RSS

Monthly Archives: November 2012

የፊደል ትርጉም፡- ፊደል ምንድን ነው?

 ‹የፊደል ዘይቤ፣ ባጭር ቃል ሲፈታ፣

የቋንቋ ድብኝት፣ የቃል ኹሉ ጎታ፤

የመጻሕፍት ምንጭ፣ የምሥጢራት ነቅ፣

ቢቀዳ ቢቀዳ፣ ውሃው የማያልቅ፡፡› ኪዳነ ወልድ ክፍሌ

(ለአስተዋይ ሰው ይህ ውብ ግጥም ብቻ ይበቀዋል፤ ማብራሪያ መፈለግ የማሃይምነት ግማሽ ክፍል አለበትና፡፡ እኛ ደግሞ በዘመነ-እንብላ፣ እንጠጣ ተገኝተንና በዚህም አስተሳሰብ ተወጥረን ለነጽሮተ-ሕሊና አልታደልንም፤ ያወቅን ይመስለናል እንጂ ቢያንስ ግማሽ ማሃይም ነን፡፡ ለሊቃውንቱ ከሆነ ግን ከዚህ ግጥም አልፎ ሐተታ መደረት ዝባዝንኬ ማብዛት ነው፤ ምክንያቱም ለእነሱ የማስተዋል ጥልቀትና ምጥቀት፣ የግንዛቤ ስፋትና በቃላቱ ጥብቀት በተለያየ አንግል ማመራመር እንጂ የአዋቂነት መለኪያው የማጣቃሻ ጋጋታ አይደለም፡፡ ለማንኛውም እኛ ማሃይምነታችንን ተቀብለን (ያልተቀበለም መሊቅነቱ እየገመገመ) እነሱ የሚሰጡንን ማብራሪያ እንጠቃቅስ፡፡)

የግዕዝ ፊደል የራሱ ሥርዎ ቃላዊና የይዘት ትርጉም አለው፡፡ የይዘት ትርጉሙ በሥርዎ ቃሉ ላይ ተመሥርቶ የሚብራራ ነው፡፡ የሀገራችን ሊቃውንትም ልክ እንደሌሎች የዕውቀት ዘርፎች የፊደልን ምንነትም የሚያሥረዱት ከጥሬ ዘሩ አመጣጥ ጀምረው ነው፡፡ እንዴት ተረጎሙት? ከሥርዎ ቃል ትርጉሙ እንነሳ፡፡

ሀ. ሥርዎ ቃላዊ ትርጉም

ሥርዎ ቃላዊ ትርጉም ማለት የሚተረጎመው ቃል የመጣበት ቋንቋና የግሥ መሠረቱን ለማሳየት የሚደረግ ትርጉም ነው፡፡ ሊቃውንት ፊደልን በተመሳሳይና በተለያየ አተያይ ተርጉመውታል፡፡ እኔ ዘባረቄ እንዳላበላሸው የራሳቸውን የሊቃውንቱን ትርጉም ገለጻ እንደወረደ ላስቀምጥ፡፡

‹ሀገረ-መጻሕፍት፤ ሰዋሰው ግእዝ ወዐማርኛ ክፍል ፩‹ በሚል መጽሐፋው አለቃ አፈወርቅ ዘውዴ ‹ፊደል (ፍዱል) …  ጥቅም፣ ችሎታ፣ ዕውቀት፣ ፍልሱፍ፣ ፍሉይ፣ ፍዱፋድ፣ ፈልፈል እንደማለት ይታሰባል፡፡ ግሱም ፌደ (ፌደለ) ፈየደ (ፈደለ) ረባ ጠቀመ ለየ ይላል፡፡ ወይም ፈደለ ብሎ ይገሳል፡፡ በአማርኛ እገሌ ፋይዳ ቢስ ነው፤ ይህስ ፋይዳ የለውም እንደሚባለው ኹሉ፤ በዚህ መሠረት ፌደ ብሎ ፈየደ፤ ፌደለ ብሌ ፈደለ ያሰኛል፡፡ ፈደለ በማለት ፋንታ ፈለየ ለየ ይላል፡፡

በዚህ መሠረት ፊደል ልዩ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም በመልኩና በስሙ በድምጡም ስለ ማይተባበር ነው ‹የ› እና ‹ለ› ስለሚወራረሱ ነው፤ በለ ፋንታ የግሱ መድረሻ ሆኗል፡፡ ደግሞም ፍዱል በማለት ፋንታ በደጊመ ፊደል ፍድፋድ ማለቱ የደ ፊደልና የየ ፊደል ስለሚወራረሱ ነው፡፡ ይህም ሰፈየ ሰፋ ብሎ ሰፌድ  እንደ ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ፊደል ማለት ብዙ ማለት ነው፡፡ ምክንያቱም ግዕዙ ፊደል ሠላሳ ቅንጣት ሲኾን በቅጠሎቹ መሠረት ብትኖቹ ፊደሎች 202 ስለሆኑ ነው፡፡ ግሱም ፌደ እንደ ሤመ፤ ፌደ እንደ ፄወወ፤ ፌደለ እንደከፈለ ፈደለ ይረባል፡፡ ስለዚህም ፋይዳ የተባለው ጥሬ በምላት የተነገረ ሲኾን ፊደል በፌደለ ሕጸት የተነገ ጥሬ ነው፡፡ ፌደ ይፈይድ ማለት በፋይዳ መሠረት ፌደለ ይፌድል ማለት በፊደል መሠረት እንደኾነ መናገር ነው፡፡› (አለቃ አፈወርቅ ዘውዴ፤ሀገረ,መጻሕፍት፤ ሰዋሰው ግእዝ ወዐማርኛ ክፍል ፩፣ 1988፤ ገጽ 59)

ሌላው ታላቁ ታላቁ ሊቅ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃል መጽሐፋቸው ፊደል  በቁሙ ልዩ፣ ምርጥ፣ ዘር፣ ቀለም፣ ምልክት፣ አምሳል፣ የድምፅና የቃል መልክ ሥዕል መግለጫ፣ ማስታወቂያ‹ (ሰዋሰው-716) ማለት መሆኑን ተርጉመዋል፡፡ በ1926 ዓ.ም. ባሳተሙት መዝገበ ፊደል መጽሐፋቸው ደግሞ ‹ፊደል ማለት የነገር፣ የቃል ምልክት አምሳል ወይም መግለጫ፣ ማስታወቃያ ማለት ነው፡፡› ብለው ገልጸውታል፡፡ በዋናው የሰዋሰው መጽሐፋቸው መግቢያ ደግሞ ሰፋ አድርገው በማብራራት ‹ፊደል ማለት የቋንቋና የቃል የአነጋገር ኹሉ ምልክት፣ አምሳል ወይም መግለጫ ማስታወቂያ ማለት ነው፡፡ የሰው ኹሉ መልክ በጥሩ ሥዕልና በመስታዮት ታይረቶ፣ ተለይቶ እንዲታወቅ የማይታየውም ኅቡእ ንባብ ረቂቅ ሐሳብ በቀለም ገዝፎ በክርስታስ ተጥፎ በፊደል መልክ ታይቶ ተለይቶ ይታወቃልና ስለዚህ ምልት አምሳል መግለጫ ማስታወቂያ አሉት፡፡ በግእዝ ፈደለ ብሎ ጣፈ፣ ቆጠረ፣ ለየ፣ መረጠ ይላልና ፊደል ከዚህ ይወጣል፤ ልዩ ምርጥ ማለት ነው፤ ቅንጣቱን ቅንጣትነቱን የቃል ዘር መኾኑን ያሳያል፡፡ ዐረቦች ሐርፍ፣ ዕብራውያን ኦት ይሉታል፤ በተገናኝ ምልክት ማለት ነው፡፡ (ሰዋሰው ግእዝ-27) በሚል አስቀምጠውታል፡፡ ይህም የሳቸው ትርጉም በሌሎቹ ሊቃውንት ኹሉ የተነወጸባረቀና የታመነበት ነው ማለት ይቻላል፡፡

አቡነ መልከ ጸዴቅም (የበፊቱ ሊቀ ሥልጣናት ሀብተ ማርያም ወርቅነህ) ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት በሚለው መጽሐፋቸው አንዳንድ ሊቃውንት ግን ፊደል ማለት ፍጡር አንድም መፍጠሪያ ማለት ነው ብለው ይናገራሉ፤ ቃሉም የወጣው ፈደለ (አጥብቆ) ፈጠረ ብለው ነው፤ ይኸንም ከግዕዝ ቋንቋ እንደወጣ አድርገው ይናገራሉ፡፡ ለአስረጅ ያህልም በአማርኛችን አንድ ሰው ባልሠራው ነገር ሲከሰስ፣ ሲወቀስ እንዳው ነገሩን ፈድሎብኝ ነው እንጂ እኔ ሠርቸው አይደለም ይላል፤ ትርጉሙም እንዲያው ጥፎብኝ አንድም ለጥፎብኝ ነው እንጅ እኔ ሠርቸው አይደለም እንደማለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ የሁለቱም ቃላት ትርጉማቸው አንድ ዓይነት ነው፤ ምክንያቱም ለክፉም ኾነ ለደግ ነገር መፍጠሪያው መጣፊያው ፊድል ስለኾነ፤ ጻፈብ፤ ለጠፈብኝ፤ ፈጠረብኝ፤ ብሎ ይናገራልና፡፡ በደህናውም ነገር ቢኾን ካለ ፊደል ሊነገር ስለማይቻል ጻፈብኝ በማለት ጻፈልኝ ሊል ይችላል፤ ማለት ለክፉ ብቻ ሳይኾን ለደግም ነገር ሊኾን ይችላል፡፡› (ጥንታዊ የኢትዮጵያ ትምህርት፤ ገጽ 17)  

ከዚህ በላይ ከጠቀስናቸው ከሦስቱ ሊቃውንት ትርጉም ተነስተን ፊደልን በጥቅሉ ‹‹ፊደል (ፍዱል)ግሱም ፌደ (ፌደለ)፤ ፈየደ (ፈደለ) ማለት ረባ ጠቀመ ለየ ከሚለው ግሥ የወጣ ጥሬ ዘር ሲኾን ጥቅም፣ ችሎታ፣ ዕውቀት፣ ፍልሱፍ፣ ፍሉይ፣ ፍዱፋድ፣ ፈልፈል ተብሎ ይፈታል፤ ወይም ፊደል ፍጡር ወይም የአስተሳሰብ መፍጠሪያ ተብሎ ሊተረጎም ይችላል ወይም በሌላ አገላለፅ ፊደል ልዩ፣ ምርጥ፣ ዘር፣ ቀለም፣ ምልክት፣ አምሳል፣ የድምፅና የቃል መልክ ሥዕል መግለጫ፣ ማስታወቂያ ማለት ነው፡፡› በሚል ጠቅልለን ማስቀመጥ እንችላለን፡፡

ለ. ይዘታዊ ትርጉም

የሀገራችን ሊቃውንት የፊደልን መሠረታዊ ጥበብነት፣ አስደናቂነት፣ ጥቅምና ከማንነት ጋር ያለውን ቁርኝ ተመልክተው ወይም ቀድሞውን ይህንን አውቀው ለትውልድ ያስተላለፉት ምንነቱን የሚያሳይ የፊደል ትርጉም አላቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የፊደልን ምንነት ከተግባሩ አንጻር የሚገልጹ የሊቃውንት ገለጻ ማሳያወችን እንመልከት፡፡ (ሊቃውንቱ በሚጥም ቋንቋ፣ ለዛና ቁጭት ገልጸውት ምን አስፈተፈተኝ በሚል ነው ይህንን ማለቴ፡፡)  

አቡነ መልከ ጸዴቅ ‹አባቶች ሲመስሉ ‹ዘእንበለ ፊደል ኢይትነገር ወንጌል› ይላሉ፤ ማለት ወንጌል ሳይቀር የምትጻፈው የምትተረጎመው በፊደል አማካይነት ነው፡፡› እያሉ እንደሚናገሩ አስቀምጠዋል፡፡  አክሊለ ብርሃን ወ/ቂርቆስ፤ መጽሔተ አእምሮ  በሚለው በ1948 ባሳተሙት መጽሐፋቸው  ገጽ 9 ላይ ፊደልን ሲተረጉሙ ‹ፊደል ማለት በግዕዝ ቋንቋ መጽሔተ አእምሮ፣ ነቅዓ ጥበብ፣ መራሄ ዕውር፣ ጸያሔ ፍኖት፣ አበ መጻሕፍት፣ ርእሰ መጻሕፍት ማለት ነው፡፡› ብለው አስቀምጠዋል፡፡ ይህንን የሳቸውን ጥቅል ሐሳብ አቡነ መልከ ጸደቅ ከላይ በጠቀስነው መጽሐፋቸው ገጽ 18 ላይ ሲያብራሩ፡- ‹

  1. ፊደል ማለት መጽሔተ አአምሮ ማለት ነው፤ ምክንያቱም ያለ ፊደል ምንም አይታወቅምና፤ የአእምሮ መገመቻ የምሥጢር መመልከቻ ማለት ነው፡፡
  2. ፊደል ማለት ነቅዓ ጥበብ ማለት ነው፤ ምክንያቱም የጥበብ ኹሉ ምንጭ መገኛ ፊደል ናትና
  3. ፊደል ማለት መራሔ ዕውር ማለት ነው፤ ምክንያቱም የሰውን ልጅ ኹሉ ከድንቁርና አውጥቶ ወደ ብርሃን ይመራልና፡፡
  4.   ፊደል ማለት ጸያሔ ፍኖት ማለት ነው፤ ምክንያቱም ድንቁርናን ጠርጎ አጽድቶ ከፍጹም ዕውቀት ያደርሳልና፤
  5. ፊደል ማለት ርእሰ መጻሕፍት ማለት ነው፤ የመጻሕፍት ኹሉ ራስ እናት ፊደል ናትና፤ ለ ፊደል ማንኛውም መጽሐፍ ሊነገር አይቻልም፤ ‹ኢተወልድ መጽሐፍ ዘእንበሌሁ ለፊድል› ይላልና፡፡ ይሉናል፡፡ (ሊቀ ሥልጣናት፣ ጥንታዊ ትምህርት፤ ገጽ 18)

ስለዚህ ፊደል በአገልግሎቷ የዕውቀቶች ኹሉ መሠረት፣ አጥንትና ሥር፣ እንዲሁም ጉልላታቸው ነች ማለት ይቻላል፡፡ ያለ እሷ የሰው ልጅ ዕውቀት መመዝገቢያ መሠረት የለውምና ሳይመዘግብና በማስታወስና በማነጻጸር ሳያገናዝብ ደግሞ ዕውቀቱ ሊበለጽግ አይችልም፡፡ ስለኾነም ነው አበው ‹ኢተወልድ መጽሐፍ ዘእንበሌሁ ለፊድል› ብለው የደመደሙት፡፡

በሌላ በኩል የፊደልን ይትባህል ከማንነት፣ ከታሪክና ከባህል አኳያም ይተነተናል፡፡ ቋንቋ የባህል አካል የኾነ የማንነት መገለጫ ነው ይባላል፤ ‹አነጋገርህ ያስታውቅብሃል› እንዳለው፡፡ ምክንያቱም የቋንቋው ተናጋሪ ማኅበረሰብ በንግግርም ይሁን በጽሑፍ ወይም ሁለቱንም አዋህዶ የእሱነቱን ባህል የሚገልጸውና የሚያስተላፈው በሚገለገልበት በቋንቋው ነውና፡፡ ከሥነ ጽሑፍ ጋር ተያይዞ ቋንቋ ሊገለጽና ማንነትንና ባህልን ሊዘግብና ሊገልጽ የሚችለው ደግሞ ፊደልን በመጠቀም ነው፡፡ የዚህን ማኅበረሰብ ማንነትና ባህል ከሀገራዊ ታሪክ ጋር ሲያያዝ ደግሞ መገለጫነቱ ከሥልጣኔና ከሀገራዊ የኅብረተሰብ መስተጋብር ጋር እየተመጋገበ ይጎላል፡፡ ይህንን በማስተዋል ነው አስረስ የኔሰው፡-

 ‹ቋንቋ መልክ ነው፤ መልክም ቋንቋ ነው፡፡ ፊደል ሐውልት ነው፤ ሐውልትም ፊደል ነው፡፡ ፊደል መልክ ነው፤ መልክም ፊደል ነው፡፡ ፊደል አባት ነው፤ አባትም ፊደል ነው፡፡ ፊደል ልጅ ነው፤ ልጅም ፊደል ነው፡፡ ፊደል ወሰን ነው፤ ወሰንም ፊደል ነው፡፡ ፊደል ዓላማ ነው፤ ዓላማም ፊደል ነው፤ ዓላማ የኩራት ምልክት ነው፤ ኩራም ነጻነት ነው፤ ነጻነትም መንግሥት ነው፤ መንግሥትም ኃይል ነው፤ የኃይል መቆሚያው ንጉሥ ነው፤ የሕዝብ ክብሩ ንጉሥ ነው፤ የንጉሥ ክብሩ የሕዝብ ብዛት ነው፤ የሕዝብ ብዛትም የንጉሦች ንጉሥ (ንጉሠ ነገሥት) መባልን ያመጣል፤ የማንኛውም ነገር መጠቅለያ ፊደል ነው፡፡ መንግሥት ካለው ፊደል አለው፤ ፊደል ካለው መንግሥት አለው፤ መንግሥት ሲጠፋ ፊደልም አብሮ ይጠፋል፤ ይህንን የማያውቅ የለም፡፡› ብለው የገለጹት፡፡ (አስረስ የኔሰው፤ የካ መታሰቢያ፤ መግቢያ) ይህንን ከኢትዮጵያ ታሪክና የሥልጣኔ ምንጭነትና ከጥንታዊ የግዛት ስፋቷ ጋር በማጣመር የሚተነትን (እንደ ሎሬት ጸጋየ ገ/መድኅን ዓይነት) ምሁር ቢያስተወለው ምን ዓይነት ትንታኔ ሊያወጣለት እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

የአስረስ የኔሰው በትቤ አክሱም ቁጭታዊ መጽሐፋቸው ደግሞ (የግዕዝ ቋንቋን)፡-

‹ኢትዮጵያ ከካም መንግሥት ዠምራ እስከ ዛሬ… ዘመን የቆየችበት በዚህ ግዕዝ ነው፤ ጽላተ ሙሴ ከመጣች ዠምሮ እስከ ዛሬ ትመሰገን የቆየችበት ይህ ግዕዝ ነው፤ የግዕዝ ቋንቋ ፊደል ራሱን የቻለ እውነትም ነጻነት ያለው መሆኑን ራሱ ምስክር ኾኖ እያስረዳ አናይህም በማለት ግዕዝ የነጻነት ሐውልት ነው፤ ይህንንም ለማየት ኦሪ. ዘፀአት 12፡-37 እይ፤ግዕዝ መልክ ነው፤ ኢትዮጵያዊ በግዕዝ ግዕዝም በኢትዮጵያ ይታወቃል፤ ግዕዝ ዓላማ ነው፤ ዓላማ ማለትም የነጻነት ክብር ምልክት ነው፡፡ ግዕዝ የአባቶች ቅርስ ነው፤ አባቶች ያስቀመጡት ሀብት ኹሉ መገናኛው ግዕዝ ነው፤ ግዕዝ የሀገር ወሰን ምልክት ነው፤ ማለት ወሰሙ በጽሕፈት ድንጋይ ተከልሎ የግዕዝ የጥበብ መምህር ነው፤ የግዕዝ መጽሐፍን በጥብቅ ያነበበ ጥንታዊ ጥበብን ያገኛል፤ግዕዝ ሀብት ነው፤ ግዕዝን አጥብቆ የመረመረ እውነተኛይቱን ዓለም ያገኛል፤ ግዕዝ ማይ (ውሃ) ነው፤ በማይ ልጅነት ከሥላሴ ይገኝበታል፤ግዕዝም ምሥጢሩ ግዕዝን ማይ ለማለት ግዮንን ያመለክታል፤ ግዮን ግዕዝ ፊደሉን ገን መመልከት ነው፤ ግዕዝ መልክ ነው ያልኩት ኢትዮጵያዊ ፊደሉን ለውጦ ቢገኝ መልኩን አንድ ነገር ቀብቶ እንደመታየት ያለ ነው፤ እንግዲህ አሁን አንድ ኢትዮጵያዊ መልኩን ነጭ ወይም ቀይ ቀለም ቀብቶ በዓለም አደባባይ ቢታይ የሚመሰገን ይኾን፡፡ ደግሞ ዋናው ጠቅላላው ነገር ግዕዝ የእግዚአብሔር ምሥጢር መነገሪያ የልዕሉ እግዚአብሔር ስም ነው፣ እግዚእ፣ አግዓዚ፣ አጋዕዝት፣ አግዓዘ ከእነዚህ ኹሉ ቃሎች የትኛው ሊቀነስ ይገባል፡፡ ይኸውም ፊደል ማለት መያዣ፣ መጨበጫ፣ ማወቂያ ነው፤ ….› ይሉናል፡፡ (ትቤ አክሱም መኑ አንተ? 1951፣ ገጽ 255)

በአጠቃላይ ሊቃውንቱ የፊደልን ምንነት አስፍተውና አምልተው የገለጹት በዚህ መልክ ነው፡፡ የፊደላትን ጠባይ፣ አፈጣጠርና ጥበባዊ ትሩፋታቸውን በሚመለከት በሚቀጥለው ሊቃውንቱ የሚነገሩንን አብረን እናዳምጣለን፤ ከቻልንም ‹ዕፁብ! ዕፁብ ውእቱ!› እያልን መደነቅ ነው፡፡ 

Advertisements
 

አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ስለ ፊደል…

የተላከ ከግስ ከመዝገበ ቃል፣

ትርጓሜ አፈታት ሐተታ ፊደል፣

ይድረስ ከወዳጀ ከሕፃናት ልብ፣

ከግእዝ ሰራዊት ካማርኛ ሕዝብ፣

ከናቴም ከጦቢያው ካፍሪካ ባላልጋ፣

እጆቿን ወደ እግዜር ከምትዘረጋ፡፡

ሰላምታ አቀርባለሁ ለፊደል ጸሐፍት፣

ላተሞች ሳይቀር እጅ በመንሳት፡፡

ስለተጠማችኹ የፊደልን ዜና፣

ከሥሩ ከምንጩ ላመጣው ነውና፤

ምናልባት ስትቀምሱት ስታጣጥሙት፣

ጠላ ነው ብላችሁ ስም እንዳትሰጡት፡፡

ጥሩን ቃል ውሃ ጠላ ነው ብትሉ፣

ይታዘባችኋል የሚቀምሰው ኹሉ፡፡

እነ ምን አለበት እነ ኹሉ ቀኙ፣

በትግረኛ መንፈስ ፊደልን ሲቃኙ፣

ከግእዝ ለይተን ዐማርኛን ኹሉ፣

ባ፩ ‹አ› ባ፩ ‹ሀ› (ሰ፣ጸ) እንጣፍ የሚሉ፣

አላወቁም ይኾን ቋንቋ እንዲበላሽ፣

ንባቡም ምሥጢሩም እንዲኾን ብላሽ፡፡

እንደነሶምሶም ዐይኑ ከወጣማ፣

ጥፈቱም ቋንቋውም ይኾናል ጨለማ፡፡

ዐወቀች፣ ዐወቀች፣ዐወቀች ቢሏት፣

መጣፏን ዐጠበች የሚሉት ተረት፣

ላየው ላስተዋለው ላይናማ ደብተራ፣

ሠምና ወርቅ ነው፣ ከዚህ ምኞት ጋራ፡፡

የፊደልን ገላ ደፍሮ ለመቁረጥ፣

ሐኪም መኾን ያሻል በአፍአ በውስጥ፣

አፍአው ዐማርኛ፣ ውስጡም ግእዝ ነው፣

ትምርቱ እንደ ገደል ያልተደፈረው፡፡

ለቋንቋ በሽታ ለጥፈት ሕማም፣

ከትምርት በቀር መድኃኒት የለም፡፡

እንደምን ይቻላል በቀንጃ ፊደል፣

የቋንቋውን ሞክሼ ማወቅ መነጠል፡፡

ጥንቱን ፊደልችን ሴማዊ በገና፣

ኹለት ኹለት ኾኖ ለምን ተሠረና፡፡

ዐማርኛችንስ በጥፈት ጎዳና፣

ካባቱ ከግእዝ መቼ ይለይና፡፡

የትምርቱስ ችጋር የዕውቀቱ ቀጠና፣

ፊደል በማሳነስ መቼ ይለቅና፡፡

በሴማያን ዘንድ በያፌት ልጆች፣

ይህ ነገር ቢሰማ ያሰኛል ሞኞች፡፡

(መዝገበ-ፊደል፤ ገጽ 28-32)

ኪዳነ ወልድ ክፍሌ

 

የፊደል የት መጣነት

(Read in PDF)የፊደል የት መጣነት

‹ወርቅ ነው፤ ወርቅ ነው የግእዝ ፊደል፣

ሰባት እጅ የጠራ በሰባት ባሕል፡፡› ኪዳነ ወልድ ክፍሌ

የሰውን ልጅ ዕውቀት ታሪካዊ ዕድገት ስንዳስሰው የጽሑፍ ምልክትን በመፍጠር ጀምሮ አሁን ያለንበት የመረጃ ዘመን ላይ ደርሷል፡፡ ከጥንቱ የጽሑፍ ምልክት ፈጠራ አንጻር ስንገመግምም በአሁን ጊዜ ያለው የዕውቀት ደረጃ ብዙም ሊለፈፍለት የማይገባ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም የጥንቱ ለመጀመር የተደረገ ጥረት ነው፤ የአሁኑ ዕውቀት ደግሞ ያለውን ማስፋፋትና ማጎልመስ ነው፡፡ ለምሳሌ አውሮፕላን ተፈልስፎ በሰማይ ላይ መብረር ከተጀመረ በኋላ ያለው የአውሮፕላን ዓይነትና የሞደል መለያየት ማሻሻል ስለሆነ የመጀሪያውን አውሮፕላን ከሠሩት የራይት ወንድማማቾች ሥሪት ወይም ለመጀመሪያ ጊዜ ንድፍን ካስቀመጠው ከዳቪንቺ ፈጠራ የበለጠ ዕይታ ሆኖ አስደንቅም፡፡  እዚህ ላይ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ ‹ዕውቀት ሲበዛ ማንኛውንም ነገር ለኑሮ የሚያስፈልገውን ነገር ለማግኘት መሰናክሉና ድካሙ ያንሳል› (መንግሥትና የሕዝብ አስተዳደር 1953፤ገጽ፡-45) ያሉትን አስተውሎታዊ ገለጻ ልብ ማለት ነው፡፡ የሰው ልጅ ዕውቀት የዳበረው ደግሞ ፊደልን በጽሑፍ መጠቀም ከጀመረ በኋላ ነው፡፡ Read the rest of this entry »

 
1 Comment

Posted by on November 22, 2012 in የኢትዮጵያ ፍልስፍና

 

እውን ኢትዮጵያዊ ፍልስፍና የለም? (3)

  2. እውንበኢትዮጵያፍልስፍናወንበርየላትም?

1. ኢትዮጵያ ውስጥ ፍልስፍና ወንበር የላትም፡፡

2. ወንበር ይዞ ፍልስፍናን የሚያስተምር ሳይኖርም አካዳሚያዊ ፍልስፍና አይኖርም፡፡

3. ስለዚህ የተለየ የኢትዮጵያ ፍልስፍና የሚባል የለም፡፡

           ትችታዊማብራሪያ

የዚህን ክርክር ትክክል መሆን ወይም አለመሆን ለመመዘን በቅድሚያ ወንበር ምንድን ነው የሚለውን ማየት ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ወንበር በሀገራችን የትምህርት ባህልና በእዚህ አግባብ መምህር ተሰይሞበትና ተማሪ ተለይቶለት የሚሠጥ የትምህርት ዓይነትን ያመለክታል፡፡ ከዘመናዊ አሰተምህር ስያሜ አንጻር ካየነው ራሱን የቻለ አካዳሚያዊ የትምህርት ዘርፍ ማለታችን ነው፡፡ ስለዚህ ‹ፍልስፍና ወንበር የላትም› ሲባልም በአንድ የትምርህት ዘርፍነት በሀገራችን የሚሰጥ ዕውቀት አይደለም ማለት ይሆናል፡፡ አሁን ‹እውን ይህ ትክክለኛ ገለጻ ነው ወይ?› ወደ ሚለው ፍተሻችን ስንገባ ‹ወንበር ተዘርግቶለት የሚሠጥ የፍልስፍና ዕውቀት ዘርፍ በኢትዮጵያ የለም?› የሚለውን ጥያቄ መመርመር ይኖርብናል፡፡ Read the rest of this entry »

 
 
 
%d bloggers like this: