለው ሰው ተረጋግቶ ለማሰብ አይችልም፤ በእርጋታ ኾኖ ያላሰላሰለ ደግሞ የጥበብ ፍቅር ሊገባውና ሊመረምራት አይችልም፡፡ በዓለማችን የምታውቋቸው አብዛኞቹ ፈላስፎች የማሰቢያ ጊዜ የነበራቸው ናቸው› አለን፡፡
አሁንም ያ የቅድሙ ተማሪ በጥያቄ አፋጠጠው ‹ይህማ ከኾነ ፈላስፋ ማለት ሥራ ፈት ማለት ሊኾን ነው?› ሲለው ‹ልትለው ትችላለህ! ግን ማሰብ ሥራ አይደለም እንዴ?› አለው መምህሩ፡፡
‹ወደ ተግባር ያልተቀየረ ሐሳብ ምን ጥቅም ሊያስገኝ?›
‹ማሰብ አንድ ነገር ነው፤ ወደ ተግባር ቀይሮ መጠቀም ደግሞ ኹለተኛ ነገር ይኾናል፤ መጀመሪያውኑ ተረጋግቶ በጥልቀት ካላሰበ ግን ስህተት ሊሠራ ይችላል፤ ስለዚህ ነው ፈላስፋ ማለት ጊዜ ኖሮት በዚያን ጊዜ ውስጥ መሠረታዊ ጥያቄዎችን በማንሳት የሚያሰላስል፣ ፍሬውን ከገለባ ለይቶ ለማወቅ የሚጥር የሚኾነው› አለና ለመጠቅለል ሞከረ መምህሩ፤ ግን አልቻለም፡፡
‹ስለዚህ ፈላስፋ ባለ ትርፍ ጊዜ ሰው ነው?›
‹አዎ! ምን? ለምን? እንዴት?… የሚሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ አስተሳሰቡን የሚያበጥረው ጊዜ ሲኖረው ነው›
‹ጊዜ ሊኖረው የሚችለው ደግሞ ሀብታም ከኾነ ወይም በሌሎች ትካሻ ላይ በዕርዳታ የሚኖር ከኾነ ብቻ ነው፤ ያለበለዚያ ለመኖር የሚያስፈልጉትን ነገሮች ለማሟላት ሲል በሥራ መወጠሩ ግድ ነው? በሌላ በኩል ደግሞ ችግር ብልሃትን ይፈጥራል እንጂ ትርፍ ጊዜ አስተውሎትን አይጨምርም፡፡› አለ ተማሪው፡፡
‹ያልከው ሐሳብ ተወሰነ ደረጃ ልክ ነው፤ ግን መረዳት ያለብህ በምንም ምክንያት ወይም መንገድ ይኹን ለመፈላሰፍ ተረጋግቶ ማሰብ ያስፈልገዋል፤ ተረጋግቶ ለማሰብና ለመከራከር ደግሞ ጊዜ ማግኘት ግድ ነው፤ ስለኾነም አንድ ሰው ፈላስፋ ለመኾን ጊዜ ሊኖረው ግድ ነው፡፡ ጊዜ የተረፈው ሰው ኹሉ ግን ፈላስፋ መኾን ይችላል ማለት አይደለም፡፡›
‹በሌላ በኩል አዙረን ብናየው እኮ ፈላስፋ ማለት ሥራ ፈቶ በሐሳብ ሲናውዝ የሚኖር ሰው ማለት ሊኾን ነው፤ በሐሳብ ብቻ ሥራ ፈቶ የሚኖር ከኾነ ደግሞ ፍልስፍናም የሥራ ፈቶች ጊዜ ማሳለፊያ ወይም የሰነፎች ምክንያት ልትኾን ነው፤ ይህንን ዓይነት የሥንፍና ተግባር መውደድ ደግሞ ትክክል አይመስለኝም፡፡› አለ ተከራካሪው ተማሪ፡፡
‹ይህ እንኳ ጫፍ ይዘህ ለመሟገት ካልኾነ መስተቀር ትርፉ መለጠጥ እንጂ መረዳት አይመስልም› አለው መምህሩ፤ በዚህ አስተያየት ኹሉም ተማሪ የተስማማ መስሎ ዝም አለ፡፡
ይሁንና አንድ ሌላ ተማሪ ጭራሽ ‹ፈላስፋ ማለት አስተሳሰቡ ከማኅበረሰቡ ጋር አብሮ የማይገጥም ዕብድ ነው› አለ፡፡
መምህሩም ‹ታዲያ ለምን እኛ አላበድንም?› የሚል ጥያቄ ጠየቀው፡፡
‹የዕብድ አድናቂ ከመቼ ወዲህ ነው የሚያብደው፤ እናንተ እኮ የእነሱ አድናቂና ሐዋሪያ ናችሁ እንጂ ‹ፈላስፋ› ለመባል የደረሳችሁ አይደላችሁም› ብሎ መለሰ ተማሪው፡፡
‹እሽ! ይሁንልህ እንበልና! ፈላስፋ ዕብድ የሚባለው ፍልስፍና ስላወቀ ነው ወይስ ያበደ ሁሉ ፈላስፋ ነው?›
‹ያበደ ኹሉማ እንዴት ፈላስፋ ይኾናል? የፍልስፍና ዕብደት ከማኅበረሰቡ ተገልሎ በራስ ዓለም መኖር ስለኾነ አስተሳሰቡን ከማኅበረሰቡ ወጣ አድርጎ ለማየት የሚሞክር የፍልስፍና ዐዋቂ ነው እንጂ!›
‹ስለዚህ ፈላስፋን የሚያሳብደው ፍልስፍና ማወቁ ነው ማለትህ ነው?›
‹ይመስለኛል!›
‹እና አንተ መቀወስ ፈልገህ ነው ፍልስፍና ልትማር የመጣኸው?›
‹እኔማ ለምን እቀውሳለሁ፤ ራሴን ጠብቄ እማራለሁ እንጂ! እኔ የምማረው ፍልስፍናን ለማወቅ እንጂ ፈላስፋ ለመኾን አይደለም፡፡›
‹ፈላስፋ የምትለው ፍልስፍናን የማያውቅ ሰው ነው እንዴ?›
‹ፍልስፍናን ሳያውቅማ እንዴት ፈላስፋ ሊባል ይችላል?›
‹ያ ከኾነማ አንተም ፈላስፋ ለመኾን ትማራለህ ማለት ነው፤ ያለበለዚያ እንዳትቀውስ አሁንኑ ፍልስፍና መማርህን ማቆም አለብህ?›
‹እንደዚያማ አይኾንም! ለምሳሌ አንተ የፍልስፍና መምህር ነህ፤ ስለዚህ ፍልስፍናን ታውቃለህ ማለት ነው፤ መቼም ሳታውቅ አታስተምረንም፤ እና አሁን አንተ ‹ፈላስፋ› ልትባል ነው?›
‹ለምን ልባል አልችልም?›
‹ፍልስፍናን ተምሮ በማወቅና በማስተማር ‹ፈላስፋ› መኾን ከተቻለማ፤ የፍልስፍናን ትምህርት የሚያስተምረው መምህር ኹል ‹ፈላስፋ› ሊኾን ነው?›
‹ለምን አይኾንም?›
‹ይህ ከኾነማ የፈላስፋ አድናቂ ኹሉ ራሱ ፈላስፋ ነው እያልከኝ ነው?›
‹የፈላስፋ አድናቂ ኾኖ ፈላስፋ መኾን አይቻልም ልትለኝ ነው?›
የመምህሩና የተማሪው ጭቅጭቅ ሊያቆም ስላልቻለ እኔ ነገሩን ለማስቀየስ ሞከርኩኝ ‹የእሱ (የተማሪው) ክርክር ‹ፈላስፋ› የሚባለው ፍልስፍናን ከማኅበረሰቡ ወግና ልማድ ወጣ አድርጎ የሚያስተውል ሰው ነው ለማለት ፈልጎ መሰለኝ!› አልኩኝ፡፡
‹ከማኅበረሰቡ ወጣ ብሎ ማየት ፈላስፋ ያስብላል እንዴ?› በማለት ጥያቄውን ወደ እኔ አዞረው፤ እኔም የፈለግሁት ይህንን ነበር፡፡
‹ከዚያ ወጣ ያለ አስተሳሰብና አስተውሎት ከሌለውማ ምኑን ፈላስፋ ኾነው?›
‹ያንኑ የማኅበረሰቡን ወግና ልማድ በማሻሻልና በማስተካከል ቢቀርፀውስ ፈላስፋነትን ማግኘት አይችልም?›
‹ለምን አይችልም ይችላል እንጂ! እኔም እኮ የምለው ይኸንን ነው፤ እነሱ ተቀበሉትም አልተቀበሉትም ሕዝቦች የተሻለ የአኗኗር ዘይቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሐሳብን የሚያፈልቅና የሚያቀርብ ብልህ ሰውን ነው ፈላስፋ ማለት ያለብን፡፡›
‹በአንተ አስተያየት ፈላስፋ ማለት ‹ብልህ ሰው› ማለት ሊኾን ነው፡፡›
‹በተወሰነ ደረጃ ትክክል ነው›
‹ይህ ከኾነም ብልሆች ኹሉ ፋላስፎች ሊኾኑ ነው፡፡›
‹ኹሉም ላይኾኑ ይችላሉ፤ ግን ‹ፈላስፋ› ለመባል ብልህ መኾን አስፈላጊ ይመስለኛ፡፡›
‹እና ቅድም ‹ዕብድ ነው› እያለ የተከራከረው ይህንን ለማለት ፈልጎ ነው የምትለኝ፡፡›
‹ይመስለኛል!›
‹ይመስለኛል! ‹ብልህ ማለት ዕብድ ማለት ይመስልሃል!››
‹እንደዚያ ማለቴ አይደለም› አልኩኝ፤ ‹ሳላስበው በየት በየት ዞሮ መጣብኝ› የሚል ሐሳብ እያሰብኩኝ!
‹ያልከውን ልትክድ ነው እንዴ? የተነሳኸው የእሱን ክርክር ለማገዝ አይደለም እንዴ?›
‹አዎ!› አልኩና ዝም አልኩ፤ ከዚህ በኋላም መሄድ አልቻልኩም፡፡ መምህሩ ግን መጨቃጨቅ የተመቸው ይመስላል በጣም ደስተኛ ነበር፡፡ እና! ፈላስፋ ማን ነው? እንግዲህ ፍልስፍናን ስንረዳ በማን ሊትታሰብ እንደምትችልና ማንስ ወዳጅ ሊኾናት እንደሚችል ማወቅ እንችል ይኾናል፡፡ ከቻልን!

Advertisements
 

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: