RSS

Monthly Archives: October 2013

ነገደ ኢትዮጵያ

ይህ ጽሑፍ መሪ ራስ አማን በላይ ‹የጥንቷ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ› በሚል ርዕስ ከመጽሐፈ ሱባኤ ተረጎምኩት ብለው በ1985 ዓ.ም. ካሳተሙት መጽሐፍ ከምዕራፍ ሦስት በሙሉ የተወሰደ ነው፡፡ ጽሑፍ እሳቸው እንዳዘጋጁት ነው እንጂ የተጨመረበት ወይም ኤዲት የተደረገ ነገር የለውም፡፡ መጽሐፉ በያዛቸው መረጃዎችም ሆነ በምንጩ በተለምዶ ከሚታወቀው የታሪክ መጽሐፎች ይለያል፤ ስለ መጽሐፉ ይዘት፣ ምንጭና አስፈላጊነት ብዙ ማለት ቢቻልም፤ መጽሐፉ ብዙ ሰዎች በቀላሉ አግኝተውት ያላለነበቡት በመሆኑ አንዱን ምዕራፍ ብቻ እንደነበረ እንደማሳያ ማቅረብ የተሻለ መስሎ ታይቶኛል፡፡ ለማንኛውም ስለ መጽሐፉ ሁኔታ ለማወቅ በመግቢያውና በመጽሐፉ ጀርባ ከጻፉት ላይ ቀንጭቦ ማየት ጠቀሜታ ይኖረዋልና እነሆ!
(ከመግቢያው የተወሰደ)
‹‹ይሄን የጥንቷ የኢትዮጵያ ታሪክ ሱዳን አጥባራ በነበርኩበት ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጽሐፈ ሲራክ እያነበብኩ ስለ ድንጋይ ጥበብና ስለሌላም ስከታተል እንደቆየሁ ጀቢል ኩራርና ጀቢል ኦባ ወደሚባለው ሃገር ሄጄ የጥንት ቤተክርስቲያን ፍርስራሽና የክርስቲያን መቃብር አገኘሁ፤ ከዚያም ጀበል ኦባ ለአንድ ሰባት ወር እንደተቀመጥኩ አንድ ሽማግሌ ሰው እንዲህ ካለ ዋሻ ውስጥ የክርስቲያኖች መጽሐፍ አለ ብለውኝ አብረን ሄድን፤ ብዙ በብራና የተጻፉና የተቀዳደዱ መጽሐፎች አገኘን፤ እንደገና ከሌላ ዋሻ ሄደን ስንቆፍር ብዙ ፅላቶችንና ቁርጥራጭ ካባዎችን፣ ቁመቱ ክንድ አንድ መቶ ስልሳ አራት ብራና የአክሱማይ ሲራክን መጽሐፍ፣ የሱባን ቋንቋና የሱባን ታሪክ የያዘ መጽሐፈ ሱባኤ፣ እንደዚሁም በጣም የረዳኝ ሁለት መቶ ብራና አራት መቶ ገጽ ያለው የኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ ዘግዱር ዘእንዳ ቤት በተፈለፈለ የድንጋይ ጉድጓድ ከተልባና ከአመድ ጋር ተቀብሮ ተገኘ፡፡
መጽሐፈ ሱባኤ ከአዳም እስከ ቀዳማዊ ምኒልክ መፀሐፈ አክማይ ሲራክ ከቀዳማዊ ምኒልክ እስከ ዮዲት መጽሐፈ ታሪክ ነገሥት ዘኢትዮጵያ በዘግዱር ዘአንደበት የተጻፈ ከዮዲት እስከ በካፋ ልጅ ዳግማዊ ኢያሱ ከዳግማዊ ኢያሱ ወዲህ እስከ ኃይለ ሥላሴ ማህፀወ ነገሥት ከመሪጌታ ጉባኤ ጎጃም ሊበን ውስጥ ከተገኘ መጽሐፍ በብዙ ችግርና ድካ ለማሳተም ወደ ኢትዮጵያ በ1966 ዓ.ም. ይዤው ገባሁ፡፡››
(ከመጽሐፉ ጀርባ የተቀነጨበ)
‹‹… በጊዜው የነገሥታትን ታሪክ ማሳትና ማወደስ አደገኛ ነበር፡፡ ሁኔታውም በጣም አሰጋኝ፤ እናም ብዙ ሺ ማይልስ ከኔ ጋር ለብዙ ዓመታት ተንከራተተ፡፡ አሁን ጊዜውና አጋጣሚው ፈቅዶ አቋርጦ ከሄደበት ከምድረ አሜሪካ በሀገሩ በኢትዮጵያ በወንድሞቼ ብርታት ለመታተም በቃ፡፡ በዚህ አጋጣሚ አፈር የተጫናቸው መጻሕፍትና ንዋየ ቅዱሳት ቀስ በቀስ እየወጡ እውነተኛ ታሪካችን እየታወቀ እንደሚሄድ የዘወትር ጸሎቴ ነው፡፡››

 

ምዕራፍ ሦስት፡- ነገደ ኢትዮጵያ

‹‹ኢያስጴድ-ኢ፡ የኢትዮጵያ ዘመነ መንግሥት
ስሙ፣ አልፋ አየን አማን ኤል ኢያስጴድ፤
ፊደሉ፡ /እ/፣ /አ/፣ /ኣ/፣ /ኤ/፣ /ኢ/
/ኢትኤል ማለት የአምላክ ሥጦታ ማለት ነው፡፡/
የክህነቱ ስም ኢትኤል የተባለው ኢትዮጵ የአበ መለክስ ናምሩድ የልጅ ልጅ ነው፡፡ ናምሩድ አዳማን ወለደ፤ አዳማ ራፌልብን ወለደ፤ ራፌልብ ኬናን ወለደ፤ ኬና ወይም ቄና ጌራራን ወለደ፤ ጌራራ ወይም ጌራ ሃሙራቢ የክህነት ስሙ መልከጼዴቅ የተባለው ታላቁ የሰላም ንጉሥና የአምላክ አገልጋይ በደብረሣሌም ኢትን ወለደ፤ ኢትም እንዳባቱ አምላኩን ወዳድና ለፈጣሪው ታዛዥ ተገዥ ስለነበረ ኢትኤል ተባለ፤ ኢትኤል ማለት የአምላክ ሥጦታ ማለት ነው፡፡
ኢትኤልም በአምላኩ መንፈስ እየተመራ ግዮን ወንዝ ወደሚፈስበት ምድር ሄዶ ተቀመጠ፤ ያንም ምድር ኢያስጵድያ የሚባለውን ድንጋይና ከጥራቱ የተነሣ የሚያንፀባርቀው ኢያስጵድ ክርስቶ ድንጋይ ክብር ዮጵ ድንጋይ የሚገኝበት ነው፡፡ ስለዚህ ዮጵ በሚባለው ወርቅና በእንቁ ድንጋይ ሃብታም ስለነበረ ኢትኤል መባሉ ቀርቶ ኢትዮጵ ተባለ፤ ሚስቱም ሲና መባሉዋ ቀርቶ እንቅዮጳግዮን ተብላለች በነገደ ዮቅጣን አግአዝያን የሚባሉት አቡሳውያን እንቆ እንቁጳግዮን የሚባለው ስም እንቆዮጳዝዮን ብለውታል፤ ይሄውም የአባይ ወርቅ ማለት ቀርቶ የፅዮን ወርቅ እንዲባል ብለው ነው፡፡
ኢትኤልም ግዮን ወንዙን ለወንዝ አጠራቅሞና ሰብስቦ እስከሚገናኝበት ያለውን ምድር ሁሉ በስሙ ኢትዮጵያ እንዲባል አድርጓል በግዮን ዳርቻ ሄዶ የልጅ ልጆቹ በሚነግሡበት ጊዜ በዚህ ድንጋይ ላይ ተቀምጠው ቅባአ መንግሥታቸውን እንዲቀቡና እንዲነግሡ ሲል ኤለንኤል ብሎ በክብር ለማሳሰቢያ ትልቅ የድንጋይ ዙፋን አስቀምጧል፡፡ ይህም ምድር ከሳሌም እስከ ግዮን ድረስ የኢትዮጵ ልጅ አዜብ ይገዛው ስለነበረ አዜብ ይባላል፡፡
አዜብ መልከዘቦ ንጉሥ በግራ ክፍል የሚገኘውን የግዮን ገባሪ ሰማያዊ ግዮን ወንዝ እስከሚፈልቅበት ምድር ድረስ ግዛቱን አስፋፍቶ ስለነበረ ያ ምድር እስከ አሁን አዜብ ወይም አዘቦ ይባላል፡፡ አዜብያ በሚለው ሃገር ውስጥ አብርሃም ሳይባል አብራም ብዙ ቀናት በእንግድነት ተቀምጦበት ነበር አብራም በዚሁ ወርቅና በብር ከብሮበት ነበር፤ ይህም ታሪክ በሴም ነገዶች ተጽፎ ይገኛል፡፡ አዜብ 132 ዓመት ገዝቶ የኢትዮጵያ ታላቅ ልጅ አቲባ ወርካዘቦ ንጉሥ በቀኝ በኩል ያለውን የግዮን ገባሪ ወንዞች የሚፈልቁበትን ሃገሮች እንዲገዛ አንግሦ ሰደደው፤ አቲባም በአባቱ በኢትዮጵ ሥር ሆኖ እስከ ታላቁ ባህር በሚገኙት ጎሣዎች ላይ በሱባ አቆጣጠር ሰባት ሱባኤ ገዝቷል፡፡
ካህኑ ኢትኤልም በኢትዮጵያ ምድር ሆኖ ምድሪቱን ከባረካትና ለልጆቹም የመገናኛ ዘዴ ጽፎ ከአስተማራቸውና ሥርዓተ መንግሥት ከአሳያቸው በኋላ ንጉሥ ነገሥት በተባለ በአሥራ አራት ሱባኤ (98 ዓመት ማለት ነው)በተወለደ በአንድ መቶ አምሣ አንድደ ዓመት አንቀላፋ፤መልከጼዴቅ ከአስፈለፈለውና ከአሠራው ዋሻ ውስጥ ወስደው አስቀመጡት፤ በኢትዮጵ መጨረሻ የግዛት ዘመን እረሃብ ነበረና እብራውያን ወደ ምስር የተሰደዱበት ዘመን ነው፡፡

ኢትዮጵያ የተባለው ኢትኤል በፋቱራ የተድኦልን ልጅ እንቁጳን አግብቶ አሥር ወንዶች ሦስት ሴቶች ወለደ፡፡ የወንዶቹ ስማቸው አቲባ፣ ቦኦር፣ ቢኦራ፣ ተምና፣ ኤቴር፣ አሻን፣ አክለብ፣ መሪሣ፣ ቴስቢ፣ ቶላ፣ አቤሜሌክ የተባለው አዜብ ናቸው፡፡ ሴቶች ደግሞ ሎዛ፣ ሚልካና ሱባ ናቸው፡፡ የአቲባና የመጨረሻው ልጅ የአዜብ ዘሮች ነገሥታት ናቸው፡፡ የቢኦር ዘሮች መናፍስት በመጥራት፣ የተምና፣ የኤቴር፣ የአሻን ዘሮች የተለያዩ ቅርጾች በመሥራት የሰው ልጆች የሚያገናኙበትን፣ የሃሣባቸውን የሚገልጹበት ምልክት ወይም ጠልሰም ታሪክ የሚያቆዩበትን ጽሕፈት የሚያቆዩ ፈላስፎች ናቸው፡፡ ይሔውም ለመጀመሪያ ጊዜ በአምላክ ስም ፊደል የቀረጸ፣ ለእያንዳንዱ ቃል ትርጓሜ አቅርቦ ያስተማራቸው አባታቸው ኢትኤል ነው፤ ከዚያ በፊት የትውልድ ታሪክ በቃል ሲነገር በልብ ሲጻፍ ቆየ እንጂ ሌላ ዘዴ አልነበራቸውም፤ የአክዚብና የመሪሣ ዘሮች ናቸው፤ የቴስቤ ዘሮች የአምላክ አገልጋዮች፣ ትንቢት ተናጋሪ፣ መጭውን በማወቅ የታወቁ ናቸው፡፡ ከነዚህ ዘር የተወለደው ታላቁ ነቢይ ቴሰቢያዊ ኤልያስ ነበር፡፡ የቶላ ዘሮች አንጠረኞች፣ ግመሹ ነገዴዎች ነበሩ፡፡
ቢአር አራምን ወለደ፤ አራም ናጊን ወለደ፤ ናጌ ሃጌን ወለደ፤ ሃጌም ሁለተኛውን ቢኦርን ወለደ፤ ቢኦር በለአምን ወለደ፤ በለአም ከምሥር ዕብራዉያን ሲወጡ በእሥራኤል ላይ በመንፈስ እየተመራ ትንቢት ተናገረ፤ የተናገረው ቃልም እንዲህ አለ ‹አየዋለሁ አሁን ግን አይደለም፤ እመለከተዋለሁ በቅርብ ግን አይደለም፤ ከያዕቆብ ኮከብ ይወጣል፤ በእሥራኤል በትር ይነሣል፡፡ ከያዕቆብ የሚመጣ ገዥ ይሆናል› ሲል ስለ መሲሁና ስለ እረሱ ነገድ ደግሞ እንዲህ ሲል ትንቢት ተናግሯል ‹ማደሪያህ የፀና ነው፤ ጎጆህም በአምባ ላይ ተሠርቷል፤ ነገር ግን አሶር እስኪማርክህ ድረስ ቄናዊ (ኬናዊ) አንተ ለጥፋት ባርነት ትሆናለህ፤ አምላክህ ይህን ሲያደርግ አወደ፤ በሕይወት ማን ይኖራል፤ ከኪቴም ዳርቻ መርከቦች ይመጣሉ፤ ያስጨነቅህን አሦርንም ያስጨንቃሉ፤ ነገር ግን እርሱም ደግሞ ይጠፋል፡፡› ብሎ የተናገረውን ልጁ ደሸት ትንቢቱን ሲከታተል በቀትር ጊዜ ከምንጩ ዳር ተቀምጦ ፍልስፍናውን በአዝዋሪት ውሃ ሲያናና ሲፈለስፍ ለብልአም የታየው ኮከብ እንደገና ለደሸት ታየው የአዝዋሪቱን አረፋ ኮከብ እየተከታተለ ሲጽፍ ድንግል ሴት ያለ ዘር የተወለደ ልጅ ታቅፋ አያት፤ ወዲያውኑ ያየውንና ወደ ድንግሊቱ የመራውን ኮከብ ሥዕል በናስ ሰሌዳ ሥሎና ቀርጾና ድንግሊቱን፣ ልጅዋን እንደታቀፈች በወርቅ ሰሌዳ ሥዕሉን ቀርጾ ለልጆቹ አስቀመጠው፤ ሊሞት ሲል ‹ይህ ኮከብ የሚመስል በምሥራቅ በኩል ሲወጣ ዐይታችሁ፤ ጨረሩን ወደሚያመለክታቸሁ ምድር ተጉዛችሁ፣ ከምድራችሁ ከምታገኙት ከምታገኙት የምድር አበል ወርቅ፣ እጣን፣ ከርቤ፣ ልብስ ይዛችሁ ይህን አምላካችን ለአባታችን ለአዳም ለሔዋን እዲሰጣት የሰጠውን፣ አብርሃም ለአባታችን ለመልከጼዴቅ አሥራት ብሎ የሰጠውን እንአርያ በክብር ይዛችሁ፣ የኮከብ ብርሃን ለስግደት ሰግዳችሁ ስጡት፤ ሉልና ዮጴ የወርቅ ሃመልመላል ለእናቱ ስጡለት፤ ይህ እስከሚሆን ድረስ እንቆ አርያውን ተመልከቱት፤ እርሃብ ዘመን ሊሆን ሲል መልኩ ይጠቁራል፤ የጥጋብ ዘመን ሊሆን ሲል መልኩ ያበራል፤ ቅባቱ ይጭረቀረቃል ሲል እናተም ማርና ወተት ወደሚስባት ምድር ሔዳችሁ ትኖራላችሁ› ብሎ ለልጆቹ በተለመደ በአሥራ አንድ ሱባኤ ሞቷል፡፡ ይህም ዘመን በእሥራኤል ንጉሥ አልነበረም፡፡ በእሥራኤል ላይ የነገሠው ንጉሥ ዳዊትም በመንፈስ የታየውን ትንቢት እንዲህ ሲል ተናጋገረ ‹በፊቱ ኢትዮጵያውያን ይሰግዳሉ ጠላቶቹም አፈር ይለብሳሉ፤ የተርሲስና የደሴቶች ነገሥታት ሥጦታን ያመጣሉ፤ የአረብና የሳባ ነገሥታ እጅ መንሻን ያቀርባሉ፡፡ነገሥታት ሁሉ ይሰግዱለታል፤ አህዛብ ሁሉ ይገዙለታል፡፡› ሲል ከደሸት በኋላ ተናግል፤ ይህም ትንቢት ለመሲህ እንጅ ለሰለሞን አይደለም፡፡ ነገር ግን ከወርቅ በፊት ሰም ስለሚቀርብ ሰም የሰለሞን ወርቅ የመሲህ ትንቢቱ ተፈጽሟል፡፡
በልአም ሙት የምታስነሣ የነበረች የሸምሸልን አባት ቀራሚድን ወለደ፤ ዘጠኝ ወንዶችና ሴት ሸምሽልን ወለደ፤ ሸምሽል ፈላስፋው ደሸትን ወለደች፤ አባቱ አይታወቅም ይባላል (እዚህ ታሪክ አልፋለሁ)፤ የደሸት ልጆች ማጂ፣ ጅማ፣ መንዳና መደባይ ናቸው፡፡ የማጂ ዘሮች በኮከብ የሚያመልኩ፣ መንፈሰ ኃይል የተሰጣቸው መጭውን የሚናገሩ፣ በመንፈስ ስለመነጋገር የሚያምኑ ናቸው፤ ማጂ ማራን፣ ዣማን፣ ጂየማን ይወልዳል፤ ጂማ አረርቲን፣ ገነቲን፣ ሞረን ይወለዳል፤ እነዚህ ሁሉ የግዮን ምንጭ በሚፈልቅበትና በሚከበው ምድር ሄደው ሠፈሩ፤ በአባታቸው ስም ምድሩን ደሸት አሉት፤ ነገሥታት ደግሞ በንጉሥ ጎዣም በዳሞው ልጅ ስም ጎዣም ተብሏል፤ ይህም ስም የተቀየረ በዐፄ ዘመነ መንግሥት በአራት ሽህ አምስት መቶ ዓመት ከተቆጠረ (500 ዓመት ከክ.ል.በፊት) ነው፤ ማራ ከወገኖቹ ተልይቶ ቤተሰቦቹን ይዞ ወደ ፀሐይ መውጫ በተራሚው ሀገር ውስጥ ሄዶ ተቀመጠ፤ ገነት ኦዶምን ይወልዳል፤ ኤዶም ወደ ፀሐይ መውጫ ወደሚገኘው ባሕር ሄዶ መኖሪያውን አደርገ፡፡
ቀለመ ዮጵ የተባለው ዘግዱር የዣማን ነገዶች ግማሹን ታሪክ ፀሐፊ አድሮጎ ቤተአንዳ የዛሬ አንዳ ቤት ግማሹን የመደባይ ነገዶች ቦረኖች ወደሞኖሩበት ቤተማራ የዛሬው መርሃቤቴ ላካቸው፤ ያንም ሃገር በአባታቸው ስም ወንዙን ዣማ አሉት፤ በዚያንም ሃገር የማሩ ነገዶች ይኖሩበታል፤ እነዚህ ማሩ የተባሉ ሁለተኛው ዘግዱር አሚንሆ የተባለውን የእብነልሃኪም የልጅ ልጅ በግብጾች ጋር በአደረገው ጦርነት ለእርዳታ ሄደው በዚያው ቀርተዋል፡፡ ያም የሠፈሩበት ሃገር አማርና ይባላል፡፡ ከሁለት ሺህ ዓመታ በላይ ከኖሩ በኋላ በዐፄ ላሊበላ ዘመነ መንግሥት ከግብፅ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በቤተሃማራ ከሚኖሩት ጎሣዎቻቸው ጋር ተቀላቅለው ኖሩ እነዚህም የዛሬዎች አማራዎች ናቸው፤ ከነገደ አማራ ኢትዮጵ አቲባን ወለደ፤ አቲባ ሁለትኛው አዜብን ከሣዱንያ ልጅ ቂቂ ከምትባል ንግሥት ወለደ፤ አዜብ ሰቢን ወለደ፤ ሰቢ በግዮን ዳርቻ ስመ መንግሥቱ ሞረሽ መለከ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ በሃያ አንድ ነገሥታ በአርባ አምሰት ሀገሮች ላይ ነገሠ፤ ግዛቱም በስሙ ሞሪያ ከተባለው ተራራና እስከ ከሱኪ ባሕር ድረስ ነው፡፡ ሞረሽ መለከ ሠራዊቱን ሃገር እንዲያቀኑ፣ ግዛት እንዲያስፋፋ ወደ መካከለኛው ግዮንና ወደ ታላቁ ባሕር ላካቸው፤ እነሱም ምድሩን እርስት አድርገው በዚያው ቀርተዋል፤ በስሙ ምድሩን ሙርታንያ፣ ሕዝቡም ሞረቴ ተብለዋ፤ ግዛቱም ሰባ ሰባት ዓመት ነው፤ በፈንታው ልጁ ልብና ነገሠ፡፡ ሞረሽ መለክ የተባለው የአዜብ ልጅ ሳቢ በሙርታንያ ልብናን ወለደ፤ ልብና በግዮን ዳርቻ ስመ መንግሥቱ ሊባኖ ተብሎ በኢትዮጵያ ምድር ሁሉ አርባ አራት ዓመት ነገሠ፤ ልብና ከፍልስጢሞችና ከአማሌቅ ጋር ሲዋጋ በጌራራ ሞተ፤ ለልብና አንድ ልጅ ስለነበረው በፈንታው ሱካውያንን፣ አዜባውያን አነገሡለት፤ በነገሠ በሦስት ዓመት የአባቶችን ሕግና ሥርዓት ለመፈጸም በግዮን ዳርቻ እንደገና ነገሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ ዳግመኛ ነገሠ፤ ግዛቱም ሦስት ሱባኤ ተኩል (ሃያ አራት ዓመት) ነው፡፡ አቤሜሌክ የተባለው መሌክ ጋዝያን በጌራራ ወለደ፤ ጋዜያም በአባቱ ፈንታ አበሰኒ ተብሎ በሲና አዜባውያንና ሱካውያን አነገሡት፤ በጋዝያ ዘመነ መንግሥት ብዙ ሕንፃ ተመሠረተ፤ ያነንም ምድር በስሙ ጋዛ ተባለ፤ ግዛቱም ሰባት ሱባኤ ነው፡፡ ይህም አርባ ስምንት ነው፡፡ አቢሲኒ የተባለው ጋዝያ አድያምን ወለደ፤ አድያም በግዮን ዳርቻ ስመ መንግሥቱ ላክንዱን ተብሎ በኢትዮጵያ ምድር ነገሠ የግዛቱም ዘመን ሰማንያ ሦስት ዓመት ነው፤ ላክንዱን የተባለው አድያም ታላቁ ንጉሠ ነገሥትን ታንዛን ወለደ፡፡
እንደዚህ ሆነ የአድያም ልጅ ታንዛን አሥራ ሁለት ወንዶች፣ አሥራ ሁለት ሴቶች ከአራት ሚስት ወለደ፤ የወንዶች ሰማቸው ስኒ፣ ጉሚዚ፣ ጉድሪ፣ ኩንፍ፣ ከፊን፣ ጎም፣ ከሬች፣ ጉፍ፣ ሓማ፣ ዝሪ፣ ሣምሪ፣ ዮቶሮ፤ የሴቶቹ ስም ካሳኪ፣ ቲካ፣ ዩኒና፣ ብሌኒ፣ ቢሸሎ፣ ችልጋ፣ ልሄም፣ ሳለታ፣ ኤፍራታ፣ ወልቃ፣ ቆቂና፣ ነገዶች ናቸው፤ እነዚህ ሁሉ አባታቸው ኢትዮጵ ንኤል የሚባል ታላቅ ድንጋይ ለማሳሰቢያ በአስቀመጠበት በግዮን ዳርቻ ሳለ ተወለዱለት ታንዛን ስመ መንግሥቱን ንርአስ አሰኝቶ በግዮን ዳርቻ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ በነገሠ ጊዜ በሥሩ አራት ንጉሦች ሲያነግሡ ታላቁ ልጁን ሲኒን በኩርነት የመጨረሻውን ልጁን ክህነትን አምላኩን እንዲያገለግል ሁለቱን የአባቶችን አፅም እንዲጠብቁና በቦታው እንዲተኩ ወደ እርስታቸው ወደ ምድያም ላካቸው፤ ሌሎቹን ሴቶችና ወንዶችን ይዞ ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ተራራማው ሃገር ሄዶ ቤተ መንግሥቱን ቆረቆረ፤ ስምዋንም ዋይዝ አላት፤ የታንዛንያ ልጆች ያገኙት ምደር ዝፍ፣ የምንጭ ውሃ፣ ታላላቅ ወንዞች የሚገቡበት ለምለም መሬት ሆኖ የዛፍ ፍሬ ለመልቀም አመቺ ስለነበረ በመካከላቸው ጠብና ግጭት እንዳይኖር ለሃያ ሁለት የታንዛኒያ ልጆች ተካፈሉት፤ ከነሱ ቀጥለው የማጂ ልጅ ሄደ፤ መደባይ የማራን ልጆች ሃገር አልምተው ነበርና ጦርነት ቢያነሱ ሊተባበሩ በታላቅ ተራራ ሥር በደጋው መሬት ቃል ኪዳን አደረጉ፤ በየደረጃቸው የታላቅነትና የታናሽነት ምልክት የሚገልጽ የማንኛው ልጅ መሆናቸውን የሚያስረዳ ክትባት አደረጉ፤ ፊታቸውን ተቆረጡ፤ የመጀመሪያው ልጅ ሲኒ ወደ ምድያም ስለሄደ የቁርጡ ክትባት ምልክት በሁለት ይጀምራል፤ ይሄውም የመጀመሪያውና የሁለተኛው ልጆች መሆናቸውን የሚገልጹትበት ቁጥር ነው፡፡ II-III እያለ እስከ ሰባት ሲደርስ እንደገና በግንባራቸው ላይ ክብ ዓይነት ቆረጣ ያደርጋሉ፡፡
ከነዚህም ሖማ የተባለው የገላው ቆዳ በጣም የጠቆረ ቁመቱ ረጂም አስፈሪና አስደንጋጭ ነበረ፤ ሖማ ማለት በሱባ ‹የእውነት ዛፍ ነህ› ማለት ነው፡፡ የሖማ ልጆች ጎጂ፣ ጂን ሻቃ፣ ጅንጀር፣ማሴሻ ናቸው፡፡ ሻቃ ጠንካራና እንደአባቱ አስፈሪ ጥቁር ነው ትርጓሜውም የአምላክ ትንፋሽ ማለት ነው፤ ሻቃም በአባቱ ሥር ሆኖ በግዮን ዳርቻ እስከ ደሸት ድረስ አራት ሱባኤ ተኩል ገዝተዋል፡፡ የሆማ ልጅ ጀንጀር ፈጣኑ ርዋጭ ናይጀርን ወለደ፤ ናይጀርም አያቱ ታንዛን ባርኮና አንግሦ ግዛ ብሎ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ፈቀደለት፤ ንጉሥ ናይጀርም የሄደበትን ሃገር ወንዝ በስሙ ናይጀር እንዲባል አድርጓል፡፡ አልጀር ብሂል ርዋጭ የሖማ ልጅ ማሊ መሣይ ካህን ስለነበረ አያቱም እንደ ቶርአብም ክህነትን ስለባረከለትና በፈቀደውና በወደደው መሬት እንዲቀመጥ ስለፈቀደለት የሄደበትን ሃገር በአያቱ ስም ታንዛን አለው፤ ልጆቹ የቡራኬን ሥራ አጥብቀው የሚወዱና የሚፈቅዱ ናቸው፤ መሣይ በቡራኬ ቀን ንፅሕ ተላጭተው በጆሯቸው ጌጣጌጥ እንጥልጥል አድርገው ይቀርባሉ፤ ሕግና ሥርዓት ሆኖ እስከዛሬ ድረስ አለ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን ሖማ በግዮን ዳርቻ መኖሪያውን አደረገና ከዛፍ ሥር ተቀምጦ ሳለ መልኩዋ የሚያምር የሚያንፀባርቅ ልብስ ለብሳ አንዲት ሴት ልጅ ከባሕሩ ውስጥ ወጥታ ከአለበት ዛፍ መጥታ እንደጥላ ሆና ስትገባ አያትና ቢፈልግ አጣት፡፡
ከዚያ ወደቤቱ ሳይሔድ ከወገኖቹ ተለይቶ በዛፍ ሥር ለብዙ ቀን ከኖረ በኋላ ተገለፀችለትና ለምንድነው ይሄን ያክል ቀን የተቀመጥከ አለችው፤ አፍቅሬሽ አላት፤ ከአፈቀርከ(ኝ) አግባኝ ብትለው አፍቅሯት ነበርና እሺ አላት፤ ስምህ ማነው ብትለው ሖማ አላት፤ ይህም ዛፍ ሖማ ነው አለቸው፤ ያንቺስ ሺባ እባላለሁ አለችው፤ ተጋብተው ብዙ ዓመታት ከሆናቸው በኋላ የወገኖቹ ሴቶች ልጆች ጂና፣ ጃንካ የሚባሉ አደን ሄደው ሳለ አገኙትና ለምን እንደጠፋና ወደ ቤቱ የማይሔድበትን አጥብቀው ጠየቁት፤ እሱም ሁሉን ነገር ገልጾ ነገራቸው፤ እነሱም አብረው እንዲኖሩ ቢጠይቁት ሺባ ባለቤቱን አስፈቅዶ አብረው ከወገኖቻቸው ተለይተው እንዲኖሩ አደረገ፤ ከዚያም ሁለቱን በሥጋ አጋባቸውና ልጅ ወለዱለት የሖማ የልጅ ልጆች እየበዙ እንደሄዱ ሲያውቁ በዘራችን ያለአምልኮት አንኖርምና ስለዚህ ከወገኖቻችን ሄደን የምናምልክበትን ነገር እናምጣ አሉዋት ለሺባ፤ እሷም እኔን ብታመልኩ መአት ቢመጣ እስወራችኋለሁ፤ የምትፈልጉትን ሁሉ እሰጣችኋላሁ፤ ስለአምልቱ ሥርዓት አባታችሁ ያሳያችኋል አለቻቸው፡፡
ሆም ሆማም እሚያመልኩበትን ጌጥ በጥቁር እንቁ አሠርቶ ሸባሻንቃ ለወንዶች ልጆች፣ ሻንቀል ለሴቶች ልጆች ማለኪያ አደረገላቸው፤ ወደ ሻበሻንቅና ወደ ሻንቀል ለአምልኮት የሚገቡ ሁሉ ክሰል ፈጭተው፣ አልመው ከቡልቃ ፍሬ ጋር ለውሰው ተቀብተው መግባት አለባቸው፤ ሴቶች ደግሞ ጥቁርና ቀይ አፈር ከቡልቃው ፍሬ ዘይት ጋር ለውሰው ተቀብተው ይገባሉ፤ ይህም የአምልኮ ባሕልና ልማድ እስከዛሬ ድረስ አለ፤ ከቡዳና ከሂንዱ ሃይማኖት ጋር ይስማማል፤ ከነዚህ እንደመነጨ የሚያስረዳው የህንዶች እምነት ከዚህ የተያያዘና ሺባ በጣም በህንዱ የታወቀች ናት፤ ሺባ የምትባለው ነጭ ነገር ስለምጠላ ዛፍ ደርቆ ቅርፊቱን በሚጥልበት ሰዓት በቶሎ እንዲጠቁር ያቃጥሉታል፤ ከነሱ መሃል ነጭ ቆዳ ሰው ቢወለድ ገለው ይቀብሩታል ወይም ያቃጥሉታል፤ ይችውም የመንፈስ ዛር ታምርን በመሥራት ከአደጋ ነገር በመሰወር የታወቀች ስለነበረች ሃንዲ የሚባሉ ጎሣዎች ወርቅና ልጃቸውን ስእለት በየጊዜው ይሰጡዋት ነበር፤ ሻቃ የሚባለው በመንፈስ እናቱ ሸበሻንቃ በተባለው ማምለኪያ የታመነ ስለነበረ ወርቅና በከብት የከበረ ሆኖ መቀመጫውን በግዮን ወንዝ አደረገ ልጆቹም በአባታቸው ስም ሻንቅላ ተባሉ፤ ወንድሞቹም ጀንና ሉቅ በዋሻና በድንጋይ ሥር ቤታቸውን አደረጉ፤ ባህላቸውም ከታላቁ ወንድማቸው ጋር ተመሳሳይ ሆነ፤ በጋብቻቸው ጊዜ ከጂን፣ ከሉቅ ልጆች ጋር ሴት በሴት ተቀያይረው ይጋባሉ፤ ሴት እህት ከሌለው አንዱ ከነሱ ዜጋ ውጭ የሆነውን ሰው ገሎ ሰለባ በማድረግ ሰለባውን አሳይቶ ሴት ማግባት ይችላል፡፡ ጀግንነቱ፣ ክብሩ፣ ሹመቱ ሁሉ በነሱ ዘንድ ሰለባ ብቻ ነው፤ ሌላ በኩርነት ያለው አለቃ መሪ ሊሆን ይችላ፡፡
እነዚህ ጎሣዎች የዛፍ ፍሬ ለቅመው ሥር ቆፍረው የአገኙትን አውሬና በራሪ ወፍ አሞራ ገድለው ከመብላት በስተቀር ከብት አርብተው አታክልት ተክውለው አያውቁም ነበር ነገር ግን የሚሠሩት ነገር ሁሉ በህብረት ነው፡፡
ኖርኡስ ታንዛን ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ በተባለ በሰማኒያ አምስት ዓመቱ ዕብራውያን ከግብፅ አርነት ነፃ ወጡ ወደ ከነዓን ርስታቸው በተመለሱ በሦስተኛው ዓመት በተወለደ በመቶ ሠላሳ አንድ ዓመት አንቀላፋ፤ በፈንታውም በሲና በረሃ የሚኖረው ራጉኤል የተባለው ታናሹ ልጅ ዮቶር በግዮን ዳርቻ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ ነገሠ፤ በምድያምና በሲና ምድር የኤልሻዳይ ካህን የክህነቱ ራጉኤል የተባለ የታንዛን ልጅ ዮቶርአብ የሚባል ነበር፡፡
ለዮቶርአብ አሥር ወንዶች፣ ሰባት ሴቶች ነበሩት፤ ወንዶች ኤልሳ፣ ዛሆ፣ ኡሪኤል፣ ንስኤል፣ አልባኤል፣ አልባ፣ ኤልሃ፣ ዙርባኤል፣ ተውሳ፣ አባብሂር፤ ሴቶች ሲፖራ፣ ልሂ፣ ዘሃራ፣ ተምና፣ ለውይዛ፣ እሰድ፣ ዘኒባ ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ በምድያም ምድር ተወለዱለት፡፡
የኤል አገልጋይ፣ የምድያም ካህን ራጉኤል በምድያም ምድር የአባቶችን ታሪክና ስም የያዙና፣ የፈጣሪን ቸርነትና ረዳትነት የሚገልፁ መጻሕፍትን በበግ፣ በፍየል፣ በፈረስ ቆዳ ጻፈ፤ ጽሕፈት በኢትኤል ተጀምሮ በልጆቹ በሥነ ሥርዓት ቢያዝም ከአጥንትና ከእንጨት ከተሠራ ሰሌዳ ላይ ከመጻፍ በስተቀር በብራና ተፅፎ አያውቅም ነበር፡፡ ራጉኤል በብርና በወርቅ በከብትም ከመክበሩ ሌላ በአስተዋይነቱና በጥበቡ ብዛት በሞአብና በአሞን ልጆች በአማሌቅም ሎጆች በፌርዛውያውን፣ በአሞራውያን፣ በከነአናውያ፣ በአቡሳውያን ታውቆ ነበር፡፡ ጥበቡን ለማየት፣ ዕውቀቱን ለመማር ወደ እርሱ ይሄዱ ነበር፡፡ ከነዚህም ከግብፅ ተነሥቶ ወደ ራጉኤል ከሄዱት አንዱ ሙሴ ነበር፡፡ ሙሴም በራጉኤል ቤት ሳለ የአምላክ አገልጋይ ካህንና ትሁት ሰው ለመሆን ይተጋ ነበር፡፡ የምድያም ካህን ራጉኤልም የአምላክ ሰው መሆኑን አስተውሎ ታላቋን ሴት ልጁን ሲፖራን ለሙሴ አጋብቶ በቤተ መቅደሱ ላይ ሾመው፤ ሙሴም ብዙ ቀናት አብሮት ተቀመጠ፡፡
እንደዚህም ሆነ፣ ግብፃውያን በዕብራውያን ላይ የሚያደርጉትን ግፍ የእሥራኤል አምላክ ተመለከተ፤ የዕብራውያን ሃዘንና ጸሎት ወደ አምላክ ደረሰ፤ ስለዚህ አምላክ በግብፃውያን አርነት እጅ ሕዝቡን እሥራኤልን ያወጣ ዘንድ ለሙሴ በአምላክ ተራረራ በኮሬብ በነበልባል ውስጥ የአምላክን መላክ ዐየ፤ ሙሴም ወደዐየበት ዛፍ ተጠጋ፤ በነበልባሉም ውስጥ እንደዚህ የሚቃል ሰማ ‹ሙሴ ሙሴ ሆይ ወደዚህ አትቅረብ፤ የቆምክበት ሥፍራ የተቀደሰ መሬት ነው፤ በቅድሚያ የአቡውያን ትምህርት የሆነ ጫማህን ከእግረልቦናህ ፈጽመህ አውጣ፤ ደግሞም እኔ የአባቶችህ አብረሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ› አለው፡፡
‹ሕዝቤን ዕብራውያንን ከግብፅ ምድር ታወጣ ዘንድ ወደ ፈርኦን እልክሃለሁ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ እኔም የላክሁህ ምልክቱ ይህ ነው፤ ሕዝቤን ከግብፅ ምድር ባወጣህ ጊዜ በዚህ ተራራ ላይ ለአምላካችሁ ትገዛላችሁ› አለው፡፡ ሙሴም የአባቶችን አምላክ ቃል ሰምቶ ወደ ግብፅ ወረደ፤ ከዚያም በብዙ ታምር ዕብራውያን ከግብፅ አርነት አውጥቶ በአምላክ ረዳትነት ተመልሶ መጣ፤ በዚያም አማቱ ራጉኤል በአምላክ ተራራ በኮሬብ ወደ ሠፈረ ሙሴ መጣ፤ ሙሴንም እኔ አማትህ ዮቶር አብ፣ ሚሰትህ ሲፓራ ፣ልጆችህ ጌርሳም አልኣዛር መጥንልሃል አለው፤ ሙሴም አማቱን ሊገናኝ ከድንኳን ወጣ፤ ሰገደም ሳመውም፤ እረስ በራሳቸው ደኅንነታቸውን ተጠያየቁ፤ ወደ ድንኳን ገቡ፤ ሙሴም አምላካቸው በግብፅ ባለሥልጣኖችና በፈርኦን ላይ ስለ ዕብራውያ ያደረገውን ሁሉ በመንገድም ያገኛቸውንም ድካም ሁሉ ኤልሻዳይ አምላክ እንዳዳናቸው ለአማቱ ነገረው፡፡
ካህኑ ራጉኤልም ለዕብራውያን ስላደረገው ቸርነት ሁሉ ደስ አለው፡፡ ራጉኤል በሙሴና በዕብራውያን ስላደረገው ቸርነት ሁሉ ከግብፅውያን አርነት ስለዳናቸው ደስ አለው፡፡ ራጉኤልም በሙሴና በዕብራውያ ሽማግሌዎች መካከል ቁሞ፤ እጁን ዘርግቶ እንዲህ አለ ‹ከግፅውያና ከፈርኦን እጅ ሕዝቡን ያዳነ የእሥራኤል አምላክ ይባረክ፤ አልሻዳይ አምላክ ከአማልክት ሁሉ የበለጠ የእሥራኤል አምላክ እንደሆነ አሁን አወቅኩ› አለ፤ እንደዚህም ብሎ የእህል መስዋእት ስንዴና ወይን በአባታቸው በመልከጼዴቅ የታዘዘውን ሁሉ የሚቀጠለውንም የሚጤሰውንም ለአምላ ወሰደ፤ ሁለቱም በአንድ ላይ መሥዋዕትን አቀረቡ፤ ኤልሻዳይ አምላካቸው መስዋዕታቸውን ተቀበለ፤ የሚቃጠለውን ሁሉ ከሰማይ እሳት ወርዶ በላው፤ በአምላካቸው ፊት ከሙሴ ከአማት ጋር የዕብራውያን ሽማግሎዎች የመሥዋዕት እንጀራ ሊበሉ መጡ፡፡
እንደዚህም ሆነ በነጋው ሙሴ በሕዝብ ሊፈርድ ተቀመጠ፤ ሕዝቡም ከጥዋት እስከ ማታ ድረስ በሙሴ ፊት ቁመው ነበረ፤ ራጉኤልም በሕዝቡ ሙሴ ያደረገውን በየጊዜው ይህ በሕዝብ የምታደርገው ምንድነው? ሙሴም አማቱን ሕዝቡ አምላክን ለመጠየቅ ወደ እኔ ይመጣሉ፤ ነገርም ቢኖራቸው ወደ እኔ ይመጣሉ፤ በዚህና በዚያ ሰውም መካከል እፈርዳለሁ፤ የአምላክ ሕግና ሥርዓትንም አስታውቃቸዋለሁ አለው፡፡
ራጉኤልም አለው ‹አንተ የምታደርገው ይህ ነገር መልካም አይደለም፤ ይህ ነገር ይከብደሃል፤ ሕዝቡም ይከብደዋል፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችለም፤ አሁንም እመክርሃለሁ፤ ቃሌን ስማ፤ አምላክ አንተ ጋር ይሆናል፤ አንተ በአምላ ፊት ለሕዝቡ ሁን፤ ነገራውንም ወደ አምላ አድርስ ሥርዓቱንም፣ ሕጉንም አስተምራቸው፤ የአምላን ሕግና ሥርዓቱን በቃልህ ሰምተው የሚጽፉ ጸሐፊዎች አዘጋጅላቸው፤ በጆሯቸው ጠዋትና ማታ የሚነግሯቸውና የሚያስተምሯቸው ዐዋቂዎችን ምረጥላቸው፤ የሚያደርጉትንም ሁሉ ለአስተማሪዎች አስተምራቸው፤ ስለነጋራቸውም ደግሞ እንደዚህ አድርግ ከሕዝቡ ሁሉ ዐዋቂዎችን አምላክን የሚፈሩ፣ የታመኑ፣ የግፍን ሥራ የሚጠሉ ሰዎች አስመርጥ፤ ከእነሱም የበላይ አዛዥ፣ የሺህ፣ የመቶ፣ የዓምሣ፣ የአሥር አለቆች ሹምላቸው በሕዝቡ ላይ ሁልጊዜ ይፍረዱ፤ ለመፍረድ የማይችሉትን ወደ አንተ ያምጡት፤ ታናሹን ነገር ሁሉ እነሱ ይፍረዱ› አለው፤ ‹ይህ ነገር ለአንተ መልከም ነው፤ ይቀልሃል፤ ይህንም ፈጽመህ ብታደርግ አምላክ ቢያዝህ መቆም ትችላለህ፤ ይህ ሕዝብ ደግሞ በሰላም ወደ ሥፍራው ይደርሳል፤ የነመልከጼዴቅ፣ የነኢትኤልም ሕግና ሥርዓት እንደዚህ ነው› አለው፡፡
ሙሴም የአማቱን የራጉኤልን ቃል ሰማ፤ ያለውንም ሁሉ አደረገ፤ ሙሴም ዐዋቂዎችን ሁሉ መርጦ በሕዝቡ ላይ የበላይ አዛዥ፣ የሺህ አለቃ፣ የአምሣ፣ የአሥር አለቃዎች፣ጸሐፊዎችና አስተማሪዎች ሁሉ አዘጋጀና ሾመላቻ፤ በሕዝቡም ላይ ፈረዱ፤ የከበዳቸውን ነገር ግን ወደ ሙሴ አመጡ፤ ከዚያም ሁለቱ በሰላልም ተሰነባበቱ፡፡
ከዚያም የክህነቱ ስም ራጉኤል የተባለው ዮቶር አብ በተወለደ በስልሳ ሰባት ዓመቱ ዕብረውያን ከግብፅ በወጡ በሦስት ዓመት አባቱ ኖርኦስ ታንዛን ስለሞተ በግዮን ወንዝ ዳርቻ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ ነገሠ፤ በነገሠ በሃያ ሁለት ዓመቱ አንቀላፋ፤ ከእሱ ቀጥሎ በፋንታው ልጁ አባብሂር ዕብራውያን የረዳ መንገድ የመራቸው ስለነበር ከዕብራውያ ወገን የምትሆን የአሚን አዳብ ልጅ ሩት አሚን የምትባለውን አግብቶ ወደ ግዮን በሚያወርደው ምድር ተቀመጠ፤ በዚያም ኢትዮጵስን ወለደ፤ ስመ መንግሥ ሰንደቅ ዣን ተብሎ በግዮን ዳርቻ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ተብሎ በነገሠ በሰባተኛው ዓመት ታላቁን ከተማ ሱባን ሠራ፤ በሱባም ታላላቅ ግንቦች ተገነቡ፤ የውሃ መከማቻ ጉድጓዶች ተዘጋጁ፤ በምድርም እንደሱባ ያለ ከተማ አይገኝም ነበር፡፡
ኢትዮጵስ የሱባውያ ንጉሥ ናኦድ በእሥራኤል ላይ መስፍን በነበረ ጊዜ በሳሌምና በአካባቢዋ የሚኖሩ መንደሮች ያለ ጦርነት በሰላም ኖሩ፤ በሱባ የሱባ ንጉሥ ኢትዮጵስ በዘመኑ ምድር ከማካፈልና ከተማ ከመቆርቆር የሀገር ስም ከማውጣት በስተቀር ጦርነት አድርጎ አያውቅም፤ ልጁን ሄቤርን በቃዴስ፣ በፀእናይ መካከል አንግሦት ስለነበር ዕብራውያንና የቃዴስ ንጉሥ ቃል ኪዳን ስለነበራቸው የሄቤር ሚስት ኢያኤል የምትባለው የኢያቤስን የጦር መሪ ሢሠራን ገደለችና የግድያውንም ምልክት እራሱን ለእሥራኤል ልጆች ሰጠች፤ በዚያም ዕብራውያን ስለተደረገላቸው እርዳታ አምላካቸውን አመሰገኑ፤ በሄቤርቤትና በእሥራኤል ልጆች ቤት ወዳጅነታቸው ፀና፡፡ ኢትዮጵስ ሰንደቅ ዣን በየ በርሃው መንደር እየቆረቆረ ሴት አግብቶ በቆረቆረው መንደር ሁሉ ማስቀመጥ ይወድ ነበር፡፡ ስለዚህ ንግሥት የተባሉት ሰባት ሰለነቡ አምሣ ልጆች ከነሱ ወለደ፡፡ እነዚህም አሥራ ሦስት የነገሡ ናቸው፡፡ እነዚህም የኤብያ ንጉሥ ኦማም በአዜብ በርሃ የምትገኝ መንደር የመጀመሪያቱ ሳባ፣ የሳባ ንግሥት ቲራ፣ የኦፊር (የዛሬው ውጋዴን) ንጉሥ ሸሚዳ፣ የኤውላጥ ንጉሥ ሃሺሞን፣ የመደባይ ንጉሥ እናርያ ኋላ በስሙ እናሪያ የተባለው የዛሬው ሊሙ፣ መደባይ መንዲ የሚባሉት የዛሬዎቹ ኦሮሞ አልብኖ ናቸው፤ የመንዲ ንጉሥ ኢያቢስ፣ የኪና ንጉሥ ጂማ፣ የልብስኖ ኑጉሥ ስልባኖን፣ የቃዲ ንጉሥ ሄቤር፡፡
በሰንደቅ ዣን ሰር ወይም ዙፋን ወራሹ ኤልካኖ፣ በሰብያ የሱባ ኑግሥ ሲሆኑ አሥሩ ወንዶች ናቸው፤ ሴቶች ደግሞ የአዲን ንግሥት በለሣ፣ የኤደን ንግሥት አሊና፣ ከሁሉም ልጆቹ በላይ ይወዳት የነበረችውን ኢትግዝያ ከግዮን መገናኛ እስከ ሱኪ ድረስ ባለው በሊብያ ምድር ሁሉ አነገሣት፤ ንግሥተ ነገሥታ ዘኢትዮጵያ የሚል የማረግ ዘውድ በራስዋ ላይ ደፋች ኢትግዝያም በአባትዋ ሥር ሆና አርባ አምስት ዓመት ከገዛች በኋላ በተራራማው ሃገር ዋሻ ውስጥ ሄዳ ተቀመጠች፤ ያንንም ሃገር ያማራ ዜጎች የሚኖሩበት ምድር ነው፡፡
ሰንደቅዣን የተባለው ኢትዮጵ ስም አርባ ስድስት ዓመት በክህነት እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ አሥር ዓመት ገዝቶ በመልካም ገዜ አረፈ፤ በፈንታውም ልጁን ኤልካኖን ስም መንግሥቱን በአባቱ ስም ኢትዮጵስ ተብሎ በግዮን ወንዝ ዳርቻ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ከኪቲም እስከ ታላቁ ባሕር ውስጥ በሚገኙት ደሴቶች ሁሉ ላይ ነገሠ፡፡››

Advertisements
 

እውን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የለም? (4)

                  3.  የዘርአ ያቆብ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋነት

 1. በኢትዮጵያ በፈላስፋነት የሚጠቀሰው ዘርአ ያዕቆብ ነው፡፡
 2. ሆኖም የዘርአ ያዕቆብ ፍልሰፍና የኢትዮጵያ ፍልስፍና ብሎ ለመውሰድ ያስቸግራል፡፡
 3. ይህ ከሆነም ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡

ትችታዊ አስተያየት

በዘርአ ያዕቆብ ማንነት ዙሪያ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከል የመጀመሪያው ጥያቄ ‹እውን ኢትዮጵያዊ ነው ወይ?› የሚል ነው፡፡ በጥቅሉም በዚህ ዙሪያያሉ የክርክር አቋሞች ጽንፍ የሚይዙ ቢመስሉም ‹ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ አልነበረም› የሚሉት ተከራካሪዎች አቋም ግን ሚዛን የሚደፋ አይደም፤ ምክንያቱም ያሉትን ማስረጃዎች ከማጣጣል ያለፈ ውድቅ የሚያደርግ አስተማማኝ ማስረጃ አቅረበው መሞገት የቻሉ አይደሉምና፤ ክርክራቸውም ምኞታዊ እንጂ ማስረጃዊ አይመስልም፤ በዚህ አቋም በዋናነት ኮንቲ ሮስኒና ኢትኖ ሊትማን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ‹ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ነው› በሚል አቋም የሚከራከሩ ደግሞ ምንም እንኳ አቋማቸውን በአግባቡ የሚደግፉ አስተማማኝ ማስረጃዎች ቢኗራቸውም እንደ ሌሎች የምዕራባዊያንና ሩቅ ምስራቅ ሀገራት ፈላስፎች በዘርአ ያዕቆብ ዙሪያ ብዙ የትንታኔና የሰላ ትችት ማሳያዎችስላላቀረቡ ትኩረትን አልሳቡም፤ ሆኖም የተቃራኒዎቻቸውን አቋም ውድቅ ማስደረግ ችለዋል፤ ይህንን አቋም ይዘው በመሞገት ግንባር ቀደሞቹክላውድ ሰምነር፤ አምሳሉ አክሊሉና ዓለማየሁ ሞገስ ሲሆኑ፣ ቴድሮስ ኪሮስ፣ ዳዊት ወርቁና ሌሎች አብረው አቋሙን በመደገፍ ያብራራሉ፡፡ ለማንኛውም የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የሁለቱንም አቋሞች የመከራከሪያ ምክንያቶች እያነጻጸሩ በማቅረብ ለማሳየት ሳይሆን፣ የራስን ግንዛቤና አቋም በማንፀባረቅ የዘርአ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊነት (ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ መሆኑን) ማሳየት ነው፤ በመሆኑም ፍልስፍናው የኢትዮጵያ ፍልስፍናን መስካሪ መሆን እንደሚችል ተከራክሮ ማሳመን ነው፡፡

እንደተባለው ‹እውን ዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ አይደለም?› በሚለው ጥያቄ እንጀምርና አሳማኝ የሆነው የትኛው አቋም እንደሆነ አነጻጽረን እንመዝን፡፡ ‹ዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ አይደለም› በማለት የሚከራከሩት ወገኖች ይህን ሊሉየቻሉባቸውን የተወሰኑ ተያያዥ ምክንያቶች ያቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ ተከራካሪዎች መካከልም አንዳንዶቹ ዘርአ ያዕቆብ የተባለ ኢትዮጵያዊ ሰው መኖሩን በመካድ አውሮፓዊ የሚያደርጉት ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ህልውናውን ሳይክዱ ፍልስፍናውን ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና› ብለው ለመቀበል የተቸገሩባቸውን ምክንያቶች በማቅረብ ይሞግታሉ፤ በሁለተኞቹ ላይ በመመሥረትም ፍልስፍናው ኢትዮጵያዊ ያልሆነው እሱም ባይሆን ነው የሚል መከራከሪያየሚያቀርቡም አሉ፡፡ በአጠቃላይ የዘርአ ያዕቆብን ህልውነትንም ሆነ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋነት እስከመካድ ያደረሷቸውን ምክንያቶች ሲዘረዝሩ፡-

 1. ስለ እሱና ስለ ፍልስፍናውበጊዜው በነበሩ የሀገር ውስጥ ታሪክ ዘጋቢዎችና በውጭ ሀገራት ሚሲዮኖች የተገኘ የጽሑፍ ማስረጃ ወይም የእማኝነት ምስክር የለም፤ ለምሳሌ በንጉሥ ሱስኒዮስ ዜና መዋዕል ላይ ስለ እሱ ተጽፎ የተገኘ ፍንጭ የለም፡፡
 2. በራሱ እጅ የተጻፈው የመጀመሪያው ጽሑፍ (መጽሐፍ) የለም፡-
 3. በሐተታ መጽሐፉ ውስጥም በኢትዮጵያዊያን የተለመደውን ገለጻ አለመጠቀሙ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ስለመሆኑ ጥርጣሬን ያጭራል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያዊያውያን ምሳሌያዊና ፈሊጣዊ ንግግሮችና ቅኔዎች ያልተጠቀመው ለምንድን ነው? ይህ የሚያሳየው መጽሐፉ በኢትዮጵያዊ ሰው አለመጻፉንና ከውጪ ሰው የተገለበጠ ወይም የውጭ ሀገር ሰው የጻፈው መሆኑን ነው፡፡
 4. ወልደ ሕይወት ከሚባለው ደቀ መዝሙሩ በኋላ ፍልስፍና ቀጣይነት ሳይኖረው መቅረቱ፤ ደቀ መዝሙሩም ቢሆን ሃይማኖታዊ ስብከትን ከመተረክ ያለፈ ፍልስፍናዊ ትችቶችን በድፍረትና በማጎልመስ ያላቀረበ መሆኑ የዘርአ ያዕቆብን ኢትዮጵያዊ ፈላስፋነት አጠያያቂ ያደርገዋል፤
 5. የሐተታውን ጽሑፍ በዚያን ጊዜ የነበረ ኢትዮጵያዊ ጻፈው ብሎ ለማመን ይከብዳል፡፡ ምናልባትም ጽሑፍን በኢትዮጵያ የነበረ አንድ ሚሲዮን ጽፎት ኋላ ተቀባይነት እንዲያገኝ በሚል ዘዴ ኢትዮጵያዊ ጽሑፍ እንደሆነ ተደርጎ የተሰናዳ ይሆናል፤እንዳው ይሁን ብለን ‹ዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ነው› ብንል እንኳን ፍልስፍናው የተጻፈው ኋላ ከ19ኛው መ/ክ/ዘ ይሆናል እንጂ በተባለው ዘመን ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው የዚህ ዓይነት ሐሳብ ያፈልቃል ብሎ ለማመን ያስቸግራል፡፡ ወዘተ…

ከዚህ በላይ በተቃዋሚዎቹ የተነሱት ነጥቦች አግባባዊነት የሌላቸው መከራከሪያዎች መሆናቸውም ማየት ያስፈልጋል፤ ይህንንም ከመጀመሪያው በመሣት እንገምግም፡-

1)  በአጠቃላይ ሲታይ የመጀመሪያው አስተያየት የሚያስኬድ አይደለም፤ ምክንያቱም አንደኛ በዚያን ጊዜ ዘርአ ያዕቆብ ተራ ሰው ስለነበር በዜና መዋዕልም ሆነ በሌሎች ጽሑፎች መጠቀስ ያለበትና የሚገባው አይደለም፤ እሱም ቢሆን ታዋቂ ሰዎችን እየጠራ እነከሌ ያውቁኛል፤ ከፈረንጆች ጋር እንደዚህ ተነጋገርኩ በማለት አልጻፈም፡፡ ሁለተኛም የሱስንዮስ ዜና መዋዕልም ሆነ የሌሎች ጽሑፎች ዓላማ በኢትዮጵያው ውስጥ የሚገኙ ታዋቂና ሊቃውንት ያደረጉትንና የሚያስተምሩትን አስተያየት መዘገብ ሳይሆን ከንጉሡ የጦርነትና የሃይማኖት እንቅስቃሴዎች ጋር የተያያዙ ክስተቶችንና ድርጊቶችን መመዝገብ ነው፤ ከንጉሡ እንቅስቃሴ ጋር በመጥፎም ሆነ በመልካም ያልተያያዙ የታሪክ ክስተቶች የመዘገብ ዕድላቸው እጅግ ሲበዛ ውስን ነው፤ ሌሎች እንደገድላትና መንፈሳዊ ተግባራት ያሉት ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ ታሪካዊ ክስተቶችን ብቻ ነው የሚዘግቡት፤ ሌሎች ታሪካዊ ክስተቶች በገላጭነት ካልሆነ በስተቀር በእነሱ የመመዝገብ ዕድላቸው የመነመነ ነው፡፡በሦስተኝነት ደረጃም ዘርአ ያዕቆብ ራሱ አስተሳሰቡን ለማንም ሳይናገር ደብቆ በመያዝ መኖሩን‹ከእኔ በኋላ የእሚመጡ እንዲዓውቁኝ ግን እስክሞት ድረስ በእኔ ዘንድ ሸሽጌ የእምይዘው ይህን መጽሐፍ ልጽፍ ወደድኁ›በማለት ጽፏል፤ ይህ በሆነበት ለምን የልቡን አውቀው አልመዘገቡትም ማለት አይቻልም፡፡ በመጨረሻም በጊዜው ስለእሱ በታሪክ ጻሐፊዎች ወይም ሌሎች አካላት የተመዘገበ ታሪካዊ መስረጃ መኖር አለመኖሩ በጥናት ተመርምሮ የተረጋገጠ አይደለም፤ ምናልባት ይኖርባቸው የነበሩ አካባቢዎች ተጠንተው በአካባቢው በጽሑፍ የተቀመጠ ነገር መኖር አለመኖሩ ተፈትሾ ከዚያ በኋላ ቢሆን እንኳን የተወሰነ ማሳያ ይሆን ነበር፤ ያለበለዚያ ግን ይህንን ‹በጊዜው በነበሩ ሰነዶች ላይ ስላልተጠቀሰ› ሚለው መከራከሪያ ሚዛን አለመድፋት ብቻ ሳይሆን ለመከራከሪያነት የሚቀርብም አይደለም፡፡

2)  የሁለተኛው መከራከሪያም ችግር ከአስተሳሰቡ የመነጨ ነው፤ ምክንያቱም የትኛውም ፈላስፋ የተባለ ሊቅ የፍልስፍናው ማስመስከሪያ እሱ የጻፈው መጽሐፍ ወይም ጽሑፍ በዚህ ዘመን መኖር ሳይሆን የሐሳቡ ምጥቀትና የአስተውሎቱ ሁኔታ ነው፤ እንዲሁም በራስ የተጻፈ ጽሑፍ ለፈላስፋነት እንደ መስፈርት ከተወሰደ አብዛኞቹ ፈላስፎች ጥያቄ ውስጥ ይገባሉ፤ ለምሳሌ ሶቅራጥስ አንድም መጽሐፍ አልጻፈም፤ ጽፈዋል የተባሉትም ፈላስፎች በራሳቸው እጅ የተጻፈው አብዛኛው ጠፍቷል፤ ወይም አልተገኘም፤ ‹የዘርአ ያዕቆብ በእጁ የተጻፈው ጽሑፍ› መገኘት እንደ መስፈርት  ከተወሰደ የሌሎችም መወሰድ አለበት፤ መስፈርቱ ለሌሎች ካልሠራ ለዘርአ ያዕቆብም መሥራት አይችልም፤ እንዲሁም ስላለመገኘቱ እርግጠኛ አይደለንም፤ የትኛው ምሁር ነው በዘርአ ያዕቆብ እጅ የተጻፈውን ጽሑፍ ለማግኘት የሞከረ ወይም በተማሪው ተገልብጦ ለትውልዶች የተላለፈ መሆኑን ወይም አለመሆኑን ለማረጋገጥ የጣረ?  ከኢትዮጵያ የወጣ ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑም ገና እርግጠኛ አልተሆነበትም፡፡ ተገኘም ታጣም ግን መሥፈርቱ አግባባዊነት የለውም፡፡

3)  ሦስተኛው መሟገቻም ቢሆን ሙሉ አይደለም፤ ምክንያቱም ‹ዘርአ ያዕቆብ ፈላስፋ ነው› በማለት የምንሟገተው ስለ ቅኔ ፍልስፍና ስላብራራልን ወይም ስለ ምሳሌያዊና ፈሊጣዊ ንግግሮች ዕምቅነት ፍልስፍናዊ ትንታኔ ስለሰጠን አይደለም፤ ለቅኔውና ለፈሊጡ ሌሎች አሉን፤ ይልቁንም ዘርአ ያዕቆብ ከሌሎቹ የቅኔ ፈላስፎችና ንግግር አዋቂ ኢትዮጵያውያን በተለየ ዕይታ ያነሣው የአምላክ ህልውነት ጥያቄና ለሁሉም ነገር መመርመሪያ ልቦናውን ብቻ ሚዛን ማድረጉ ነው እንጂ! በመሠረቱ ይህ በልቦና ሚዛንት ዕውቀትን መመዘን በተፈጥሮ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሠጠ ፀጋ ነው፤ ልዩነቱ በድፍረትና በችሎታ መጠየቁና የጠየቁትንም በራስ ግንዛቤ መልስ ለመስጠት መሞከሩ ላይ ነው፤ ዘርአ ያዕቆብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የሚለየው የራሱን ልቦና መነሻ በማድረግ ያልመሰለውን በመተቹቱና የመሰለውን ዕይታ ደግሞ ማንፀባረቁ ነው እንጂ ከሌሎች የቅኔና የመጻሕፍት ሊቃውንት የበለጠና ምጡቅ እሳቤን ስላቀረበ አይደለም፡፡ ምናልባት ወጣ ላለው አስተሳሰቡ በዘመኑ የተከሰተው የሃይማኖት ግጭትና ንትርክ፣ እንዲሁምበሃይማኖት ምክንያት የተከሰተው ጦርነት አስተወፅኦ ያደረጉለት ይመስላል፤ ችግር ብልሃትን ትወልዳለች› እንዲሉ፡፡ መታወቅ ያለበት ግን በዕይታ ምጥቀት፣ ጥልቀትና በአቀራረብ ጠቢብነት ከሆነ እሱ እግራቸው ሥር የማይደርስባቸው ምጡቃንና ጥንቁቃን ሊቃውንት በየዘመኑ እንደነበሩን ነው፡፡ ይህንን የቅኔ ሊቃውንቱን ፍጡን፣ አስተውሎታዊ ዕምቅ ገለጻና ፈሊጥ የገባው ሰው ምስክርነት ይሰጣል፡፡ ዘርአ ያዕቆብ በተለየ ፈላስፋነት እንዲታይ ያደረገው ተጨማሪው ምክንያት ከአውሮፓውያን ዕይታና አስተምሮ ጋር ተመሳሳይነት ያለው መጽሐፍ በማዘጋጀቱ ነው፡፡ ቢሆንም ያዘጋጀው መጽሐፍ ኢትዮጵያውነቱን አስቀርቶ ወይም አሳቡን ኢትዮጵያዊ ሰው ሊያነሳውና ሊከራከርበት የማይችል ሆኖ አውሮፓዊ ሰው አይሆንም፡፡ እንዳውም መጽሐፉ አሁን እንደሚደረግበት መከራከሪያ ትኩረት የሚስብ መሆኑን ቢገምት ኖሮ ስንት የሚያስደምሙ ነገሮችን ባዘጋጀ ተማሪውም የበለጠ እንዲያዘጋጅና እንዲያስተምር ባሳሰበው ነበር፡፡ አለቃ ደስታ የተባሉ ሊቅም በዚህ ጉዳይ ላይ ተጠይቀው ‹‹ምንም ከመጽሐፉና ካነጋገሩ ሁሉ ሮማዊ ነው ለማለት የሚያግዝ ነገር አላየሁም፡፡ ሰውዬውም ቢሆን ዕውቀቱ ሰፊ ነበር ነገር ግን ስለ ክርስቶስ ሥጋዌ የመድኃኒታችንን ነገር ቸል በማለቱ አናመሰግነው፡፡ ሮማዊ ነው የሚሉትም መርማሪዎች እንዲህ ያለ ሊቅ በኢትዮጵያ አይገኝም በማለት ነው እንጂ እርሱ ግን ፍጹም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ካጻጻፉና ከመጽሐፉ ይታወቃል፡፡›  (Dawit Worku; The Ethics of Zär’a Ya’eqob p.89)  ብለዋል፡፡ ይህንን ብንተወው ‹ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ አይደለም›በማለት የሚከራከሩ ሰዎች የሚከተሉትን በአገላለጹና በመጽሑፉ ውስጥ የሚገኙት ማስረጃዎችን ውድቅ ሊያደርጉ አይችሉም፡፡

 •  በጸሎት መጀመሩ፡- የኢትዮጵያውያን ባህል ነው፡፡‹ሁሉን በፈጠረ መጀመሪያና መጨረሻ በሆነ ሁሉን በያዘና የሕይወትና የጥበብ ሁሉ ምንጭ በሆነ በእግዚአብሔር ስም በሕይወቴ ዓመታት መርዘም ከደረሰብኝ ሁሉ ትንሽ እጽፍአለሁ፡፡›
 •  የተወለደበትን ሥፍራ፣ ቤተሰብና ዓመት መግለጹ:- ‹ጥንት የተወለድኩት ከአክሱም ካህናት ነው፤ ነገር ግን እኔ በአክሱም አውራጃ ከልደተ ክርስቶስ በኋላ በ፲፭፺፪ ነሐሴ ፳፭ ቀን፣ በሦስተኛው ዓመተ መንግሥቱ ለአጼ ዘርአ ያዕቆብ ከአንድ ገበሬ ተወለድኁ፡፡›
 •  የክርስትና እና የዓለማዊ ስም ያለው መሆኑን መግለጹ፡- ከጥንት ጀምሮ የነበረ የኢትዮጵያውያን ልማድና ባህል ነው፡፡ ‹በክርስትና ጥምቀት ዘርአ ያዕቆብ ተብዬ ተሰየምኁ፤ ሰዎች ግን ወርቄ ይሉኛል፡፡› እነዚህ የቤተሰብ ማንነት፣ የትውልድ ሁኔታ፣ የሥፍራ፣ የዘመንና የድሪጊት ማስረጃዎች መሠረታዊና ማንም ሰው በቀላሉ ተቃውሞ የሚሽራቸው አይደሉም፡፡ ሌላውን ሁሉ ትተነው በዚህ የተጠቀሱት ማስረጃዎች ብቻ ለዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊነት በቂ ምስክር መሆን ይችላሉ፡- ሌላ ችግር ያለበት ምሁር ካልሆነ በስተቀር፡፡
 •  የትምህርቱ ሁኔታ፡- ዜማ፣ ቅኔና የመጽሐፍ ትርጓሜ መማሩና ጉባኤ ዘርግቶ ማስተማሩ፡- የኢትዮጵያውያን የትምህርት ሥርዓት ጠብቆ ትምህርት መቅሰሙንና የማስተማር ሥርዓቱም ባህሉን የተከተለ እንደነበር ይገልጻል፡፡ ይህንንም እንዲህ በማለት ገልጾታል፡- ‹ከአደግሁ በኋላም፣ ትምህርት እንድማር አባቴ ወደ ትምህር ቤት ሰደደኝ፡፡ መዝሙረ ዳዊትም ካነበብኩ በኋላ መምህሬ አባቴን ይህ ሕፃን ልጅህ ልቡናው የበራ በትምህርትም ታጋሽ ነውና ወደ ትምርህት ቤት ብትሰደው ሊቅና መምህር ይሆንኣል አለው፡፡ አባቴም ይህንን ሰምቶ ዜማ እንድማር ሰደደኝ፡፡ ነገር ግን ጉሮሮየ ሻካራ ነውና ድምፄ አይአምርም፡፡ ስለዚህ ለጓዶኞቼ መሣቂያና መዘባበቻ ሆንኳቸው፡፡ በዝያውም ፫ ወር ቆየኁ፡፡ ከይህም በልቤ እየአዘንኁ ተነሥቼ ሰዋሰውና ቅኔ እንድማር ወደ ሌላ አስተማሪ ሔድኁ፡፡ ከጓዶኞቼ ፈጥኜ እንድማር እግዚአብሔር ጥበቡን ሰጠኝ፡፡ ይህም መጀመሪያ ካሳዘነኝ ይልቅ አስደሰተኝ፡፡ በዝያውም ፬ ዓመት ነበርኁ፡፡ … ከይህም ተነሥቼ የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜ እንዲማር ሔድኁ፡፡ በይህች ትምህርትም ፲ ዓመት ነበርኁ፡፡ መጻሕፍትንም ፈረንጆች እንደ እሚተረጉሙኣቸው፣ እንደገናም የሃገራችን መምህራን እንደ ሚተረጉሙአቸው ተማርኁ፡፡ ትርጓሜአቸው ግን ብዙ ጊዜ ከልቦናዬ ጋር አልተስማማም፡፡ ነገር ግን ሐሣቤን ሁሉ በልቤ ሸሽጌ ዝም አልኁ፡፡ ፬ ዓመትም መጻሕፍት ማስተማርን ጀመርኁ፡፡› በዚህ ዓይነት የትምህርት ሥርዓትና ልማድ የተማረና ያስተማረ ምስዮን መኖሩን እስካሁን ማንም አልጻፈም፡- እኔም አላነበብኩም፡፡ ይህ የትምህርት ሥርዓት የኢትዮጵያ ቤ/ክን ሥርዓተ አስተምህሮና ከጥንት ጀምሮ በኢትዮጵያ ሊቃውንት የሚፈልቁበት የትምህርት ዘይቤ ነው፡፡ በዚህ ሥርዓት ተምሮና በዚህ መሠረትም ጉባዔ ዘርግቶ ያስትምር የነበረ መሆኑ ለዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊነት አስተማማኝ ምስክር ነው፡፡
 •  የእነ አልፎንሱ መምጣትን የገለጸበት ሁኔታ፤ የታሪኩ ክስተትም በኢትዮጵያውኛ ድምጸት ነው የተገለጸው፡- ‹በ፲፱ኛ ዓመተ መንግሥቱ ለአፄ ሱስንዮስ የፈረንጆች ተወላጅ አቡነ እልፎንስ መጣ፡፡ ከ፪ ዓመትም በኋላ ንጉሡ የፈረንጆችን ሃይማኖት ስለ ወደደ ከኢትዮጵያ አገር ሁሉ ትልቅ ስደት ሆነ፡፡›፤ የአልፎንሱን መምጣት ብቻ ሳይሆን ከሀገር መውጣቱንም ‹ከ፫ ዓመት በኋላ አልፎንሱ ወደ ሀገሩ ሔደ፡፡› በማለት ገልጽዋል፡፡
 • በአክሱም ሲያስተምር ያጋጠመው ችግርና መሰደዱ፡- ድሪጊቱንና የድርጊቱን ክንውንና ሁኔታ የሚገልጽ ነው፤ እንዲሁም ወደ ካቶሊኮች ከሀገር እንዲወጡ ከታወጀ በኋላ ተመልሶ እንዲያስተምር መጠየቁ፡- ኢትዮጵያዊነቱን በግልጽ የሚመሰክር ነው፡፡እኔም ከሀገሬ መጻሕፍት ስአስተምር ስአለኁ ከጓደኞቼ ብዙዎቹ ጠሉኝ፡፡… ብዙ ጊዜም ወደ ንጉሥ አሳጡኝና እግዚአብሔር ግን አዳነኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ከካህናተ አክሱም ፩ ጠላቴ ወልደ ዮሐንስ የተባለ የንጉሥ ወዳጁ ነውና የነገሥታት ፍቅር በሽንገላ ምላስ ስለሚገኝ ሔደ፡፡ ይህም ሸንጋይ ወደ ንጉሥ ገብቶ ስለ እኔ እንዲህ አለው፤ በእውነት ይህ ሰው ሕዝብን ያስታቸዋል፤ ስለ ሃይማኖታችን እንነሳና ንጉሥን እንግደለው፤ ፈረንጆችንም እናባርራቸው ይልኣል፡፡ ይህንንና እሚመስለውን ብዙ ሸነገለብኝ፡፡ እኔም ይህን ዓውቄ፣ በገናው ፈርቼ የነበረኝን ፫ ወቄት ወርቅና የእምጸልይበትንም መዝሙረ ዳዊት ይዤ በሌሊት ሸሸሁ፡፡ ወደ ተከዜ ፈሳሽ በረኃ ግድምም ገባኁ፡፡ በነገታው ራብ ያዘኝ፤ ከሃብታሞች ባለ አገሮች እንጀራ እንድለምንም እየፈራኁ ወጣኁ፡፡ ሰጡኝና በልቼ እየሮጥኁ ሔድኁ፡፡ እንደ ይሁ እያልኁ ብዙ ቀን አደረግኁ፡፡….…ከ፫ ዓመት በኋላ አልፎንሱ ወደ ሀገሩ ሔደ፡፡ ጠላቶቹ ሁሉ ተነሡ ወዳጆቹ ግን ከእርሱ ጋር ተሰደዱ፡፡ በዚያን ጊዜም የጥንትን ትምህርት አጥንተው የሚያስተምሩ ምህራን በሁሉም አገር ተፈለጉ፡፡ በአክሱም የአሉት ዘመዶቼም እንደ ቀድሞው በአክሱም ሆኜ ወደ ሊቅነቴ ተመልሼ መጻሕፍትን እንዳስተምር ፈለጉኝ፡፡ በአቡነ አልፎንስ ስለ ሆነው መሰደድ ፈርቼ የሸሸኁ ስለ መሰልኋቸውም ጠላቶችህ ጠፍተዋል ወዳጆችህ ድነዋልና ወደ እኛ ተመለስ ብለው መልክተኛ ላኩብኝ፡፡ እኔም ጠላት የለኝም፤ ይህ የእግዚአብሔር ሰው ጌታየ ሃብቱና ልጆቹ፣ ምሽቴም ከኣልሆኑ በቀር ወዳጅም የለኝም፤ ከቶም ልተዋቸው አልችልምና ለእኔም ወደ እናንተ መመለስ አይሆንልኝም፤ እናንተም በሰላም ኑሩ ብዬ መለስሁላቸው፡፡
 •  በዋሻ ውስጥ ለብቻው የቆየበት አኗኗርና ከኅብረተሰቡ ጋር የነበረው ግንኙነት- የኢትዮጵያዊያንን የችግር ጊዜ ማሰለፊያ ልምድ የተከተለ ነው፤ ነገር ግን ዘርአ ያዕቆብ ሌላ የውጭ ሀገር ሰው ቢሆን ኖሮ ወደ ሌሎች ሀገራት የመውጣት ልምድና እድል ስለሚኖረውና በቀላሉም በኅብረሰቡ አደጋ ይደርስብኛል ብሎ ስለሚሰጋ (መልኩና ቀለሙ ያጋልጠዋልና) ከኅብረተሰቡ ጋር በገበያ በመገናኘት በባህታዊ መልክ በበረሃ ዋሻ ውስጥ ለመኖር ቢያንስ በሥነ-ልቦናው ይቸገር ነበር፤ ባህታዊ በመምሰል መኖር ቢደፍርና ቢችል እንኳን ያጋጠመውን ችግር ወይም በነጭነቱ የደረሰበትን ሁኔታ የሚጠቁም ነገር ያስቀምጥልን ነበር፤ ምክንያቱም በዚያን ጊዜ በእነ አልፎንሱ ምክንያት የካቶሊኮች ጥላቻ ሕዝቡ ውስጥ ሰርጾ ነበርና፡፡ ከእሱ ይልቅ ዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያውያን ከካህኑና ከንጉሡ መልከጸዴቅ ጀምረው ባህላቸው ያደረጉትን ብህትውና ባያምንበትም ለጊዜ ማሳለፊያ መጠቀሙ ኢትዮጵያዊነቱን በማስረገጥ ይመሰክራል፤ ችግር ሲያጋጥም በበረሃና በጫካ ተደብቆ ማሳለፍም የሀገራችን ተለምዶ ነው፡፡ ሁኔታውን እንዲህ በማለት ገልጾታል፡፡…ወደሸዋ ግድም ስሔድ ሰው የሌለው በርኻ አገኘኁ፡፡ ከገደሉ በታች መልካም ዋሻ ነበረውና ሰው አይዓውቀኝ በዚሁ እኖራለሁ አልኁ፡፡ ሱስንዮስ እስኪሞት ምድረስ በዚያ ªዓመት ቆየሁ፡፡ ፩ ፩ ጊዜም ወደ ገበያ እየወጣኁ ወይም ወደ አማሮች አገር እሔድ ነበርኁ፡፡ ለአማራ ሰዎች የእምበላው እንዲሰጡኝ የእምለምን ባህታዊ መነኮስ እመስላቸው ነበርኁ፡፡ ነገር ግን ሰዎች ወደ የት (እንደምወጣና) እንደ ምገባ ኣያዓውቁም፡፡ በዋሻዬ ለብቻዬ በሆንኁ ጊዜም በመንግሥተ ሰማያት የምኖር መሰለኝ፤ ቁጥር የሌለው ክፋታቸውን ዓውቄ ከሰው ጋር መኖር ጠላሁ፡፡ ሌሊት መጥተው የበርኃ አራዊት እንደ አይበሉኝም በእሚከለክላቸው በድንጋይና በእሾኅ አጥር ዋሻን አሰናዳኁ፡፡ እሚፈልጉኝ ሰዎች ወደኔ ቢመጡም የምኣመልጥበት መውጫ አደረኩለት፡፡ በዝያውምበ ሰላምኖርኁ፡፡ በእሚሰማኝ በእግዚአብሔር ተስፋ አድርጌ በሙሉ ልቤ በመዝሙረ ዳዊት ጸለይኁ፡፡
 • እንፍራን የሚባለው ቦታ በመሔድ ሀብቱ ከሚባለው ሰው ጋር ተገናኝቶ ዳዊት እየጻፈ፣ ምሽት አግብቶ፣ እያስተማረ የመኖሩ ሁኔታ፡- አጠቃላይ የሚገልጸው የኢትዮጵያዊያንን ልማድና የአኗኗር ሁኔታ ነው፡፡ አንድ ቀን ወደ እንፍራንዝ አገር ወደ አንድ ጌታ ሰው የእግዚያብሔር ሀብት ነውና ሀብቱ ወደ ተባለ ደረስኩ በዚያውም አንድ ቀን አደርኩ፡፡ በማግስቱም አክሱም ወዳሉት ዘመዶቼ ደብዳቤ እንድልክ ከእርሱ ቀለምና ወረቀት ለመንኩት፡፡ ይህ ሰውም አንተ ጸሐፊ ነህ ወይ?› አለኝ አዎ ጸሐፊ ነኝአልሁት፡፡ ከእኔ ጋር ጥቂት ቀን ተቀምጠህ የዳዊት መዝሙርን ጻፍልኝና ዋጋህንም እሰጥሃለኁ› ብሎ ተናገረኝ፡፡እሺ!አልኩት፡፡ …በጥቂት ጊዜም ቀለምና ብራና አዘጋጅቼ አንድ የዳዊት መዝሙር ጻፍኩ፡፡ጽሕፈቴም ያማረች ናትና ጌታዬ ሀብቱና ሁሉም አይተዋት ተደነቁ፡፡ ጌታዬ ሀብቱም ደሞዜን አንድ መልካም ልብስ ሰጠኝ፤ ደግሞም ወልደ ሚካኤል የተባለ የጌታ የሀብቱ ልጅ ላባቴ እንደ ፃፍከው ለእኔም ፃፍልኝ አለኝና ፃፍኩለት፡፡ አንድ በሬና ሁለት ፍየሎችም ሰጠኝ፡፡ ከዚህ በኋላ ብዙዎች ወደ እኔ ዘንድ መጥተው ዳዊትና ሌሎች መጻሕፍትን፣ ደብዳቤዎችን አፃፉ፡፡ በዚያ አገር ካለ እኔ በቀር ሌላ ፀሐፊ አልነበረምና ልብስ፣ ፍየሎች፣ እህል፣ ጨውና ሌላም እነርሱን የመሳሰሉ ሰጡኝ፡፡ ለጌታ የሀብቱም አንድ ወልደገብርኤል ተሰማ የተባለና ሁለተኛ ወልደህይወት ምትኩ የተባሉ ሁለት ልጆች ነበሩት፡፡ አባታቸው ሀብቱም የሚበቃህን ምግብ እሰጥሃለሁና በእጅህ ፅፈህ የምታፈራውን ላንተ ይሆናልና፤ የዳዊትን ንባብ አስተምራቸው አለኝ፡፡አባቴ ሆይ ያዘዝከኝን ሁሉ አደርጋለሁ አልኩት፡፡ ነገር ግን ካንተ በቀር ዘመድ የለኝምና በአባቴና በእናቴ ዘመዶችም ፋንታ ዘመድ ሁነኝ አልኩት፡፡
 • የደቀመዘሙሩ የወልደ ሕይወት ምስክርነት፡-ይህን መጽሐፍ ወርቄ የተባለው ዘርአ ያዕቆብ በ፷፰ ዓመተ ሕይወቱ ፋሲለደስ ሙቶ ዮሓንስ በነገሠ ጻፈው፡፡ ዘርአ ያዕቆብ ይህ መጽሐፍ ከጻፈ በኋላ እግዚአብሔር ፈጣሪያችንን እየወደደና ቀንና ሌሊት እየአመሰገነው በጣም ከበርቴ ሁኖ የልጅ ልጅ አይቶ በመልካም ሽምግልና ፳፭ ዓመት ቆዬ፡፡ ልጁ ሃብቱም መድኃኒት ከተባለችው ምሽቱ ፭ ወንዶችና ፬ ሴቶች ወለደ፡፡ ወርቄ የተባለው የዘርአ ያዕቆብ ዕድሜው ሁሉ አለ ሕማም ፺፫ ዓመት ሆነ፡፡ በእግዚአብሔር ፈጣሪኣችን በአልለው ትልቅ ተስፋም ሞተ፡፡ ምሽቱም ከ፩ ዓመት በኋላ ሞተችና ከባልዋ ጋር ተቀበረች፡፡ …. እኔም ምትኩ የተባልኁ ወልደ ሕይወት የመጨረሻው መልካምነት እንድትዓውቁ ብዬ ከመምህሬ መጽሐፍ ላይ ይህን ትንሽ ጨመርኁ፡፡ ስለ ጥበቤ ግን እግዚአብሔር ያስታወቀኝና ዘርአ ያዕቆብም ፶፱ ዓመት ያስተማረኝ ይሀውና እኔም ለሁላቸው የኢትዮጵያ ልጆች ለዕውቀትና ተግሣፅ እንዲሆናቸው ይህ መጽሓፍ ጻፍኁ፡፡
 • ወዘተ….

እንዲሁም የሐሳቡና የዕይታው መለየት ካልሆነ በስተቀር የአጻጻፍ ስልቱና ልማዱ ከሌሎች ከገድላትና ከመዋዕላት አጻጻፎች የተለየ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያ ሊቃውንት የሚጽፉትን ነገር ከቅዱሳን መጻሕፍት ማጣቀሻዎች ጋር ማገናኘት ልማዳቸው ነው፤ ዘርአ ያዕቆብም ቢሆን ለምሳሌ የዳዊትን መዝሙር እየጠቀሰ መግለጹ፣ እንዲሁም ገድላትን ዜና መዋዕላትንም ሲጽፉ ቅኔን የማጎር ልማድ የላቸውም ዘርአ ያዕቆብ እንደዚሁ ነው የጻፈው፡፡ ስለሆነም ዘርአ ያዕቆብም የተቀኘውን ቅኔ በመጽሐፉ ውስጥ ባለማካተቱ ኢትዮጵያዊ አይደለህ ልንለው አይገባም፤ በሌላ በኩል በኢትዮጵያውያኑ ቅኔን ይቀኙታልና በጥልቀቱም ይደነቁበታል እንጂ ጽፎ የማስቀመጥ ልማድ የለም፡- አእምሮ እስካለ ድረስ ቅኔ ሊጠፋ አይችልም ስለዚህ ቅኔ ጽፎ ማጥናትና ሌሎች እንዲያጠኑትም ጽፎ ማስቀመጥ አዲስ ቅኔ እንዳያስቡ እንደማድረግ ይቆጠራል፡፡ ዘርአ ያዕቆብም የተቀኛቸውን ቅኔዎች በመጻፍ በፍልስፍናው ውስጥ ያላስቀመጣቸው በዚህ ልማድ የተነሣ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ቅኔ በመጽሐፉ ውስጥ አለማካተቱ ኢትዮጵያዊ አለመሆኑን አያሳይም ይልቅም ቅኔን ወዶት ለዓመታት የተማረው መሆኑ ኢትዮጵያዊነቱን ቁልጭ አድርጎ ያስረዳል፡፡

4)  4ኛው ጥያቄ ሰፊ ጥናትና ምርምርን የሚጠይቅ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም ዘርአ ያዕቆብ ያቀጣጠለው ዕይታ ለምን እስከ እዚህ ዘመን ድረስ ሳይቀጥል እንደቀረ ወይም የተቋረበትን ምክንያት በአግባቡ ለመግለጽ አግባባዊና አጥጋቢ መልስ ለመግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ ይሁንና የፍልስፍናው ዕይታ አለመቀጠሉና ሌሎችንም ቀስቅሶ አለመስፋፋቱ የዘርአ ያዕቆብን ፈላስፋነት የሚያስቀር ወይም አስተውሎቱን ከኢትዮጵያዊነት ውጭ የሚያወጣ አይደለም፡፡ ፍልስፍናው የሚመዘነውም በተያያዥነት በትምህርት መልክ እየተሰጠ እኛ ጋር በመድረሱ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ መቀጠል አለመቀጠል የተከታታይ ትውልዶቹ ኃላፊነትና ድርሻ እንጂ የፈላስፋው ዕይታ አካል አይደለም፤ ፍልስፍና በዚህ የምንመዝነው ከሆነ ታሪካዊ አስተምህሮ እንጂ አስተውሎታዊ ልዩ ዕይታ መሆኑን ማየት አልቻልንም፡፡  ዳግመኛም ቀጣይ ትውልዶች ስላሳደጉት ዕውቀቱ ፍልስፍና የሚሆን፤ ያበለጸገው ትውልድ ስላልተገኘ ፍልስፍናው ትርጉም የሚያጣ ከሆነም ፍልስፍናን ከዘገባ አቀራረብ የተለየ ዕውቀት አላደረግነውም ማለት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ፍልስፍናው አብቦ እንዳይቀጥል ያደረገው ሌላ ምክንያትም ሊኖር ይችላል፡፡

በሌላ በኩል ግን ‹የዘርአ ያዕቆብ ፍልስፍና ለምን ቀጣይነት አልኖረውም?› ቢባል ፍልስፍናው ብዙዎችን በመሳብ እንዲበለጽግ ከሌሎች የዕውቀት ዕይታዎች የተሻለና የመጠቀ ወይም ተጽዕኖ ፈጥሮ  ከሌሎች የትምህርት (የዕውቀት) ዘይቤዎች የሚመረጥና የሚጠቅም መሆኑ የታመነበት መሆን ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ በኢትዮጵያ ውስጥ የቅኔ፣ የአንድምታና የዜማ ስልቶች እየበለጸጉና እየተሻሻሉ መጥተዋል፡፡ ቅኔ ከቅ.ያሬድ፣ በ14ኛው መ/ክ ከነበረው ከነ ዮሐንስ ጎብላዊ፣ ከእነ ተዋናይ… ስልትና ደረጃ አድጎና ተሻሽሎ አሁን በሚገኝበት ሁኔታ ላይ ይገኛል፤ የመጽሐፍ ትርጓሜ ስልትም የላይ ቤትና የታች ቤት በሚል አተረጓጎም ተከፋፍሎ ብዙ ሊቃውንትን መሳብ፣ ማከራከርና መበልፀግ ችሏል፤የዜማ ትምህርትም በ6ኛው መ/ክ/ዘ ተጀምሮ ከእንቅስቃሴ ስልትና ሥርዓት ጋር እየበለጸገ መጥቷል፡፡ ይህ ከሆነ የዘርአ ያዕቆብ ፍልስፍናዊ አስተምህሮ በመሻሻል ቀጣይነት ሳይኖረው የቀረው ለምንድን ነው? ተብሎ ሲጠየቅ አንደኛው ምክንያት ሊሆን የሚችለው እንደሌላው ትምህርት ሊቃውንቱን መሳብ ስላልቻለ ወይም የሚሰጠው የዕውቀት ጥበብ ጥልቀትና አመራማሪነት በዚህ ዘመን በእኛ እንደሚገመተው ሳይሆን በዚያን ዘመን በሚመረመርበት የሃይማኖት ፅናዓትና የኅብራዊ አተረጓጎምና አረዳድ ምጥቀቱና ጥልቀቱ ሊያስደንቅ  ስላልቻለ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ቅኔን ለመማር አዳዲስ ትምህርት ቤቶችንና አስተማሪዎችን በመዘዋወር የሚፈልጉ ትጉኃን ተማሪዎችና ሊቃውንት የዘርአ ያዕቆብ ፍልስፍናን ካልናቁት በስተቀር ሳያውቁት አይቀሩም፤ የሚያውቁት ከነበረና ከሳባቸው ደግሞ ወይ በድገፋ ወይም በነቀፋ ቢያንስ ይቀኙበት ቢቻል ደግሞ ትምህርቱን በመገልበጥ ያስፋፉት ነበር፤ ያ አልሆነም፡- የደቂቀ እስጢፋን ያህል እንኳን ተጽዕኖ ማሳረፍ አልቻለም፡፡ በዚህ መልክ በመሳብ በልጦ ካልተገኘም፣ በዚህ ምክንያት ብቻ ቀጣይነት ኖሮት ትምህርቱ ላይስፋፋ ይችላል፤ ማለትም ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ከዚህ የበለጡ አስደናቂ ተግባራትና አስተውሎቶች ያሉባቸው የቁጥር፣ የመጻሕፍትና የቅኔ ትምህርቶች አሏቸውና የዘርአ ያዕቆብን ፍልስፍና ‹ጡጥም ከፈስ ተቆጠረች› ብለው በመናቅ ትተውት ይሆናል፡፡

እንዲሁም የዘርአ ያዕቆብ ፍልስፍና የኢትዮጵያውያን የትምህርት ሥርዓት አካል አይደለም፤ ይህ ከሆነም ከመጀመሪያው ምክንያት ጋር ተያይዞ ቀጣይነት ሊኖረው የሚችልበት ዕድል ውስን ይሆናል፡፡ ደቀመዝሙሩ ወልደ ሕይወትም ቢሆን ጉባኤ ዘርግቶ ፍልስፍና ማስተማሩን አልነገረንም፤ ይጠቅማል የሚለውን ምክርና ዕዝናት ለኢትዮጵያውያን ወገኖች ነው ጽፎ ያስተላለፈው፤ ጉባኤ ተዘርግቶለት ትምህርቱ ካልተሰጠም በመቀጠል ደቂቃነ መዘምራንን አፍርቶ ከዚህ ዘመን ለመድረስ ይቸግረዋል፡፡ ይህ ግን የዘርአ ያዕቆብንና የደቀ መዝሙሩን የወልደ ሕይወትን ያህል ሌሎች ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት ማስተዋል ወይም መፈላሰፍ ሳይችሉ ቀርተው ሳይሆን የአስተሳሰብ አቅጣጫ፣ የጠቀሜታ ሁኔታ፣ የኅብራዊ ዕውቀት  ፍልስፍና ልማድና የአስተምህሮውን ዕድል የማግኘት ችግር ይዟቸው ይሆናል- በዘርአ ያዕቆብ ልማድ ያልቀጠሉት፡፡ ይህንን ለጠቅላላ ግንዛቤና ማነጻጸሪያ ብንልም ‹ፍልስፍናው ቀጣይነት ሳይኖረው ስለቀረ ኢትዮጵያውያ ፍልስፍናን ማሰብ ስለማይችሉ እሱም ኢትዮጵያዊ ሊሆን አይችልም› የሚለው ሙግት በራሱ የአስተሳሰብ ችግር አለበት፡፡

5)  5ኛው ጥያቄ የአመለካከት ችግር ስለሆነ አስተያየት መስጠትም አያስፈልግም ነበር፡፡ ሆኖም የእዚህ አመለካት መነሻውና ምክንያቱ ምን እንደሆነ ማየት ጠቀሜታ ስለሚኖረውና ለእነ ኮንቲ ሮስኒ ‹ፍልስፍናው የኢትዮጵያዊ ሊሆን አይችልም› የሚል ክርክር እስከ መፍጠር ያደረሰው መሠረት ይህ አመለካከት ስለሆነ በቁንጽሉ ማየት አይከፋም፡፡ የዚህ አስተሳሰብ መነሻው አውሮፓውያን አፍሪካውያንን ወይም ጥቁሮችን የሚመለከቱበት መነጽር ዓይናቸውን ጨለማ አልብሶ ስለሚጋርዳቸው ነው፡፡ በዚህ ግርዶሽ የተነሳም ጥቁር የሚያስብ ሙሉ ሰው አይደለም የሚል ቅድመ ግምት በአፍሪካ ውስጥ የተሠሩትን መልካም ሥራዎች የሚሲዮን ወይም አሳሽ ከነበረ አውሮፓዊ ጋር መለጠፍና ማያያዝ፤ ወይም ታሪኩንና ዕይታውን አስቀይሶ የአውሮፓውያን ዕይታ አካልና ውጤት እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ዋና ዓላማቸው ነው፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ መታየት ያለበት የግርዶሹ ምክንያት፤ ከዚያም የዚህ የመነጽር ግርዶሽ ያመጣው ተጽዕኖ ነው፤ ይህንን ግን ማንም የእነ ካንትንና የእነ ሔግልን የዘረኝነት ጽሑፍ የተመለከተ በቀላሉ ስለሚረዳው እዚህ ማተቱ አስፈላጊ አይሆንም፡፡

ሌላው ምክንያት ዕውቀትን የቅርብ ዘመናት የሰው ልጅ የማሰብ ችሎታ መጨመር ያመጣው አድርጎ መገመትም የችግሩ አካል ይመስላል፤ ምክንያቱም ‹በ17ኛው መ/ክ/ዘ የነበረ ኢትዮጵያዊ› እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብን ማፍለቅ አይችልም ብሎ መገመት ‹በዚያን ዘመን አእምሮው ይህንን አስተሳሰብ ለማፍለቅ ብቁ አልነበረም› ማለት ይመስላል፡፡ ይህ ደግሞ ከዚያ በፊት የነበሩትን አስደናቂ የኢትዮጵያውያን ጥበባት ያለ አስተውሎት የተገኙ ያስመስላል፤ የሰው ልጆች ቀድመው የሠሯቸውን አስደናቂ የፍልስፍና ውጤቶች ሁሉ ትርጉም የሚያሳጣ ነው፡፡ በሌላ በኩል በዚያን ዘመን አካባቢ የነበሩ የአውሮፓ ጠበብት ከዘርአ ያዕቆብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የፍልስፍና እሳቤን አፍልቀው መጻፍ ከቻሉ እሱ የማይችልበት ምክንያት ምንድነው? ኢትዮጵያዊ ወይም ጥቁር ስለሆነ ነው በዚያን ጊዜ የዚህን ዓይነት የፍልስፍና እሳቤን ማፍለቅ የሚያቅተው? …

ምናልባት ‹በዚያን ዘመን ከሃይማኖት ትምህርት ውጭ የሚታይ ዕውቀት እንደ መሳሳት ስለሚቆጠር ወይም መናፍቅ ስለሚያስብል ከዚህ አስተሳሰብ በተለየ የእግዚአብሔርን መኖር እስከ መጠየቅ ለመድረስ አይቻልም› ተብሎ ሊሆን ይችላል ብለን ብንወስደው እንኳን ትችቱ ሙሉ አይሆንም፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ዘርአ ያቆብ በመጽሐፉ ያሠፈረውን ዕይታ እንዴት ሊያፈልቅ እንደቻለ ምክንያቱን ከታሪክና ከማኅበራዊ ችግሮች አኳያ አብራርቶ ገልጽዋል፤ ሁለተኛም የእኛን ፍላጎትና ምኞት ትክክል እውነት ለማድረግ ወይም ለማስመሰል የሚገኘውን ማስረጃ ተቃርነን መገመት ስህተት ነው (የተጻፈው በዚያን ዘመን መሆኑን ይገልጻልና)፤ ሦስተኛ በሃይማኖት ትምህርት ዕውቀት ውስጥ አድጎና ያም አስተሳሰብ እንደነበረ ሆኖ  እያለ የተለየና ወጣ ያለ እሳቤን ማየትና አቅርቦም መከራከር የተለመደ የሰው ልጅ የታሪኩ አካል እንጂ ልዩ ነገር አይደለም፤ ዘርአ ያዕቆብ ለምን የተለየ ተደርጎ ይወሰዳል?፡- ለዚህም ሶቅራጥስን፣ ማኬቢሊን፣ ሌሎችንም በምሳሌነት ማየት ይቻላል፡- አራተኛ ኢትዮጵያዊያን ከሃይማኖት ትምህርት ውጭ ምንም ዕውቀት እንዳልነበራቸው አድርጎ የሚረዳት ችግር አለበት፤ አምስተኛ ይህ አስተሳሰብ በምዕራባዊያን ፈላስፎች የተለመደና የሚታወቅ ሆኖ እያለ ለኢትዮጵያዊያን ሲሆን ለምን እንደተለየና የማይቻል መስሎ ሊቀርብ ቻለ? በጥቅሉ ግን የሰው ልጅ በአዝጋሚ ለውጥ መልክ ካለማወቅ ወደ ማወቅና መፈላሰፍ አድጓል የሚለው አስተሳሰብ የችግሩ መሠረት ይመስላል፤ ይህ ራሱን የቻለ ሌላ መከራከሪያ ስለሆነ እንለፈው እንጂ የሰው ልጅ ዕውቀት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል የሚለው የዝግመተ ለውጠኞች ምኞትና ግምት ትክክል አይደለም፡፡ በጥቅሉ ከዚህ በላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች የተነሣ ዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ አይደለም በማለት የሚከራከሩ አካላት ምንም ማስረጃና አጥጋቢ የሆነ ምክንያት ሳይኖራቸው እንደሚፈነጩ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ በዘርአ ያቆብ የሐተታ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙት ማስረጃዎች እንደ ቀላል የሚታዩ አይደሉም፤ የሥፍራ፣ የጊዜ፣ የድርጊትና የአስተሳሰብ ሁኔታንና ልምድን የሚገልጹ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ ውድቅ ሊሆኑ የሚችሉት የእነሱን እውነትነት የሚያፋልሱ ወይም የሚነቅፉ ማስረጃዎች ወይም አሳማኝ ምስክሮች ሲገኙ ብቻ ነው፡፡ ያለበለዚያ የሚኖረው ክርክር ‹በዚያን ዘመን በአካል ተከስቼ ካላየሁ› አላምንም ወይም ምንም ነገር አልቀበልም ወይም ኢትዮጵያዊ ሰው ጥቁር ስለሆነ የተለየ ሐሣብ ማፍለቅና የተለየ አስተሳሰብ ሊኖረው አይችልም ማለት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ሲታይ ከላይ የቀረቡት ነቀፌታዎች ወይም ተቃውሞዎች እንጂ ‹ዘርአ ያዕቆብ ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ አለመሆኑን› አምነን የሌላ ሀገር ፈላስፋ የሆነ ወይም ፈላስፋ ያልሆነ ተራ ሰው መሆኑን እንድናምን የሚያደርጉ ማስረጃዎች አይደሉም፡፡ ምክንያቱም ተቀበልነውም ካድነውም የዘርአ ያዕቆብ ሐተታ መሆኑን የሚገልጽ በግዕዝ ተጽፎ የተገኘ መጽሐፍ አለ፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የተመዘገበው ታሪክ ትክክል ያልሆነ ከሆነ (እና!ዘርአ ያዕቆብም ኢትዮጵያዊ አይደለም ካልን)ጽሕፉ የማን ነው? በመጽሐፉ የተመዘገበውን ክደን ትክክል አለመሆኑን ልናምን የቻልነውስ ምን ዓይነት አሳማኝና አስተማማኝ ማስረጃ ማግኘት ችለን ነው? የዚህ መጽሐፍ ማስረጃ ሐሰት ከሆነስ አብዛኞቹ የታሪክ ማስረጃዎች ተቀባይነት እንዴት ሊኖራቸው ይችላል? … ጥያቄውን በሌላ አንግልም እንመልከተው፡፡

የመጽሐፉ ማስረጃዎች ተጥለውና ተነቅፈው ከዚያ ውጭ ያሉ ግምቶች እንደ ዋና ማስረጃነት በመወሰድ ዋና መሟገቻ የሆኑበት ምክንያት ምንድን ነው? ለመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጡት ሚሲዮኖች ወይም ሀገር አሳሾች መካከል እንኳን በኢትዮጵያ ቋንቋ (በግዕዝ) በሀገሩ ቋንቋ የፍልስፍና መጽሐፍ አዘጋጅቶ ያሳተመ አለ? አለ ከተባለ ምን የሚል ወጥ የፍልስፍና መጽሐፍ እንደተጻፈ መግልጽ ግድ ነው፤ በፍልስፍና መጽሐፍነቱ የተሠጠው ልዩ ዕይታም እንዲሁ መታየት አለበት፡፡ በየለም ከተስማማን ግን በሀገሩ ቋንቋ የፍልስፍና (ዕይታ ያለው) መጽሐፍ ሳያዘጋጅ ባልተረዳውና መጽሐፉን ብዙ የአውሮፓውያን ሊቃውንት ሊያነቡለትና ሊጠቀሙበት በማይችል በግዕዝ ቋንቋ የሚጽፈት ምክንያት ምንድን ነው?  ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት እንዲያነቡለት ነው እንዳይባል ወይ የአውሮፓውያኑን ፍልስፍና ገልብጦ አልጻፈ ወይም የአውሮፓን አስተምሮ ከኢትዮጰያ የትምህርት ልምድ ጋር በማነጻጸር አልነቀፈ፣ አላወደሰ ይህንን ዓይነት መጽሐፍ የጻፈበት ምክንያት ምንድን ነው? ምናልባት የፍልስፍና አስተሳሰብን ለኢትዮጵያዊን ለማስተማር ብሎ ይሆን? ሊሆን ይችላል ከተባለ ለምን ታዲያ ከዚህ ይልቅ የፍልስፍና ይዘትን የያዘና የፈላስፎችን ፍልስፍና ምንነት የሚገልጽ መጽሐፍ አላዘጋጀም?…  ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱበት ይችላሉ፡፡

በጥቅሉ ከላይ የተጠቀሱት የተቃውሞ ነጥቦች አንድ የጋራ መነሻ ያላቸው ናቸው፡- ይኽውም ‹በመጽሐፉ የተመዘገበው ማስረጃ ሐሰት ነው› የሚል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለት የአመለካከት መሠረቶች ይኖሩታል፤ አንደኛው ‹አፍሪካ ውስጥ ምክንያታዊ አስተሳሰብ የለም› የሚል የጥቁር ማሰብ አይችልም ቅኝት ተጽዕኖ ሲሆን ሁለተኛውና ከአንደኛው ጋር የተያያው ደግሞ ሁሉም ነገር ከውጭ መጥቷል እንጂ ከኢትዮጵያ ሊፈልቅ የሚችል አዲስ የዕውቀት መንፈስ አይገኝም የሚል የአስተሳሰብ ዥረት (ተፅዕኖ) ያመጣው ጣጣ ይመስላል፡፡ ያ ካልሆነ ግን ፈላስፋነቱ ይቅር ብንል እነኳ ዘርአ ያዕቆብ ‹ኢትዮጵያዊ አይደለም› ለማለት የሚያሥችል እሱ በጠቀሳቸው ሥፍራዎች የተከናወነ የታሪክ ጥናት ማስረጃ የለም፤ በጥናት አስደግፎ ውድቅ የሚያደርግ ማስረጃ በምክንያት በማቅረብ ሳያረጋግጡም የነበረውን ሐቅ መካድ አግባብ አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል በተለያዩ ሊቃውንት እንደቀረበውም የዘርአ ያቆብ ፈላስፋነትም ቢሆን በምዕራባዊያን ፍልስፍና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ በመፍጠር ከሚታወቁት ከደካርትና ከአማኑዔል ካንት ጋር በምክንያታዊ ዕይታው፣ በተጠየቅ ስልቱና ባነሳቸው ነጥቦች ይቀራረባል፡

የዘርአ ያዕቆብ ፍልስፍና ምን ይመስላል?

ይቆየን!

 
 
%d bloggers like this: