RSS
Link
05 Mar

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

ዘይእዜ (ቅኔ)

ይሄሎ ቃል በተቃውሞ፣

ወለድኩ ቃል ለእመ ትቤ ድንግል

ለአዝማድ ዮሴፍ ወሰሎሜ

እስመ አብ እም ቅድመ ዓለም ወለድክዎ ይብል፤

ወከመ ኢይትክሐድ አብ ከመ መልከአ አብ መልክአ ወልድ

ወከመ ኢትከሐድ እም ገባሪተ ኃይል

ኢሀሎ እምቅድመ ክሒደ ወላዲት ዘይክል፡፡

ወከመ ኢትከሐድ እም ገባሪተ ኃይል

ትርጉም፡-

ቃል በተቃውሞ ይኖራል፣

ለሰሎሜና ዮሴፍ ዘመዶቿ

ድንግል ቃልን ወለድኩ ብትል

አብ ከዓለም በፊት (አስቀድሞ) ወለድሁት ይላልና

አብ እንዳይካድ የቃል መልክ እንደ አብ መልክ ነውና፣

ታምር ፈጣሪዋ እናትም እንዳትካድ

ከቀድሞ ጀምሮ እናትን መካድ የሚችል የለምና፡፡

ታምር አድራጊዋ እናትም እንዳትካድ፡፡[1]

በኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት በዓለም ላይ የተለያዩ አቋሞች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በጥቅሉም በሦስት ጭብጦች በመከፋፈል ልናስቀምጣቸው እንችላለን፡፡

 1. ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ ያልነበረ ሰው ነው፡፡
 2. ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ የነበረ ታላቅ የሥነ ምግባር መምህር ነበር፡፡
 3. ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክም ሰውም (አምላክ ወሰብዕ) ነው፡፡

በነዚህ አማራጮችም ‹አንተም ልክ ነህ፤ እሱም ልክ ነው፤ ስለዚህ ስህተት የሚባል ነገር የለም፡፡› የሚል አቋምና አረዳድ አይሠራም፡፡ ምክንያቱም ሦስቱም አማራጮችም ትክክል ከኾኑ ስህተተኛ የኾነ አቋም አይኖርም፤ ስህተተኛ ከሌለም ትክክለኛውን መምረጥ ስለማይቻል አንዱን ደግፎ ሌላውን ነቅፎ መከራከር አይቻልም፤ ይህ ደግሞ የተጠየቅ ዕይታንና የሐሣብ ፍሰትን ይቃወማል፡፡ አንድ የመደምደሚያ መቋጫ ሊኖረው የግድ ነውና፡፡ ስለዚህ ከሦስቱ አማራጮች መካከል ትክክል በመኾን ተቀባይነት ሊኖረው  የሚችለው አንዱ ብቻ ነው፡፡ ትክክለኛው አማራጭም የትኛው አንደኾነ በተጠየቅ በመመዘን መመርመር፤ መርምረንም በትክክለኛው ውጤት መስማማት ያስፈልጋል፡፡

1ኛ. ኢየሱስ ክርስቶስ የሚባል ሰው በታሪክ አልነበረም፡፡

የዚህን ንዑስ ርዕስ የሚያነብ የትኛውም ክርስቲያን ጥሩ ስሜት እንደማይሰማው ይገባኛል፡፡ ይሁንና እንደእኔ እምነት የትኛውም ክርስቲያን ለሚጠየቀው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ መስጠት ይኖርበታል፤ ‹ኢየሱስ ክርስቶስ የሚባል ሰው በታሪክ አልነበረም› በማለት የሚከራከሩ ሰዎች መኖራቸውንም ማወቅ አለበት፤ የእነዚህ ሰዎች መኖር እውነት ከኾነም ለሚጠይቁት ጥያቄ አጥጋቢ መልስ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ምናልባት እዚህም ላይ ቢኾን ‹ኢየሱስ ክርስቶስ የሚባል ሰው በታሪክ አልነበረም፡፡› በማለት የሚከራከር በሌሎች ሀገራት ይኖር ይኾናል እንጂ በእኛ ሀገር ይህንን አቋም ይዞ የሚከራከር የለም፤ በሌለበትም አማራጭ እንደኾነ በመውሰድ ማቅረብ አጉል ጥርጣሬን መጋበዝ ነው፡፡› የሚል መከራከሪያ ይቀርብ ይሆናል፡፡ ይሁንና ይህ አስተያየት የዓለምን ነበራዊ ሁኔታ ብቻ ሳይኾን የዘመናችንን ኹኔታም ያላገነዛበ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ‹የክርስቲያኖችና የሙስሊሞች ሥነ መለኮት ጉባኤዎች› የሚለውን የትርጉም መጽሐፍ ማየት ይቻላል፤ መጽሐፍ እንቢ ብሎ የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች የቅርብ ጊዜ ፈጠራዎች እንደኾኑ ለማሳየት የተደረገ ምኞትን የያዘ ነው፡፡ እናም እውነተኛውን ታሪክ ለማያውቅ ሰው እውነት መምሰሉና እንደማጣቃሻም መወሰዱ አይቀርም፡፡ እንደ ምሳሌም ይህንን አልኩ እንጂ በዚህ መልክ የተጻፉና የተተረጎሙ መጻሕፍት በብዛት አሉ፡፡ ስለዚህ የዚህ ንዑስ ርዕስ መንፈስንም ‹ይህም አለ› በሚል መልክ መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ይህንን በዚህ ላይ እንግታና ‹ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ ያልነበረ ሰው ነው፡፡› ብለው የሚከራከሩ ሰዎች ምን ያህል እውነተኛና አሳማኝ መከራከሪያ  አላቸው?› በማለት ጠይቀን እንመዝነው፡፡

 1. ይህን አማራጭ አቋም ግን በጊዜው የነበሩ የክርስትና ማስረጃዎች ብቻ ሳይኾኑ ሌሎች የታሪክ መጻሕፍትና ክስተቶችም ይቃወሙታል፡፡ የዓለማችንን የታሪክ ማስረጃዎችም በሙሉ የሚደፈጥጥና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡

ለምሳሌም፡-

 • o የአይሁዳዊያን ታሪክን የጻፈው የማትያስ ልጅ ዮሴፍ ምስክርነት (37-100 ዓ.ም.)
 • o የሮማ ታሪክ ጸሐፊ የኾነው ታሲተስ (20-120 ዓ.ም.) ምስክርነት
 • o በቶማስ ስምና በሌሎች ሐዋሪያት ስም የተጻፉ የግኖስቲኮች ወንጌል
 • o የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ጸሐፊዎች… የኢየሱስ ክርስቶስን በታሪክ የነበረ ህልው ሰው መኾን ይመሰክራሉ፡፡
 1. እነዚህ ማስረጃዎች ደግሞ የተለያየ አመለካከት፣ ፍልስፍና፣ ሥነ-ልቦና፣ ሃይማኖትና የባህል ዳራ ያላቸው ሰዎች የጻፏቸው ናቸው፡፡ በዚህ ኹኔታ ላይ የሚገኙ ምስክሮችም የሌለ ነገርን በመስማማት ፈጥረው ጻፉ ማለት የሚቻል አይደለም፡፡ እንዳውም ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ ያልነበረ ሰው ነው የሚለው መከራከሪያ ብዙ የምናውቃቸውን ታሪኮችና የአስተምህሮ ውጤቶች ኹሉ ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ ለምሳሌ ታሲተስ የጻፈውን የሮማን ታሪክ ከተቀበልን በዚያ ውስጥ ተፅፎ የሚገኘውን የኢየሱስ ክርስቶስን ታሪክ ያልነበረ ነው እንዴት ለማለት እንችላለን? ነው በዓለም ላይ አጠቃላይ የታሪክ ጽሑፎች መካዳችን ነው? ምክንያቱም የሮማ መንግሥት ታሪክ ስንል በመንግሥቱ የተፈጸሙ ዋና ዋና ክንውኖች ማለታችን መኾኑ ይታወቃል፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክም በዚህ ታሪክ ክስተት ውስጥ ዐቢይ ክስተት ነው፡፡ ይህ ከኾነ ኢየሱስ ክርስቶስ በተለየ በህልውና የሌለ በመኾን ታሪኩ ሐሰት የሚኾነው በምን ምክንያት ነው? የአይሁዳዊያን ታሪክም ቢኾን አይሁዳዊያን የሚባሉ የእሥራኤል ሕዝቦች አልነበሩም ካልተባለ በስተቀር የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክን ከእነሱ ታሪክ ነጥሎ ማስወገድ አይቻልም፡፡ በታሪኩ ዙሪያ ባለመስማማት መከራከር አንድ ነገር ነው፤ ታሪኩን ሙሉ ለሙሉ መካድ ሌላ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ ያልነበረ ሰው ነው የሚለው መከራከሪያ ውኃ አለመቋጠሩ ብቻ ሳይኾን ለውኃ የሚኾን ሥፍራም የለው፡፡
 2. በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ክርስቶስ ያልነበረ ሰው ስለመኾኑ የሚገልፅ ምንም ማስረጃ የለውም፡- በኢየሱስ ክርስቶስ ዙሪያ የተጸፉ የታሪክ ማስረጃዎችን ሐሰትነት የሚያስረዳ የተቃዋሚ ሰው ጽሑፍ ብናገኝ ይህንን የክርስቶስ ህልውነት (በታሪክ መከሰት) ለመጠራጠር እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን ያለው ኹኔታ ተቃራኒው ነው፤ ከዚህ በላይ የጠቀስናቸውና ሌሎች  ከተቃዋሚዎቹምና ከአማኞቹ በኩል ያሉት የታሪክ ማስረጃዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ከዛሬ 2000 ዓመት በፊት በኢየሩሳሌም የነበረ ሰው ስለመኾኑ በሰፊው ያብራራሉ፡፡ ይህ ከኾነም ማስረጃ ያለው እያለ የሌለውን የምኞት ነቀፋ አቋም እንዴት እንደግፋለን? ማስረጃ የሌለውን ክርክር አዕምሮ እሺ ብሎ እንደማይቀበለው ኹሉ ይህንንም ዕይታ ወይም የመከራከሪያ አቋም አዕምሮ ያለው ሰው ይቀበለዋል ለማለት ያስቸግራል፤ እንኳን ተመራማሪና ጠያቂ የኾነ ፈላስፋና ሳይንቲስት?

‹ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ የነበረ ሰው ሊኾን ይችላል፤ ኾኖም በወንጌል የተዘገበው ታሪክ የእሱ አይደለም፡፡› በማለት ለመከራከር ይሞከር ይኾናል፡፡

 • o ይህም አቋም ቢኾን መሠረቱ ምን እንደኾነ ግልፅ አይደለም፡፡ አቋሙ የሚያወራው የሌላ ኢየሱስ ክርስቶስን ህልውነት ከኾነ እየተነጋገርን ያለነው ከዛሬ 2000 ዓመት በፊት በኢየሩሳሌም ተከስቶ ስለነበረው ነው፡፡ ስለ አንድ ሰው ስንነጋገርም ርእሳችን ስለዚያው ሰው ብቻ መኾን ይኖርበታል እንጂ በዚያ ሰው ስም ሊጠሩበት የቻሉ ሰዎችን ማንነት፣ ተግባርና ታሪክ እያምታታን መኾን አይገባውም፡፡ ስለዚህ የምንነጋገረው ተቃዋሚዎቹና ተከታዮቹ ስለተስማሙበት በተባለው ጊዜና ሥፍራ ስለነበረው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ኾኖ ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ታሪኩ የተመዘገበው ካልኾነ ታሪኩ በምን ተመዝግቦ የሚገኘውን ነው ‹በህልውና ያልነበረ ነው› በማለት የሚከራከሩት?
 • o በሌላ በኩልም በዚያን ጊዜ ከምንለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሌላ ኢየሱስ ክርስቶስ የተባለ ሰው ስለመኖሩ የታሪክ ጽሑፍ ማስረጃ የለም፡፡ ከዚህ በላይ የጠቀስናቸው የሮማና የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊዎችና ግኖስቲኮችም ቢኾኑ የጻፉት እኛ ስለምንለው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው እንጂ ስለሌላ አይደለም፡፡ ለምሳሌም የማትያስ ልጅ ዮሴፍ የታባለው የአይሁዳዊያን ታሪክ ፀሐፊ በወንጌል ተጽፈው የሚገኙትን ታሪኮች (በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ስለመጠመቁ፣ ያቆብ የክርስቶስ ወንድም ስለመኾን፣ ስለ መሰቀሉ…) ነው ያቀረበው፡፡ ይህ እውነት ከኾነም የሌላውን ኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ በምንና ከማን አግኝተውት ነው በወንጌል የተመዘገበው ታሪክ የእሱ አይደለም የሚባለው?
 • o በወንጌል የተመዘገበው የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ አይደለም ማለት ወንጌል እውነት አይደለም ማለት ነው፡፡ ወንጌል ግን እውነት ስለመኾኑ በተለያየ በጥንት ጊዜ (በ1ኛውና በ2ኛው መ/ክ/ዘ) ከጸሐፊዎቹ በተለያየ ቋንቋ ተገልብጠውና ተተርጉመው የሚገኙ የብራና መጽሐፎች እንዲሁም በተለያየ ጊዜ በነበሩ ሰዎች ተጠቅሰው የነበሩ የወንጌል ጥቅሶች ተሰብስበው ልዩነታቸው ሲጠና ከ99% በላይ ተመሳሳይ ኾነው ተገኝተዋል፡፡ ወደ 1% የሚጠጋ ልዩነትም ቢኾን ሊገኝ የቻለው ከአተረጓጎምና ከአገላለጽ ልዩነት የተነሳ መኾኑ ተረጋግጧል፡፡ እንዲሁም ‹አርኮ ቮልዩም› እና የማትያስ ልጅ ዮሴፍ የጻፈው ታሪክ የሚያረጋግጡት በወንጌል የተጻፈው ታሪክ እውነት መኾኑን ሲኾን ወንጌል ደግሞ የያዘው የኢየሱስ ክርስቶስን ታሪክ (የፈጸማቸውን ተግባራትና የደረጋቸውን ንግግሮች) መኾኑ ይታወቃል፡፡ ይህም እውነት ከኾነ የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ በወንጌል የተጻፈው አይደለም ማለት ስህተት ነው፡፡ ስለዚህ በወንጌል ተመዝግቦ የሚገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ እውነተኛ ነው የሚለው አማራጭ ትክክል ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ ያልነበረ ሰው ነው የሚለው መከራከሪያ ምንም ማስረጃና የክርክር ተጠየቅ የሌለው አቋም ስለኾነ ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም፡፡

ስለዚህ በወንጌል ተመዝግቦ የሚገኘው የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ ነው፡፡

2ኛ. ክርስቶስ በታሪክ ከተከሰቱት ታላላቅ ሰዎች መካከል አንዱ ነው?

ከከባድ እንቅልፉ ሰውን ለመቀስቀስ

ቢነሣ ሶቅራጥስ ቢወለድ ኢየሱስ

እነ ስም አይጠሩ

ሳይፈሩ ሳያፍሩ

ያንን በጎልጎታ፤ ያንን በእሥር ቤት

በመስቀል ሰቀሉት፤ በመርዝ ገደሉት፡፡[2]

ከዚህ በላይ ባለው ንዑስ ርዕስ ‹ኢየሱስ ክርስቶስ በታሪክ በህልውነት በምድር ላይ ያልተከሰተ ሰው ነው፡፡› የሚለው መከራከሪያ እንደማያስኬድ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ምክንያትም በክርስቶስ ህልውነት ተስማምተን ክርክራችን በአደረጋቸው ተግባራትና ንግግሮች ዙሪያ ሊኾን ግድ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህኛው ንዑስ ርዕስ ክርስቶስ በዓለማችን ከተከሰቱ ታላላቅ ሰዎች አንዱ ነው እንጂ የተለየ አይደለም፤ ስለኾነም አምላክ ብለን ልንጠራው፣  ልናከብረውና ልናመልከው አይገባም፡፡› ከሚሉት ጋር እንከራከራለን፡፡ ምክንያቱያም ክርስቶስ አምላክ ሳይኾን በዓለማችን እንደተከሰቱት እንደ እነ ሙሴ፣ ሶቅራጥስ፣ ቡድሃ፣ ሙሐመድ፣ ኮንፊሽየስና መሰል ሰዎች ዓይነት ሰው ብቻ ከኾነ በአምላክነቱ የእግዚአብሔርን መኖር ያረጋግጣልና ያልነው ይሻራል፡፡ የክርስትና ሃይማኖትም የተመሠረተው በስህተት ላይ ነው ማለት ይኾናል፡፡ ስለዚህ ‹ክርስቶስ በዓለማችን ሰው በመኾን በታሪክ የተከሰተ አምላክ ነው ወይስ ከታላላቅ የሥነ ምግባር መምህራን  መካከል እንደ አንዱ ነው?› የሚለው ጥያቄ መመለስ አለበት፡፡

ለዚህ ጥያቄም ክርስቶስ በመሬት ላይ የሠራቸው ተግባራትና ትምህርቱ መልስ በመስጠት ይመሠክራሉ፡፡ ክርስቶስንም ልናውቀው የቻልነው በዋናነት በአስተማረው ትምህርትና ሌሎችም በትንቢትና በአስተምህሮ (በስብከት) በነገሩን መሠረት ነው፡፡ ትምርህቱና የፈጸማቸው ተግባራትም በወንጌል ተከትበው (ተጽፈው) ይገኛሉ፡፡ አምላክ ሳይኾን ጥሩ የሥነ ምግባር መምህር የነበረ ነው የሚሉትም መነሻ ማስረጃቸው የእሱው ትምህርትና ሌሎችም ስለ እሱ በመሠከሩት ተነስተው መኾን ይኖርበታል፡፡ ያለበለዚያ ጥሩ የሥነ ምግባር መምህር መኾኑን በምንና እንዴት ማወቅ ቻሉ?

የክርስቶስን በስብዕና መገለፅ (ህልውነት) ደግፎ የሚከራከር የትኛውም ሰውም አራት አማራጮች ብቻ ይኖሩታል፡፡ ከአራቱ አማራጮችም አንደኛው ኢየሱስ ክርስቶስ እሩቅ ብእሲ (ሰው ብቻ) ሳይኾን አምላክም መኾኑን ይመሠክራል፡፡ ሌሎቹ ግን ታላቅ የሥነ ምግባር መምህር መኾኑን ማሳየት አይችሉም፡፡ ለማንኛውም በክርስቶስ አስተምህሮና ተግባራት ዙሪያ ሊነሡ የሚችሉ አማራጭ አቋሞችን ተመልክተን ትክክል የኾነውን እንደግፍ፡፡:

 1.   ትምህርቱ ሐሰት ነው፤ ይህንንም ያውቃል፡፡

እንደዚህ አቋም ከኾነ ኢየሱስ ክርስቶስ አታልይ የኾነ ውሸታም ሰው እንጂ ታላቅ ሰው ተብሎ መከበር አይገባውም፡- እንኳን በአምላክነት ሊከበርና ሊመለክ ቀርቶ በውሸታምነቱ መጠየቅ አለበት፡፡ አታላይነቱን አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ የትምህርቱን ሐሰትነት በትክክል ጠንቅቆ የሚያውቅ መኾኑ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰው ሰይጣን ይባላል ወይስ ሌላ ምን ይባላል? አምላክ ሳይኾን አምላክ ነኝ ብሎ የሚዋሽ፣ በተግባር የፈጸመው አንድም የአምላክነት ተግባር ሳይኖር እፈፅማለሁ ወይም ፈፀምኩ ብሎ ከማታለል የበለጠ ምን መጥፎ ሥራ አለ? አይኖርም፡፡ ስለኾነም ይህ አማራጭ ትክክል ከኾነ ክርስቶስ በዓለማችን መጥፎ ሰዎች መካከል የመጀመሪያው ሰው ነው ማለት ይቻላል እንጂ በታላቅነታቸው ከሚታወቁ የዓለማችን ሰዎች ተርታ መመደብ የለበትም፡፡

2. ትምህርቱ ሐሰት ነው፤ ይህንን ግን አያውቅም፡፡

በዚህ አማራጭ መሠረት ደግሞ ክርስቶስ አዕምሮው የቀወሰ ሰው እንጂ ሌላ ሊባል አይገባውም፡፡ ምክንያቱም ትምህርቱ ሐሰት እሱንም የማያውቀው ከኾነ ንክ ወይም ቀወስ  እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡ ጤነኛ ሰው ቢያንስ የሚያስተምረው ስህተት መኾኑን ያውቃል፤ ሐሰተኛ ትምህርት እያስተማረ መኾኑን ካላወቀና ለተሳሳተ ነገር ሳያውቅ ከሞተ ምን ይባላል? ቀወስ እነጂ፡፡ ይህንን ዓይነት ሰውም ከታላላቅ ሰዎች ጋር አብሮ መመደብ ስህተት ነው፡፡ ታላቅነት እንዴት በቀውስነት ይገኛል? ስለዚህ እንኳን አምላክ ልንለው ከተራ ሰው እኩልም መመደብ ስህተት ነው፡፡

3.  ትምህርቱ እውነት ነው፤ ይህንን ግን አያውቅም፡፡

ይህ ደግሞ የባሰበት ነው፡፡ በአማራጭነትም ለመውሰድ አይመችም፡፡ ቆይ እሱ የማያውቀውን እውነት የሚያስተምረው እንዴት ኾኖ ነው? በዕድል ነው የሚያስተምረውና የሚፈፅመው ነገር እውነት የኾነው? እንዴትስ ሳያውቅ ስለ የባሕርይ አምላክነቱ ያስተምራል? ዕውቀት የሌለው አምላክ አለ እንዴ? ደግሞስ እሱ ያላወቀውን ትምህርት እኛ እንዴት እውነትነቱን ማወቅ ቻልን? ብዙ ጥያቄዎችን ይጎለጉላል፡፡ ስለዚህ ይህ አማራጭ ለነቃፊዎች እንኳን የማይመች መስደቢያም ሊሆናቸው የማይችል ነው፡፡

ስለዚህ በክርሰቶስ ባለን አቋም፣ እምነትና ግንዛቤ ላይ የሚኖረን አንድ አማራጭ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ያሉት አማራጮች ሊሠሩ የሚችሉት አንድም ውሸታም ሰው ነው ብለን ከደመደምን ወይም ጤነኛ ሰው አይደለም ቀውስ ነበር ብለን እሱ ያስተማረውንም ኾነ ሌሎቹ ስለ እሱ ያስተማሩትን ትምህርት ሙሉ ለሙሉ የተሳሳተ መኾኑን ከተቀበልን ነው፡፡ በእነዚህ አማራጮች ደግሞ ክርስቶስ ታላቅ የሥነ ምግባር መምህር መኾን የሚችልበት ሥፍራ የለውም፡- ተቃራኒው እንጂ፡፡ ከነእዚህ ይልቅ ሙሉ በሙሉ ክርስቶስ የሚባል ሰው አልነበረው በማለት ዓይኔን ግንባር ያድርገው፤ ጆሬዬንም ይድፈነው በማለት የካደው አቋም ይሻላል፡- እንበል? እሱ ደግሞ እንደማያስኬድ ተመለክተናል፡፡ ስለዚህ የሚቀረን አማራጭ ኢየሱስ ክርስቶስ በስብዕና የሚያስተምረውን ጠንቅቆ የሚያውቅ እውነተኛ መምህር ነው የሚለው ነው፡፡

4.  ትምህርቱ እውነት ነው፤ ይህንንም ያውቃል፡፡

በዚህ አማራጭ መሠረት ክርስቶስ በመሬት  በመቆየት ያስተማራቸው ትምህርቶችና የፈፀማቸው ተግባራት ትክክልና እውነት የኾኑ ናቸው፤ እናም እነዚህንም ጠንቅቆ በማወቅ ሲተገብራቸው ኖሯል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ደግሞ ስለ ራሱ የባሕርይ አምላክነት ተናግሯል፤ የሠራውም የአምላክነት ተግባር መኾኑ በተከታዮቹና በሌሎች ጭምር ተመሥክሮለታል፡፡ ይህ ከኾነም ክርሰቶስ የባሕርይ አምላክ እግዚአብሔር ነው እንጂ እንደሌሎቹ ታላላቅ ሰዎች ዓይነት እሩቅ ብዕሲ (ሰው ብቻ) አይደለም፡፡ ቆይ እሱ የተናገው እውነት ነው ብለን ከተቀበልን፣ እሱ ራሱና ያስተማራቸው ተከታዮቹ ስለ እግዚአብሔርነቱ ከመሰከሩ ‹ታላቅ ሰው እንጂ አምላክ አይደለም› የምንልበት አግባብ ምንድነው? እራሳችንን ዋሾ እያደረግን አይኾንም?

በአጠቃለይ ስንመከተው ክርስቶስ ውሸታም ወይም ቀውስ የነበረ ሰው ስለመኾኑ ምንም ዓይነት ማስረጃ የለም፤ አመክንዮአዊ መከራከሪያም አይደለም፡፡ ስለኾነም እነዚህ የዋሾነትና የዕብደት አማራጮች ለክርስቶስ ማንነት እንዳማራጭ ኾነው መቅረብ አይችሉም፡- ምንም ዓይነት ጥላቻ ቢኖርም እንኳ፤ ወይ መካድ ነው የተሻለው፡፡ በሌላ በኩል ክርስቶስ በስብዕና በዓለማችን ላይ በቆየበት ጊዜ አምላክነቱን በቃልም በግብርም መግለፁን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች ደግሞ በብዛት አሉ፡፡ እነዚህ ማስረጃዎችም ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ መኾኑንም እንጂ ሰው መኾኑን በመግለፅ ብቻ የተወሰኑ አይደሉም፡፡ ለአብነትም ከዚህ በታች የተጠቀሱት ምክንያታዊ ማስረጃዎች በቂ ይመስሉኛል፡፡ ስለዚህ ክርስቶስ ሰው የኾነ አምላክ እግዚእብሔር ነው፡፡ ይህ ከኾነም ሰዎችን ለማዳን ክርስቶስ በስብዕና መገለፁ የእግዚአብሔርን ህልውነት አረጋጋጭ ብቻ ሳይኾን የሞራላዊ ጠባያቱን መመዛዘንና መጣጣም ማሳያም ነው፡፡

3ኛ. የክርስቶስ እግዚአብሔርነት[3]

  ዕዝል ጉባኤ ቃና

አይሁድ እግዚአ ኢረሰይዎ ለወልደ አምላክ ልዑል፣

እስመ ምስለ ኖሎት ይመውዕል እንዘ ይሰክብ በጎል፡፡

ትርጉም፡-

አይሁድ የልዑል አምላክ ልጅን ጌታ አላደረጉትም፣

በበረት እየተኛ ከእረኞች ጋር ይውላልና፡፡[4]

የክርስቶስ የባሕርይ አምላክ (እግዚአብሔር) መኾን የመጽሐፍ ቅዱስ  (በተለይም የሐዲስ ኪዳን) ዋና ማጠንጠኛ  ዕንብርት ነው፡፡ ክርስቶስ ራሱ ያስተማረውና ስለእሱ በሌሎች የተነገሩ ትምህርቶችም አምላክ (እግዚአብሔር) መኾኑን መስካሪዎች ናቸው፡፡ ለዚህም ተመዝግበው የሚገኙ መረጃዎችን በተጠየቅ ማየት በቂ ነው፡፡

 ተጠየቃዊ ሙግት

 1. እግዚአብሔር አንድ ብቻ ነው፡፡
 2. ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡
 3. ስለዚህ አንዱ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ማብራሪያ፡-

I.  እግዚአብሔር አንድ ብቻ ነው፡፡

 1. በፍልስፍና አስተምህሮ እግዚአብሔር ካለ አንድ ብቻ መኾኑ ተቀባይነት አለው፡፡

ከአንድ በላይ የመለኮትነት ባሕርይ ያለው ፈጣሪ ይኖራል ብሎ ማመን አመክንዮዊ ተቀባይነት የለውም፤ ከአንድ በላይ አምላክ ሊኖር እንደሚችል ማሳየትም አይቻልም፡፡ ምክንያቱም፡-

v  ከአንድ በላይ አምልክ ቢኖር ኖሮ አንድ ዓለመ-ፍጥረት መኖር አይችልም ነበር፡፡ መኖር ቢችልና የተለያየ ዓለማተ ፍጥረት ፈጣሪዎችና ገዥዎች የኾኑ የተለያዩ አማልክት ቢኖሩም አንደኛ ውስንነት ይኖርባቸዋል፤ በመኾኑም የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት ባለቤት መኾን አይችሉም፤ የተዋረድ የአምላክነት ማዕረግ መስጠትም ውስንነትን ማሳያ ነው፤

v   ሁለተኛም ተስማምተው መኖር አይችሉም፤ ዓለማተ-ፍጥረቱ የጦርነትና የብጥብጥ መድረክ ይኾኑ ነበር እንጂ፤ የሕግና ሥርዓት አኗኗርም አይኖራቸውም፡፡

 1. በአብዛኛው የሃይማኖት አስተምህሮ መሠረት የአንድ አምላክ መኖር ነው፡፡

v  በዓለም ላይ ባሉ ታላላቅ ሃይማኖቶች ኹሉ የሚታመነው አንድ እግዚአብሔር (አምላክ) ብቻ እንዳለ ነው፡፡ ምክንያቱም ሃይማኖት ከአምላክ ጋር የሚደረግ ግኑኝነት ነውና፡፡ የዓለማችን ዋና ዋና ሃይማኖቶች የኾኑት የአይሁድ እምነት፣ እስልምና እና ክርስትና የአስተምህሮ መሠረታቸው  አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን  በማመን ላይ የቆመ ነው፡፡ የአይሁዳዊያንና የክርስቲያኖች የጋራ ቅዱስ መጽሐፍ የኾነ የብሉይ ኪዳንም አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን በመመስከር ማረጋገጫ ይሠጣል፡፡[5] የአሥርቱ ትዕዛዛት መሠረታቸው በአንድ አምላክ ማመን ነው፡፡…

 1. ክርስቲያኖች ብቻ በሚቀበሉት በአዲስ ኪዳንም ቢኾን አንድ እግዚአብሔር ብቻ መኖሩ በግልጽ ተጽፎ ይገኛል፡፡[6]
 2. ስለዚህ የሚመለክ እግዚአብሔር አንድ ብቻ ነው፡፡

II.  ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ከዚህ በታች በተጠየቅ የቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎች የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክነት የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት ኹሉ የክርስቶስም መታወቂያ ጠባያት ናቸውና፡፡ ለምሳሌም ኢየሱስ ክርስቶስ፡-

2.1.   በእግዚአብሔር ቃልነቱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ተጠየቃዊ ሙግት

v  የእግዚአብሔር ቃል እግዚአብሔር ነው፡፡

v  ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡

v  ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ኢግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

üየእግዚአብሔር ቃል ከእግዚአብሔርነቱ የተለየ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቃል የሚባለውም የእሱው ጥበብ፣ ዕውቀት፣ ኃይልና ምክንያት ነው፡፡ የእግዚአብሔር ጥበብ፣ ዕውቀትና ምክንያትም በፍጽምና ከራሱ ጋር ለዘላለም የሚኖር እንጂ እግዚአብሔር ጥበበኛ ሳይኾን ኖሮ ኋላ ጥበበኛነትን ያገኘ ዕውቀትም ሳይኖረው ቀርቶ ኋላ ዕውቀትን ማወቅ የቻለ ወይም ምክንያታዊነት የሌለው ግብታዊ አምልክ ኾኖ የኖረና የሚኖር አይደለም፡፡ በተጨማሪም ቃሉ እግዚአብሔር መኾኑና ፍጥረት ኹሉ የተፈጠረውም በእሱ እንደኾነ በግልፅ ተፅፎ ይገኛል፡፡[7]

ü  ኢየሱስ ክርስቶስ ተብሎ የተጠራው ሰው በመኾን የተገለፀውም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡[8] ይህም በግልፅ   ተቀምጧል፡፡

üይህም የሚያሳየው ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እግዚእብሔር መኾኑን ነው፡፡

2.2.   በእግዚአብሔር ልጅነቱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ተጠየቃዊ ሙግት

v  የሰው የባሕርይ ልጅ ሰው እንደኾነው ኹሉ የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅም እግዚአብሔር ነው፡፡

v  ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡

v  ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

üበቀላል ንጽጽር ብንመለከት ሰው የሚወልደው ሰውን ነው እንጂ እንስሳ ወይም ሌላ ነገር አደለም፤ እንስሳም እንደዚሁ እንስሳን ብቻ ነው የሚወልደው፡፡ ምንም እንኳን በጉደፈቻ፣ አስተምሮ በቀለም አባት በመኾን ወዘተ… የሚገኙ የፀጋ ልጅነቶች ቢኖሩም ባሕሪያዊ ልጅነትን አያስገኙም፡፡ እግዚአብሔርም ሰዎችን ልጆቼ በማለት የሚጠራቸው እነሱም አባታችን በማለት የሚጠሩት በፀጋ ልጅነታቸው ነው፡፡‹ለተቀበሉት ኹሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይኾኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፡፡› እንዲል፡፡ እግዚአብሔር ግን በባሕርዩ የሚወልደው ልጅ ራሱ እግዚአብሔር ሊኾን የግድ ነው፡፡ ያ ማለት ደግሞ የእግዚአብሔር መታወቂያ ጠባያት ኹሉ ልጁም ይኖሩታል፡፡ (በመሠረቱ ይህ ሐሣብ የምሥጢረ ሥላሴ ትምህርት ስለኾነ ለብዙ ሰው ግር ሊል እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡) ነገር ግን እግዚአብሔር ልጅ አለው የምንል ከኾነ የልጁንም እግዚአብሔርነት መቀበል የግድ ነው፡፡ ያ ማለት አባትና ልጅ በባሕርይ አንድ ናቸው፤ አንድ የእግዚአብሔርነት ባህርይ አላቸው ወይም ገንዘብ ያደርጋሉ፡፡[9]  የእግዚአብሔር  አባትነት በዘላለማዊነት እንደኾነ ኹሉ ልጅነቱም ለዘላለም ነው፤ በሌሎችም የእግዚአብሔር ጠባያት እንደዚሁ፡፡

üኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለመኾኑ ራሱ አባቱ አብ ምስክርነትን ሰጥቷል፡፡[10] የክርስትና ሃይማኖትም የተመሠረተው ኢየሱስ ክርስቶስን የእግዚአብሔር ልጅ ብሎ በማመን ላይ ነው፤ ሕይወትም የሚገኘው በእሱ ነው፡፡ እግዚአብሔርም ትልቅ ፍቅሩን የገለፀው ልጁን በመላኩ ነው፡፡[11] ክርስቶስ የስቅላት ፍርድ የተፈረደበት ‹ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ› በማለት እግዚአብሔርን ተሳድቧል በሚል ነው፡፡[12] እንዲሁም የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅነቱን ኢሳያስ[13]፤ መልአኩ ገብረኤል[14]፤  መጥምቀ ዮሐንስ[15]፤ ሐዋሪያው ቅ.ናትናኤል[16]፤ ቅ.ጳውሎስ[17] እና ሌሎችም[18] መስክረዋል፡፡

በአጠቃላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ መኾኑ እግዚአብሔር አብ በምስክርነት ያረጋገጠው፣ የሐዋሪያት አስተምህሮ መሠረት፣ ራሱ ክርስቶስም የመሰከረውና ራሱን የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ብሏል በማለት ካህናት በስቅላት እንዲቀጣ ያስፈረዱበት ዋና የወንጌል ትምህርት ማጠንጠኛ ነው፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹እኔና አብ አንድ ነን› እንዳለው እግዚአብሔር አብን በባህርይ የሚመስለው፣ በሥልጣን የሚስተካከለው  እግዚአብሔር ነው፡፡

2.3.   በፈጣሪነቱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ተጠየቃዊ ሙግት

v  የሰማይና ምድር ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው፡፡

v  ፍጥረት ኹሉ የተፈጠረው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

v  ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

በመጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ፍጥረትን ኹሉ መፍጠሩ በግልፅ ተቀምጧል፡፡  ሰማያትና ምድር ከእነ ግሳንግስ ፍጥረቶቻቸው በእግዚአብሔር መፈጣራቸውን ማስተዋል ፈጣሪነቱን  ለመረዳት በቂ ነው፡፡[19]

እግዚአብሔር ፍጥረቱን ኹሉ የፈጠረው በቃሉ በመጠበብ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ቃል የኾነው ዕውቀቱ፣ ጥበቡና ኃይሉ ደግሞ ኢየሱስ ክርሰቶስ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ ፍጥረት ኹሉም ፍጥረት በኢየሱስ ክርስቶስ የተፈጠረ ነው ማለት አሳማኝነት አለው፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም በቂ ምስክርነት ይሠጣሉ፡፡[20]

2.4.     በዘላለማዊነቱ (ጊዜ የማይወስነው በመኾኑ፣ መጀመሪያውና መጨረሻው በመኾኑ) እግዚአብሔር ነው፡፡

ተጠየቃዊ ሙግት

v የኹሉም ነገር መጀመሪያና መጨረሻ እግዚአብሔር ነው፡- ከእሱ በፊትና በኋላ ምንም ነገር የለም፡፡

v ኢየሱስ ክርስቶስ ጊዜ የማይወስነው፣ አልፋና ኦሜጋ (ቀዳማዊና ዳኅራዊ) ነው፡፡

v ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

በዚህ አገላለፅ መጀመሪያ ማለት መነሻ የሌለው ቀዳሚ ማለት ሲኾን መጨረሻ ማለት ደግሞ ፍፃሜ የሌለው ዘላለማዊ ማለት ነው፡፡ ይህም ከጊዜ ክስተት ውጪ ማለትን ይጨምራል፡፡ ይህም የእግዚአብሔር የባህርዩ መታወቂያ ጠባይ ነው፡፡[21]

ከዚህ በላይ የተመለከትነው የእግዚአብሔር ዘላለማዊነት ጠባይ ለክርስቶስም ቃል በቃል ተጠቅሰው እናገኛቸዋለን፡፡[22]

ይህ ከኾነም ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር መኾኑ ምንም ጥርጥር የለበትም፡፡

2.5.  በሥልጣኑ (በተፈጥሮ ላይ፣ በመልአክት ላይ፣ በአጋንንት ላይ፣ በሞት ላይ፣ በሕግጋት ላይ፣ ሰማይና ምድርን በመግዛት፣ በራሱ ላይ፣…) እግዚአብሔር ነው፡፡

ተጠየቃዊ ሙግት

v  በኹሉም ነገር ላይ ሥልጣን ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

v  ኢየሱስ ክርስቶስ በየትኛውም ነገር ላይ ሥልጣን አለው፡፡

v  ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

ሰማይና ምድርን ከእነ ሠራዊታቸውና ከረቂቃን እስከ ግዙፋን አካላት ከመፍጠር ጀምሮ እስከ ማስተዳደርና መጠበቅ ድረስ ሥልጣንና ኃይል ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስም በተለያዩ ክስተቶች ላይ ሥልጣኑን አሳይቷል፡፡ ለምሳሌም፡-

 1. በፍጥረት ላይ፡- ለምሳሌ ነፋሳትና ማዕበላትን በሥልጣኑ በማዘዝ[23]፣ ከተፈጥሮ ሕግ ውጭ በውሃ ላይ በመራመድ[24]፣ መሬትን ለቆ ወደ ሰማይ በማዕረግ[25]፣ የለመለመች ዕፅን ረግሞ ወዲያው በማድረቅ[26]… ሥልጣኑን አሳይቷል፤ በሥቅለቱ የተፈጠረ ክስተት[27]፣ በቃሉ ብቻ የፈፀማቸው ታምራትም … ምስክሮች ናቸው፡፡
 2.  በመልአክት ላይ፡- መላዕክት ኹሉ ለእሱ መስገዳቸው[28]፣ የሚያገለግሉት መኾኑ [29]፣ መገዛታቸው[30]፣ መታዘዛቸው[31]
 3. በሕይወት ላይ[32]
 4. በሞት ላይ[33]
 5. በሕግጋት ላይ፡- የኦሪትን ሕግጋት በማሻሻል[34]፣ ከሰንበት በላይ በመኾኑ[35]፣ በአጠቃላይ እንደ ኦሪት ነበያት ‹እግዚአብሔር እንዲህ ይላል› ሳይል እንደ ባለሥልጣን ‹እኔ ግን እንዲህ እላችሁ› በማለት ማስተማሩ…
 6.  በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ፡- ‹መንግሥትህ ትምጣ› እያልን የምንፀልየው ለእሱ መኾኑ[36]፣ መንግሥቱም ዘላለማዊ ሰማያዊ መኾኑ[37]….
 7.  በራሱ ላይ፡- ነፍሱን ከሥጋው በራሱ ሥልጣን በመለየቱ[38]
 8. የሰማይና ምድር ሥልጣን ያለው መኾኑ፡-[39] ወዘተ…

እነዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ በሥልጣኑ የፈጸማቸው ድርጊቶችና የተናገራቸው ምክሮች እግዚአብሔር መኾኑን ይመሰክራሉ፡፡

2.6.   በጌትነቱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ጠየቃዊ ሙግት

v  ጌታ የሚለው መጠሪያ ከእግዚአብሔር ስሞች አንዱ ነው፡፡

v ኢየሱስ ክርሰቶስም አምላክነትን በሚያሚያመለክት ጌታ እየተባለ ተጠርቷል፡፡፡

v ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር አምላክ ነው፡፡

ማብራሪያ

በመለኮትነት ጌትነት የባህርዩ የኾነ አምላክ አንድ መኾኑንን ራሱ እግዚአብሔር በማስጠንቀቅ ያሳወቀው[40]፣ ኢየሱስ ክርስቶስም ያረጋገጠው[41] ሐቅ ነው፡፡

የባሕርይ አምላክ መገለጫ የኾነው የጌትነት ስም ኢየሱስ ክርስቶስም ተጠርቶበታል፡፡ ለምሳሌም በጌትነት በአብ ቀኝ በመቀመጡ[42] (እኩል ወይም አንድ መኾኑ)፣ የክብር ጌታ በመኾኑ [43]፣ የጌቶች ጌታ በመባሉ[44]፣ የሰንበት ጌታ በመኾኑ[45]፣ በጌትነቱ የሚታመንበትና የሚለመን በመኾኑ[46]፣ ለፍርድ በግርማ መለኮቱ በመምጣቱ[47]፣…..ጌትነቱን አረጋግጧል፡፡

ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ የጌቶች ጌታ የኾነው እግዚአብሔር አምላክ ነው፡፡

2.7.   የዘላለማዊ ክብር ባለቤት በመኾኑ እግዚአብሔር ነው፡፡

ተጠየቃዊ ሙግት

v  ዘላለማዊ ክብር ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

v  ኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለማዊ ክብር ባለቤት ነው፡፡

v  ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ኢግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

ለዘላለም በመለኮታዊ ክብር የሚኖር እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ይህን ክብሩንም ማንም ማን ሊጋራውና ሊያገኘው (ሊኖረው) አይችልም፡፡[48] የመለኮቱ ነፀብራቅ መገለጫው ነውና፡፡ ፍጡራን ሁልም ከዚህ ክብር በፀጋ ለማግኘት ይለምናሉ፤ ተካፋይ በመሆናቸውም ያመሰግናሉ፡፡[49]

ኢየሱስ ክርስቶስ በአባቱ ቀኝ በክብር መቀመጡ[50]፣ በክብር በመልአክት መለከት እያስነፋ ለፍርድ መምጣቱ[51]፣ ዓለም ሳይፈጠር በፊት በነረው ክብር ባባቱ መከበሩ[52]፣ ዘላለማዊ ክብር ያለው መኾኑና የሐዋሪያት ምስጋና ማሰረጊያቸውም የእሱ ክብር መኾኑ[53]…. የዘላለማዊ ክብር ባለቤት መኾኑን ማሳያዎች ናቸው፡፡

በዚህ የተነሣም ኢየሱስ ክርስቶስ የክብር ባለቤት የኾነው ኢግዚአብሔር ነው ለማለት እንችላለን፡፡

2.8.   በመመለኩና ፀሎትን በመቀበሉ እግዚአብሔር ነው፡፡

        ተጠየቃዊ ሙግት

v  መመለክ የሚገባው አምላክ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

v  ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመለክ ጌታ ነው፡፡

v  ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

ከዚህ በላይ በተደጋጋሚ እንደተገፀው የባሕርይ አምላክ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ስለኾነ ሊሰገድለትና ሊመለክ የሚገባውም እሱ ብቻ ነው፡፡ ይህ ከአሥርቱ ትዕዛዛት መካከልም አንዱና የመጀመሪያው ነው፤ በአምልኮት ጉዳይ ላይ እግዚአብሔር ቀናተኛም ስለኾነ ‹እግዚአብሔር በአምልኮቱ፣ ንጉሥ በመንግሥቱ፣ ጎረምሳ በሚስቱ ሲመጡባቸው› አይወዱም፤ አይታገሱም ይባላል፡፡ ከአንዱ እግዚአብሔር ውጭ አምልኮት የሚፈጽምም ጣኦት ማምለክ ነው፡፡ ስለኾነም የሚመለክ ጌታ እግዚአብሔር ብቻ መኾኑ ምንም ጥያቄ የሌለው እሙን ነገር ነው፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስም በአምልኮት በዘላማዊነት የሚመሰገን መኾኑ[54]፣ በእሱ የባሕርይ አምላክነትና አዳኝነት ማመን የዘላለም ሕይወትን የሚያስገኝ መኾኑ[55]፣ ስግደትና ፀሎትን የሚቀበል መኾኑ[56]፣ … አምልኮት የሚገባው አምላክ መኾኑን ይመሠክራል፡፡

2.9.   ምሉዕ በኩለሄ በመኾኑ እግዚአብሔር ነው፡-

  ተጠየቃዊ ሙግት

v     እግዚአብሔር ብቻ ኹሉም ሥፍራ መገኘት ይችላል፡፡

v    ኢየሱስ ክርስቶስ በየትኛው ሥፍራ ይገኛል፡፡

v    ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

ከእግዚአብሔር ጠባያት አንዱ በኹሉም ሥፍራ ምንም ነገር ሳያግደው በአንድ ጊዜ መገኘት መቻል ነው፡፡[57]

ኢየሱስ ክርስቶስም በሰማያት ኾኖ በመሬት በሐዋሪያትና በምዕመናን ዘንድ ነበር፤ አለም[58]፣ ዘመን ሳይገድበውም በጥንት ጊዜ ነበር፤ ይኖራልም[59]

ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ሥፍራ የማይወስነው እግዚአብሔር ነው፡፡

2.10.  በሞራላዊ ጠባያቱ እግዚአብሔር ነው፡፡

2.10.1.    ደግና ቅዱስ በመኾኑ እግዚአብሔር ነው፡፡

ተጠየቃዊ ሙግት

v   ቅዱስነትና ደግነት የባህሪዩ የኾነ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

v  ኢየሱስ ክርስቶስ በባህርዩ ቅዱስና ደግ ነው፡፡

v  ስለዚህ ኢየሰሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

በቅድስናው ፍፁም የኾነ እግዚአብሔር ብቻ ለመኾኑ አጨቃጫቂ አይደለም፡- እሙን ነው፡፡[60] የሌሎች ፍጥረታት (የመልአክት፣ የሰዎች፣…) ቅድስና ግን የፀጋ (የሥጦታ) ቅድስና ስለኾነ ሕፀፅ አለበት፡፡ ደግነትም እንደዚሁ፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔር የባሕርይ ቅድስናና መልካምነት መገለጫዎችም  ክርስቶስ አሉት፡፡[61]  ስለዚህ ኢየሰሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ባሕርይ የሞራል ጠባያት ገንዘብ ያደረገ  እግዚአብሔር ነው፡፡

2.10.2.   ኃጢያትን ይቅር በማለቱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ተጠየቃዊ ሙግት

v   እግዚአብሔር ብቻ የሰዎችን ኹሉ ኃጢያት ይቅር በማለት የመማር ሥልጣን አለው፡፡

v  ኢየሱስ ክርስቶስ ኃጢያትን ኹሉ ይቅር ይላል፡፡

v  ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

ምንም እንኳን ካህናት የሰዎችን ኃጢያት በማናዘዝ ተቀብለው ለእግዚአብሔር ቢያቀርቡም በራሳቸው የሰው ልጆችን ኹሉ ይቅር ብለው መማር አይችሉም፡፡ ስለኾነም ኃያጢያትን ኹሉ ይቅር በማለት የሚምረው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡[62] ምክንያቱም ኃጢያት ቅዱስ የኾነ ሕግን መተላለፍ ስለኾነ በደል ነው፡፡ ይህንን በደልም በአግባቡ ለይቶ በማወቅ ከጠባያቱ ጋር የተጣጣመ የይቅርታ ፍርድን መስጠት የሚችል እግዚአብሔር ነውና፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በራሱ ሥልጣን ይቅርታን ለሰዎች ሰጥቷል፡፡ ለምሳሌም በታምራት የፈወሳቸውን ሰዎች ኃጢያታቸው አንደተሰረየላቸው በመግለፅ[63]፣ አብሮት የተሰቀለውን ወንበዴ ገነትን እንደሚገባ በእርግጠኝነት በመግለፅ[64]፣…ኃጢያትን ኹሉ በራሱ ይቅር ብሏል፡፡ ይህን ማድረግ ከቻለም ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

2.10.3.   በፈራጅነቱ እግዚአብሔር ነው፡፡

ተጠየቃዊ ሙግት

2.10.4.  እግዚአብሔር ብቻ በኹሉም ሰው ላይ መፍረድ ይችላል፡፡

2.10.5.  ኢየሱስ ክርስቶስ የዓለም ፈራጅ ነው፡፡

2.10.6.  ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

እግዚአብሔር ልብ ያሰበውን አዕምሮ ያመላለሰውን ምንም ሳያስቀር ስለሚያውቅ በማንኛውም ተግባር ላይ ትክክለኛ ፍርድ መስጠት ይችላል፤ ይህንንም በግልፅ ተናሯል፡፡[65]

ወንጌል በምጽአት (በዓለም መጨረሻ) በሰዎች ኹሉ ላይ እንደሥራቸው የሚፈርድ ኢየሱስ ክርስቶስ መኾኑን ይመሰክራል፡፡[66] ይህንን ማድረግ የሚችል ከኾነም  ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

2.11.  ኹሉንም ነገር መርምሮ የሚያውቅ በመኾኑ እግዚአብሔር ነው፡፡

ተጠየቃዊ ሙግት

9.1.  እግዚአብሔር ብቻ በሰዎች አዕምሮ የሚታሰበውን ሐሣብ ኹሉ ያውቃል፡፡

9.2. ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ኹሉ የሚያስቡትን መርምሮ ያውቃል፡፡

9.3. ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

ማብራሪያ

ሰው ምሥጢር የኾነ ፍጡር ስለኾነ ልቡንና ኩላሊቱን በመመርመር ማንነቱን፣ ተግበራቱንና የሐሳቡን የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡[67]

ኢየሲስ ክርስቶስ በመሬት ላይ በነበረ ጊዜ የሰዎችን ሐሣብ ያውቅ ነበር [68]፣ በሰዎች ልብ የሚስተዋለውንና በአዕምሮ የሚታወቀውን መርምሮ ያውቃል[69] … ፡፡ ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ ኹሉን ነገር ምንም ሳያስቀር የሚያውቀው እግዚአብሔር ነው፡፡

2.12.  ኹሉን ቻይነት ባህርዩ (በስብዕና በመገለጡና በኃያልነቱ) እግዚአብሔር ነው፡

ተጠየቃዊ ሙግት

v  ኹሉን ነገር ማድረግና መኾን የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

v  ኢየሱስ ክርስቶስ በስብዕና የተገለጠ ኹሉን የማድረግ ሥልጣን ያለው ነው፡፡

v  ስለዚህ የኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

2.13.  የዓለም አዳኝና መድኃኒት በመኾኑ እግዚአብሔር ነው፡፡

ተጠየቃዊ ሙግት

v  መድኃኒት በመኾን ዓለምን ሊያድን የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡

v  ኢየሱስ ክርሰቶስ የዓለም አዳኝ መድኃኒት ነው፡፡

v  ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚእብሔር ነው፡፡

2.14.  በአደረገው ታምራቱ የተነሣ እግዚአብሔር ነው፡፡

  ተጠየቃዊ ሙግት

v  በሥልጣኑ የተለያዩ ታምራት የሚፈፅም እግዚአብሔር ነው፡፡

v  ኢየሱስ ክርስቶስ በሥልጣኑ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ታምራትን ፈፅሟል፡፡

v  ስለዚህ ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ነው፡፡

III. ስለዚህ አንዱ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

እነዚህ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ተጠየቆች  ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ እግዚአብሔር መኾኑን ይመሠክራሉ፡፡ ይህ ከኾነም በኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ የሚኖረን ትክክለኛ አቋም ‹ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው የኾነ አምላክ፣ እግዚአብሔር ነው፡፡› የሚል መኾኑ የግድ ነው፡፡


[1] የግእዝ ቅኔያት የሥነ ጥበብ ቅርስ ገፅ 129-130

[2] እጓለ ገ/ዮሐንስ፤ፍቅረ ድንግል በየነ በ‹ የምሣሌያዊ ንግግሮች ሰዋሰው፡-ሰምና ወርቅ ሰዋሰው› መጽሐፉ፣ገጽ 71 ካስቀመጠው የተወሰደ፡፡

[3] ይህንን ንዑስ ርዕስ በሰፊው ለመረዳት H.H. Pope Shenouda III(1989), The Divinity of Christ ; Coptic orthodox puplisher association 50 Nertherford Road London SW4 6AE እና የዲያቆን እሸቱ ታደሰ ወንድም አገኘሁ (1989)፣‹የክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት  ማንበብ ይጠቅማል፡፡

[4] የግእዝ ቅኔያት የሥነ ጥበብ ቅርስ 2፣ ገፅ 37

[5]ዘጸ.20*3፤ዘዳ.5*7፤ዘዳ.4*35፤ዘዳ.6*4፤ኢሳ43*10-11፤ኢሳ.44*6-7፤ ኢሳ.45*21-22፤ ኢሳ.46*9፤ ሆሴ.13*4….

[6] ሮሜ.3*30፤ 1ኛ ቆሮ.8*4፤ያዕ.2*19 …

[7] ዮሐ.1*1፣3፤ መዝ.33*6፤ምሳ.3*19፤ ዕብ.11*3፤…

[8]  ዮሐ.1*14፤ራዕ.19*12-13፤ቆላ.2*2-3፤1ኛቆሮ.1*24

[9] ምሳ.30*4፤መዝ.2*7፤ዕብ.1*2

[10] ማቴ.3*17፤ማር.9*7፤…

[11] ማቴ.16*13-18፤ዮሐ.20*31፤1ኛ ዮሐ.1*14፤4*9፣14፤5*12

[12] ማቴ.26*23-25

[13] ኢሳ.9*6

[14] ሉቃ.1*35

[15] ዮሐ.1*34

[16] የሐ.1*49-50፤3,9፤4,15፤5,5፣20

[17] ዕብ.1*5፤ ሮሜ.5*10…

[18]ማቴ.4,3፣6፤8,29፤14,35፤ማር.1,1፤3,11፤15,39፤የሐ.5,25፤6,69፤10,36፤11,4፤19,3፤20,3

[19] ዘፍ.1*1፤ መዝ.33*6፤ መዝ.148*4፤ ኢሳ.42*5፤ ኢሳ.44*24፤ ኢሳ.45*18፤ 10*12…

[20] ዮሐ.1*3፤ዕብ.1*2፣11*2፤ቆላ.1*15-16፤1ኛቆሮ.8*6…

[21] ዘጸ.3*14፤ ኢሳ.43*10፤ኢሳ.44*6፤ኢሳ.48*13

[22] ዮሐ.1*1፣3፣14፤ራዕ.1*7-8፣1*17፣22*12-16…

[23] ማር.4*37-41፤የሐ.6*17-119፤ማር.6*47-51

[24] ማቴ.14*25-32

[25] የሐ.ሥ.1*9

[26] ማቴ.21*19

[27] ማቴ.27*51፤ ማር.15*32፤ ሉቃ.23*44-45

[28] ዕብ.1*6፤ ፊል.2*10

[29] ማቴ.4*11፤ ማር.1*13

[30] 1ኛ ጴጥ.3*21-23

[31] ማቴ.13*41-42፤24*30-31፤ ራዕ.1*1፤ 22*6

[32] ዮሐ.1*4፤3*16-17፤5*21፤6*33-35፤10*27-28፤11*25-26፤ 14*6 …

[33] ዮሐ.8*51፤ሮሜ.5*10-12፣18፤2ኛጢሞ.1*10፤ራዕ.1*18፤ ዮሐ.20*51…

[34] ማቴ.5*21-22-

[35] ማር.2*28፤ሉቃ.6*5

[36] ማቴ.6*10፣13፤13*40-42፤16*28

[37] 2ኛ ጢሞ.4*1፤ዳን.7*14

[38] ዮሐ.10*17-18

[39]  ማቴ.28*18፤1ኛ ጴጥ.4*11፤12*10

[40] ዘዳ.10*16-17፤ኢሳ.45*21

[41] ሉቃ.4*10፣12

[42] ማቴ.22*43-46፤ሮሜ.8*34፤

[43] 1ኛ ጴጥ.3*18፤ያዕ.2*1፤1ኛቆሮ.2*8

[44] ራዕ.17*14፤19*16

[45] ማቴ.12*1-8

[46] ሉቃ.23*42፤ዮሐ.20*29፤የሐዋ.7*59፤16*25-34፤…

[47] ማቴ.7*22-23፤25*37፣44፤…

[48] ኢሳ.42*8

[49] ኢሳ.6*3

[50] የሐዋ.7*56፤ኤፌ.1*21-22፤ሮሜ.8*34፤ራዕ.3*21፤7*17…

[51] ማቴ.16*27፤25*31-32፤ሉቃ.9*26፤…

[52] ዮሐ.17*4-5

[53] 1ኛ ጴጥ.4*15፤2ኛ ጴጥ.3*18፤ይሁ.25…

[54] 1ኛ ጴጥ.4*15፤2ኛ ጴጥ.3*18፤ይሁ.25

[55] የሐ.3*16፣36፤11*25-26፤14*1፤የሐዋ.2*38፤ 10*43፤13*38፤ ሮሜ.9*33፤10*11፤…

[56] ማቴ.3*11፤14*33፤28*9፣17፤ ማር.5*23፣38፤41-42፤ሉቃ.5*38፤ዮሐ.14*13-14፤ 16*23-24፤ ፊል.2*10-11፤…

[57] መዝ.138*7-10፤ኢሳ.66*1፤1ኛ ነገ.8*27፤…

[58]ዮሐ.3*13፤14*23፤ማቴ.18*20፤28*20፤ሉቃ.23*43፤የሐዋ.7*56፤ፊል.1*23፤ገላ.2*20፤ራዕ.3*20፤…

[59]የሐ.8*58፤17*5፤ራዕ.5*5፤22*16፤ሚክ.5*2፤ዕብ.13*8፤ማቴ.28*20፤ዳን.7*14…

[60] ኢሳ.6*3፤ማቴ.19*17፤ሉቃ.1*49፤ራዕ.15*3-4

[61] ሉቃ.1*35፤ዮሐ.10*11፤የሐዋ.3*14፤4*30፤ዕብ.7*26፤ራዕ.3*7፤4*8፤…

[62] ዘጸ.34*6-7፤መዝ.102*1-2፤129*3-4፤ማቴ.6*12-14፤…

[63] ማቴ.9*2፣4-5፤ማር.2*5፣7-10፤ሉቃ.5*20፤7*48

[64] ሉቃ.23*43

[65] ዘፍ.18*25፤መዝ.9*8፤49፤6፤93*1-2፤95*13፤96*9፤ሮሜ.3*6፤…

[66] ማቴ.16*27፤25*31-46፤2ቆሮ.5*10፤2ጢሞ.4*1፤ ራዕ.2*2-9፣23፤22*12

[67] 1ነገ.8*39፤ምሳ.17*3፤21*2፤መዝ.7*9*21፤ኤር.11*20፤17*9-10፤አሞ.4*13፤ 1ተሰ.2*4 …

[68] ማቴ.16*8፤9*3፤12*24-25፤17*27፤ማር.8*16-17፤ሉቃ.5*21-22፤7*39-40፤ ዮሐ.1*47-50፤4*፤11*11፤…

[69] ራዕ.*23

Advertisements
 
 

2 responses to “ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

 1. mastewwal2001@yahoo.com

  April 26, 2012 at 3:17 pm

  good interesting best……

   

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

 
%d bloggers like this: