RSS

Monthly Archives: March 2013

እውን አንተን ወለደ?

 

ለተረት ተረትህ ድርጎ፣ መሞገትን ባትወድም፣

እኔ ከአንተ መልስ እሻለሁ፣ መቸም ላንተ ወሬ አይገድም፣

አስጠብቦ አያስጨንቅም፣

ከጀርባ ላብ አያፈልቅም።

 

መልስ ቢጠየፍ ህሊናህ፣ ፌዘኝነትን ወዶ፣

ከአባትህ የስልጣኔ ሀሁ፣ አቡጊዳህ ተወላግዶ፣

ከልጅህ ማነን? ጥያቄ ምላሽህ ተካክዶ፣

ቢሆንም ያለኽው ቅሉ፣ ያባትክን አጽም አስታመህ፣

ባባትህ ብርሃን ጨልመህ፣

በስልጣኔው ሰይጥነህ፣

ቢሆንም ያለኸው ቅሉ፣

አበው መጠየቅ አይከብድም አሉ፣

እስቲ ልጠይቅህ ያንተ ማነው አባትህ?

  Read the rest of this entry »

Advertisements
 

የአውራምባ ማኅበረሰብ መሥራች ዙምራ ፈላስፋ ወይስ ተራ ሰው?

ባለቅኔው ቀኝ ጌታ የፍታሔ ንጉሤ ‹የንግግር ውበቱ ማሳጠር ነው› እንዳለው፤ ወይም አበው ‹እንደወርቅ አንክብሎ፣ እንደሸማጠቅልሎ› እንደሚሉት በአጭር ዐ.ነገር ከሽነውና አስውበው አስደናቂ የፍልስፍና ዕይታዎችን የሚናገሩና አመክንዮአዊ በሆነ አቀራረባቸው የሚያስገረሙ ብልሆችና አስተዋይ ሰዎች በኢትዮጵያ ነበሩ፤ አሉም፡፡  ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው ያልተማረው የዘመናችንና የሀገራችን ድንቅ ፈላስፋ የአውራ አምባው ማኅበረሰብ መሥራችና ቀራጭ የዙምራ ዕይታና አቀራረብ ነው፡፡ ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ‹ፍልስፍና ፪› በሚል መጽሐፉ ‹በሕይወት፣ በሰው ልጆችና በእግዚአብሔር መሃከል ያሉ ጥያቄዎችን ማንሳት የጀመርከው መቼ ነው?› ብሎ ለጠየቀው ጥያቄ የሰጠውን መልስ በምሳሌነት ወስዶ መመልከት የዙምራን ማንነትና የአስተውሎቱን ምጥቀት ለመገምገም ይረዳል፡፡ ዙምራ ለተጠየቀው ጥያቄ እንዲህ ነበር የመለሰው፡-

‹‹እኔ ራሴ አላውቀውም፡፡ ራሴን ሳውቅ ጀምሮ እጠይቃለሁ፡፡ መጠየቄ ተቋርጦም አያውቅ፡፡ እናቴ ስትናገር ‹ስለ ሰው ልጆች ማኅበራዊ ሕይወት መጠየቅ የጀመረው በአራት ዓመቱ ነው፤ስለ እምነት የጠየቀው ደግሞ በሁለት ዓመቱ ነው› ትላለች፡፡ እንግዲህ ከእናቴ የሰማሁትን ነው የምናገር፡፡ የእኔ ወላጆች እምነታቻው እስልምና ነው፡፡ ክርስቲያን ዘመዶች አሏቸው፡፡ አንድ መንደር ነው የተቀመጡ፡፡ ቡና በአንድ ይጠጣሉ፤ ሥራ በወንፈል አብረው ይሠራሉ፡፡ እኛ ልጆቹም አብረን እንጫወታለን፡፡ አሁንም እናቴ ስትናገር ‹ተወልዶ በስድስት ወሩ ቆሞ ሄዷል፤ በሁለት ዓመቱ ደግሞ ስለ እምነት መጠየቅ ጀምሯል› ትላለች፡፡ ልለይበት የቻልኩትን ልናገርና በሁለት ዓመቴ ክርስቲያን ዘመዶቼ ቤት ሄጃለሁ፡፡ ተዚያ ስሄድ ወላጆቻቸው የሉም፡፡ ልጆቹ ምግብ ይበላሉ፡፡ ምግቡ የሥጋ ምግብ ነው፡፡ እኔን ሙስሊም ነህ ብለውኛል፡፡ እነሱ ክርስቲያን ናቸው ብለዋል፡፡ ብለዋል ነው የምል፡፡ ወላጆቻቸው ቢኖሩ የሥጋ ምግብ ስለሆነ፤ አይሰጡኝም፡፡ ልጆቹ ያው እንደኔው ናቸውና ሰጡኝ፡፡ ምግቡ ስለጣመኝ ግጥም አድርጌ በልቼ ትራፊዬን ተቤቴ! እናቴ ሥጋውን ስታይ፡

‹እሱን ሥጋ ተምን አገኘኸው?› ትለኛለች፡፡

‹እነ አተዋ ልጆቹ ሰጥተውኝ ነው› እላለሁ እንደኔው ይጥማታል ብዬ፡፡

‹የክርስቲያን ሥጋ በላህ?› ትልና ትቆጣለች፡፡ ያ ብቻ አልበቃትም፡፡ ሥጋዋ እየጣመችኝ በእጇም እንዳትይዘው ተጠይፋ በእንጨት ይዛ አውጥታ ትጥለዋለች፡፡ ዓይኔ ሥጋዋ ላይ ቀርቷል፡፡ የክርስቲያን ሥጋ ነክቼ ዕቃ እንዳልነካበት እጄን ታጥባለች፡፡ እየታጠብኩ ሥጋዬ መውደቁ ስለቆጨኝ፤

‹እማዬ ሥጋዬን የቀማሽኝ ለምን ነው?› ብዬ ጠየቅኳት፡፡ (ያው እንግዲህ እሷ የነገረችኝን ነው የምነግርህ)

‹የክርስቲያን ሥጋ ሆኖ ነው› ትላለች፡፡

‹ከክርስቲያኖች ቤት ስለታረደ ነውዪ ሥጋውማ የበግ ነው› አልኳት፡፡

‹ሥጋው የክርስቲያን ነው›

‹ክርስቲያን ማለት ምንድነው?›

‹ሰው› ትላለች፡፡

‹ዛዲያ እኛ ምንድነን ሰው አደለንም ማለት ነው?›

‹እኛማ ሙስሊሞች ነን›

‹ሙስሊም ሰው አይደለም?›

‹ነው እንጂ፡፡ ሰው ነው›

አሁን ሁላችንም ሰው ሁነናል ማለት ነው፡፡

‹ዛዲያ እኔስ ሰው የበላውን አይደለ የበላሁ? ለምን ሥጋዬን ቀማሽኝ?› አልኳት፡፡

‹አንተ! የክርስቲያን ሥጋ አይበላም› ትላለች ቆጣ ብላ፡፡

ሃሳቤን ቀየርኩና እንደገና ጠየቅኳት፡፡

‹ክርስቲያን የምን ሥጋ ነው የሚበላ?›

‹የከብት›

‹ሙስሊምሰ የምን ሥጋ ነው የሚበላ?›

‹የከብት›

‹ሁላችንም እኩል ሰው ተሆንን፤ ሁላችንም የከብት ሥጋ ተበላን ዛዲያ ለምን ቀማሽኝ› እናቴ መልስ የላትም፡፡

በስንት ዓመቴ እንደሆነ ባላውቅም በሰው ልጅ ፍጥረት ላይ ሌላም ጥያቄ አንስቻለሁ፡፡

‹መጀመሪያ ክርስቲያን ሲፈጠር ተምን ተፈጠረ?›

‹ተአዳምና ተሄዋን›

‹ሙስሊምስ?›

‹ተአደምና ተሃዋ› ይሉኛል፡፡

‹ሁለት ሴቶችን ሁለት ወንዶች ናቸው ማለት ነው መጀመሪያ ሰው ሲፈጠር የተፈጠሩ?›

‹አይደለም፡፡ የሀገር ቋንቋ ነው ባጠራር አራት ቢመስሉም ሁለት ናቸው› አሉኝ፡፡

ክርስቲያኖች እግዜር፤ ሙስሊሞች ደሞ አላህ ሲሉ እሰማለሁ፡፡

‹አላህና እግዚአብሔር ሆነው እየተማከሩ በጋራ ይቺን ዓለምና እኛን የፈጠሩ?› እላለሁ፡፡

‹ፈጣሪማ አንድ ነው›

‹እንግዳው ስሙ ለምን ሁለት ሆነ?›

‹እሱ ያገር ቋንቋ ነውእንጂ ፈጣሪ አንድ ነው› ይላሉ፡፡ ሁላቸወም በአንድነቱ ይስማማሉ፤ የማይስማሙት በስሙ ነው፡፡

ፈጣሪ አንድ ተሆነ፤ እኛ ሁላችን የአዳምና ሄዋን ዝርያዎች ተሆንን እምነት የሚገለጠው በምንድነው? እምነት ጥሩ ማሰብ፤ ጥሩ መሥራት ነው፡፡ እኛ የምናምን ፈጣሪ አንድ ነው፤ እንደ ዳቦ አይቆረስም ብለን ነው፡፡ ሰዎች ግን ስሙን እየሸነሸኑት እምነቶች ተሺህ በላይ ደርሰዋል፡፡

እያደግሁ ስሄድ ሃሳቤን የሚደግፉ አጋጥመውኛል፡፡ ‹ሃሳብህ ጥሩ ነው፡፡ ግን ወይ መስግድ፤ ወይ በተስኪያን ቢኖርህ ይሉኛል፡፡ በተስኪያኑ የሚሠራው፤ መስጊዱ የሚሠራው በሰው ነው፡፡ ራሴ በምሠራው ነገር አልተቃወምኩትም፡፡

‹መስጊዱን ወይም በተስኪያኑን ብሠራለት ፈጣሪ የት ቦታ ነው ያለ?› አልኩ፡፡
‹እሱማ የትም ቦታ ነው ያለ፡፡ በሁሉም ቦታ ፈጣሪ አለ› ይሉኛል፡፡

ቤት አልቸገረውም ማለት ነው፡፡ እሱ በሁሉም ቦታ ላይ እየተገኘ እኔ አንድ ቦታ ላይ ሠርቼ ስገባ እከፍተዋለሁ፤ ስወጣ እዘገዋለሁ፡፡ ስወጣ የምዘጋውን ቤት ሠርቼ ‹ና ተዚህ ግባልኝ› ልለው ህሊናዬ አይፈቅድም፡፡ የእሱ ፈቅዶ ይሆናል፡፡ እሱ እኔን ይቆጣጠራል እንጂ እኔ አልቆጣጠረውም፡፡ ና ግባ ውጣ ልለው አልችልም፡፡ ይልቁንስ የእሱ ህንጣ እኛ አይደለንም ወይ? የፈጣሪ ህንጣ እኛ ነን፤ የፈጣሪ በተስኪያን እኛ ነን፡፡ ሌላም የለው፡፡ በተስኪያንና መስጊድ ሠርተን ‹ሂድ ተዚያ ውስጥ ግባ› ተምንለው ለምን የእሱ በተስኪያንና መስጊድ ሁነን አንቀጥልም? ለምን እንደሆነ ባላውቅም ሰዎች ስሙንና ስርፋውን አለያይተው በመጥራት መለያየትን ነው የሚመርጡት፡፡››

የዙምራ ትችት ልክም ይሁን ስህተት ሳይማር የተጠቀመውን የአቀራረብ ስልትና የዕይታውን ምጥቀት ስናስተውል እንደነቃለን፤ ያልተማሩ ለምንላቸው ለኢትዮጵያዊያን አስተዋይ ሰዎች ከእሱ የበለጠ ምሳሌም መፈለግ አስፈላጊ አይመስለም፤ የዙምራ አቀራረብም የሀገራችን የተጠየቅ ልጠየቅ የክርክር ሥርዓትን የተከተለ ይመስላል፤ የተጠየቅ ልጠየቅ ሙግት ደግሞ አንዱ የሀገራን የክርክር ባህል የነበረ ነው (ከሶቅራጥስ የእሰጥ አገባ የክርክር ስልት ጋርም ልናመሳስለው እንችላለን)፡፡ የመከራከሪያ ነጥቡ ደግሞ ከፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ጋር ተመሳሳይ ነው፤ የሚከራከረው ግን የዘርዓ ያዕቆብን ፍልስፍና ዐይቶና ዐውቆ ሳይሆን በልቦናው ያስተዋለውን መዝኖ ነው፡፡ ይህ የዙምራ አስተውሎታዊ ክርክርም የአበውን ባህላዊ ፍልስፍና ዘመናችን ላይ ሆነን እንድናይ የሚያደርገን ይመስለኛል፡፡ ከላይ ካነበብነው ተነሥተን እስቲ ራሳችንን እንጠይቅ ዙምራ የሀጋራችን ፈላስፋ ወይስ ተራ የማኅበረሰብ መሪ? ሳናውቃቸው የቀረን እንደዙምራ ዓይነት ሰዎችስ በየአካባቢው በተለያዩ ዘመናት አልነበሩም? በቅኔና በመጻሕፍት አንድምታ በዕውቀት የበሰሉት ሊቃውንትስ እንዴት ይታያሉ? በየገዳማቱ በተመስጦ የሚኖሩትስ አይፈላሰፉ ይሆን?…

 
 

የኢትዮጵያ ጀግኖች እንዲህ ተወድሰው ነበር፤ ዛሬስ?

 

 አጥንቱን ልልቀመው

አጥንቱን ልልቀመው መቃብር ቆፍሬ፣

ጎበናን ተሸዋ አሉላን ተትግሬ፣

ስመኝ አድሬያለሁ ትንትና ዛሬ፣

ጎበናን ለጥይት አሉላን ለጭሬ፡፡

  Read the rest of this entry »

 

የክሽፈት እንጉርጉሮ፣ ታሪክ ላይ ተሸንቅሮ!

በካሣሁን ዓለሙ

‹አንድ ሰው በአደባባይ ሲናገርም ሆነ ጽሑፍ አሳትሞ ሲያሰራጭ ራሱን አጋልጦአል፤ የተናገረው ወይም የጻፈው መቶ በመቶ ያህል በራሱ ጉዳይ ላይ ብቻ ከሆነ፣ የመተቸት ወይም ሐሳብ የመስጠት ግደታ የለብንም፤ ነገር ግን የተናገረው ወይም  የጻፈው በአገርና በሕዝብ ጉዳይ ላይ ከሆነ፣ የዚያ አገር ዜጋ ሁሉ በጉዳዩ ውስጥ የመሳተፍና ሐሳቡን በሙሉ ነጻነት የመስጠት መብት አለው፡፡›

(ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም፣ መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ፣ ገጽ78-79)

mesfin b

1. መንደርደሪያ

‹ክሽፈት! ክሽፈት!› ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የሚቀነቀን እንጉርጉሮ ነው፤ በብሎጎች፣ በማኅበራዊ ድራተ-ገጾች፣ በእርስ በርስ ጨዋታዎች…. በጭቅጭቅ ወይም በክርክር መልክ ይዘመራል፡፡ የዚህ እንጉርጉሮ መነሻ ደግሞ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ‹መክሸፍ እንደኢትዮጵያ ታሪክ› በሚል ርዕስ በቅርቡ ያሳተሙት መጽሐፍ ነው፡፡ እንደኔ ዕይታ በዚህ ዓመት በአማርኛ ከታተሙ መጻሕፍት መካከልም እንደዚህ መጽሐፍ አመራማሪ፣ አወያይና አከራከሪ መጽሐፍ የተገኘ አይመስለኝም፤ ለዚህም የመጽሐፉ ርእሰ ክብደት፣ የአቀራረቡ ምርምራዊ ሙግት መሆን፣ ታሪክን ከፍልስፍናውና ከኩነቶቹ በመመሥረት ያስቀመጠበት ዐውዱ ፣ ታዋቂ የታሪክ ሊቃውንት ሥራዎችን ወስዶ በቀጥታ መተቸቱ፣ በኢትዮጵያ ታሪክና ነባራዊ ሁኔታ ዙሪያ በቁጭት አቀራረብ መቃኘቱ፣ ጸሐፊው ቀድሞውንም ተፅዕኖ ፈጣሪ የአደባባይ ደፋር ምሁር መሆናቸው፣… መጽሐፉን ልዩና አነጋጋሪ ያደረገው ይመስለኛል፡፡ የሚያሳድረው ተጽዕኖም ከፍተኛ መሆኑ በግልፅ እየታየ ነው፡፡

በዚህ መልክ ተፅዕኖው ከፍተኛ የሆነ መጽሐፍ ከሆነም መልካም ጎኖቹ እንዳሉ ሆነው አጠያያቂነትና አከራካሪነቱም በአግባቡ መመርመር ይኖርበታል ባይ ነኝ፤ ስለሆነም በመጽሐፉ ርዕስ፣ ይዘትና መዋቅር ዙሪያ መወያየት፣ መከራከርና መነጋገር ያስፈልጋል፤ የተጀመረውም ዝማሬያዊ ውዳሴም ሆነ ትችታዊ ነቀፋው መቀጠሉ የውይይት ባህልን ያዳብራል፤ ጠቃሚም የሚሆነው በትችት በመቃኘት ሲከራከሩበት ነው፡፡ በራሴ ግን የመሰለኝን አስተያያትና ትችት ላቅርብ ብዬ ይችን ጽሑፍ አዘጋጀሁ፤ ምንም እንኳን አስተያየቴ በሌሎች ተችዎች አልተነካም፤ አልተሞገተበትም ባልልም፤ ከኢትዮጵያ የሥልጣኔ ደረጃና የታሪክ አተያይ አንጻር ብዙም የታየ አልመሰለኝም፡፡ ስለዚህ መጽሐፉ ላይ በግሌ የማልስማማቸው የአቀራረብ፣ የመነሻና የአተያይ አስተያየቶች ጠቋቁሜያሉ፤ አቀራረቤም ትችታዊ ስለሆነ በዚህ ስሜት እንዲታይ ታዳሚዎችን አደራ እላለሁ፡፡ Read the rest of this entry »

 

አድዋ ለኢትዮጵያ ምኗ ነው?

268135_10200223072073445_1761812899_n‹ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፤

ግብሩ እንቁላል ነበር ይህን ጊዜ አበሻ፡፡›

የ117ኛውን ዓመት የአድዋ ድል በዓል ሳስብ ባለፈው ዓመት በ116ኛው ዓመት በዓል ዙሪያ ‹የአድዋ ድል ምናችን ነው?› የሚል ዓይነት ክርክር ተነስቶ ዓይቼ ስለነበር ያ መነሻ ሆኖኝ ክርክሬን በጥቅል መልክ በዚህ ርዕስ ዙሪያ ለማድረግ ፈለግሁ፡፡ ሆኖም የሙግቴ አካሔድ አቋሞችን በመገምገም ዙሪያ እንጂ ማስረጃዎችን በማንጠርና በመሰግሰግ ላይ ያተኮረ አይደለም፤ ስለዚህ አንባቢዎቼም በዚህ ዕይታ ቢረዱልኝ ጥሩ መግባባት ይኖረናል የሚል ግምት አለኝ፡፡

እንደኔ አረዳድ የአድዋ ድል ለነፃነት መስዋዕት የተከፈለበት የታሪካችን የማዕዘን ድንጋይ ስለሆነ ልዩ ክብር ይገበዋል፡፡ አድዋ በታሪኩ ብዙ የሆነ የኢትዮጵያውያን ሁሉ የኩራት መንፈስ የተመዘገበበት ታሪክን የያዘ የጋራ መግባቢያ መድረክ ነው፡፡ እንኳን ሌላ የጥንት ታሪካችን እንዲታወስ ሁሉ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ከሆነ በአድዋ ጦርነት ዙሪያ የሚነሱ የክርክር አቋሞችና ጥያቄዎች ይህንን መንፈስ እንዳይሸረሽሩት መጠንቀቅ ግድ ይላል፡፡ ስለሆነም ላድዋ ድል ልዩ ክብር መስጠት እነኳን ለኢትዮጵያውያን ለሌሎች አፍሪካዊያን ያስፈልጋል ባይ ነኝ በግሌ፡፡

እንዳው ይሁን እስቲ ብለን ብንከራከር እንኳን መከራከሪያዎቻችን ከማወናበድ ያለፈ አሳማኝነት የሚኖራቸው አይመስሉም፡፡ ለማንኛውም በአድዋ ጉዳይ ላይ ሊኖሩ የሚችሉ መከራከሪያዎችን በአራት መደቦች ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ ማለትም በአቋም ደረጃ፡-

1ኛ. በጦርነቱ መካሔድ ላይ ባለመስማማት መከራከር

2ኛ. በጦርነቱ ሳይሆን በውጤቱ ላይ ባለመስማማት መከራከር

3ኛ. ጦርነቱንም ሆነ በጦርነቱ የተገኘውን ውጤት በመቀበል፤ የድሉ ታሪክ ለሌላ ጥቅም ውሏል ብሎ መከራከር

4ኛ. ከአድዋ ጦርነት ድል ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ችግር አልነበረም፤ ይልቁንስ ትልቅ ፋይዳ አስገኝቶልናል ብሎ መሟገት

እንደ እኔ ግንዛቤ በአድዋ ጉዳይ የተነሣ የትኛውም ክርክር ከእነዚህ መከራከሪያ ጭብጦች ውጭ ሊወጣ ዐይችልም፡፡ ይህ ከሆነም የትኛው የመከራከሪያ አቋም ትክክል እንደሆነ በተጠየቅ እየቃኙ መዳሰስ አስፈላጊ ነው፡፡ ከመጀመሪያው እንነሣ፡፡ Read the rest of this entry »

 
 
%d bloggers like this: