RSS

Monthly Archives: March 2012

‹የዓለም የሥልጣኔ ምንጭ ኢትዮጵያ ናት›፤ ማንስ ነው አይደለችም የሚል?

የዓለም የሥልጣኔ ምንጭ ኢትዮጵያ ናት! please read this updated aricle in PDF

እንዳውም ‹ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ› ብላችሁ ካልተሳለቃችሁብኝ የዓለም ሥልጣኔ ምንጩ ኢትዮጵያ ናት የሚል አስተሳሰብ ከሰረፀብኝ ውሎ አድሯል፡፡ ምን ላድርግ የግብፅን የጥንት ሥልጣኔ ያጠኑ የግብፅ ጥናት ሊቆች(Egyptologists)  ‹የጥንቱ የዓለም ሥልጣኔ ከግብፅ ተነሥቶ እንደተስፋፋ ሞገቱኝ!› ተስማማሁ፡፡ ስስማማላቸው ነው መሰል ‹ግብፅ የተመሠረተችው እኮ በጥንት ኢትዮጵያውያን ነው› ብለው ማስረጃ አቀረቡ፡፡ አረ ተው ብላቸው ‹የጥንቱን ከአሁኑ ጋር እያነጻጸሩ እመን አሉኝ› እስቲ ቆይ ላስብበት ብዬ የሀገር ውስጡን ትውፊቱን፣ ተረቱንና ባህሉንና መልካችንን ‹የጥንት ግብፅ ሥልጣኔ ነው› ከተባለው ጋር ሳነጻጽር ቁርጥ የራሳችን ሆኖ አገኘሁት፡፡ ከዚያም ባሰብከው መሠረት ‹ውሳኔህ ከምን?› አሉኝ ‹አመንኩ ተጠመቅኩ› አልኳቸው፡፡ እናንተ ጥርጣሬ ይዟችሁ ‹የውሳኔ እጅህ ከምን? አስረዳ!› ብላችሁ ከላዬ ላይ አልወርድ ካለችሁ ‹ግራ ቀኙን ተመልክቼ የውሳኔዬን ማብራሪያ ላቀርብ ነው›! Read the rest of this entry »

Advertisements
 

ተሐድሶ እንዴት ይታያል?

አያቶች፡-…

አባቶች… ጥበብ ዕድሜያቸውን ገብረው፣

የጎጆ ንድፍ ሲያበጁ፣

አረጁ… ዘመናቸውን ፈጁ…

ልጆች!

ጎጆውን ለመውረስ ሳይከጅሉ፣

እንዲህ አሉ….

‹ያባቶቻችን ጎጆ

ይሁን ባዶ ይሁን ኦና

በኛ መጠን አልተቀለሰምና፡፡..›

(በዕውቀቱ ሥዩም)

ከቅርብ ጊዜያት ጀምሮ የተሐድሶ ጉዳይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አነታራኪ ሆኗል፡፡ ንትርኩም ባፍ በመጣፍ እንደሚባለው ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡ ይህም በተለለያዩ ድራተ ገጽ፣ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ መጽሐፎችና ቴሌቪዥን ጣቢያዎችም እየተገለጸ ቆይቷል፡፡ ጭቅጭቁ ደግሞ ተሐድሶ የሚባለው እንቅስቃሴ አለ ወይስ የለም ከማለት ይጀምራል፡፡ እኔም ከዚህ  ‹እውን የተባለው የተሐድሶ እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እየተካሔደ ነው? ወይም አለ?› ብዬ በመጠየቅ ልነሳ ፈለኩ፡፡

የዚህ ጥያቄ መልስ ‹የለም› የሚል ቢሆን ኖሮ የተባለው ሁሉ ስህተት ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ መነታረክ አያስፈልግም ነበር፡፡ በ‹ሌለ› ጉዳይ ላይ መነታረኩ ምን ጥቅም ይኖረዋል? በሌለ ነገር ያለው ‹የለም› የሚለው ስም ብቻ ነው፡፡ ባይሆን አንድ ነገር በአግባቡ መታየት ይኖርበታል ‹እና በእንቅስቃሴው ዙሪያ የተዘጋጁ መጽሐፎች፣ መጽሔቶች፣… ከየት አምጥተውት ነው መነጋገሪያ ያደረጉት?› Read the rest of this entry »

 
 

መሠረታዊ ሎጂክ እና ሕጸጽ

መሠረታዊ ሎጂክ እና ሕጸጽ

መግቢያ
የሰው ልጅ አእምሮ ያለው ፍጡር ነው፡፡ አእምሮውም በምክንያት ይመራል፡፡ የምንኖርበት ዓለምም ምክንያት ዓልባ ሆኖ አልተፈጠረም፡፡ ይህም ምክንያታዊ ዓለም በምክንያታዊ አእምሮ ይታወቃል፡፡ የሰው ልጅ አእምሮም በተፈጥሮው ትክክለኛ ምክንያት ያገኘለትን ነገር ሲያምን ወይም ሲደግፍ ያላገኘለትን ግን ይቃወማል፡፡ ሆኖም አእምሮው ትክክለኛውን ምክንያት ትክክል ካልኾነው ለመለየት የሚቸገርበት ሁኔታ ብዙ ነው፡፡ ‹ለምን?› ቢባል አእምሮው ውስንነት አለበት፤ በስሜታዊነት የመሸፈን ችግር ያጋጥመዋል፤ በተፈጥሮው ያገኘውንና በልምድ ያከማቸውን ዕውቀት የማገናዘብ ችግርም ሊኖርበት ይችላል፡፡ ይህ ከኾነም ሰው ሁሉ ትክክለኛውን ምክንያት በአግባቡ ዐውቆ መጠቀም እንዲችል አእምሮውን በሎጂካዊ (አመክንዮአዊ) ዕውቀት ሊደግፈው ይገባል፡፡ …
አእምሮውን በአመክንዮአዊ ዕውቀት እንዲያበለጽግም ተጠየቃዊነትንና አመክንዮአዊ አመለካከትን የሚያሳዩና የሚያስረዱ በዚህ ዙሪያ የተጻፉ መጻሕፍት ያስፈልጉታል፡፡ ምንም እንኳን በዚህ ዙሪያ በሀገራችን ደረጃ በውጭ ቋንቋ የተጻፉ መጻሕፍት ቢኖሩም በሀገራዊ ቋንቋ የተዘጋጁት ግን ቁጥር ውስጥ የሚገቡ አይደሉም፡፡ ስለኾነም በሀገራዊ ቋንቋ ምክንያታዊ አመለካካትንና ተጠየቃዊ ዕይታን የሚያበለፅጉ መጻሕፍት በብዛት ቢጻፉ (ቢተረጎሙ) ጠቀሜታቸው የጎላ ይሆናል፡፡ የዕውቀት ፍሰት በእነሱ ውስጥ እንዲያልፍ ያደርጋሉና፡፡

ማንኛውም ጸሐፊ (ተርጓሚ) አንድ መጽሐፍ ለሕትመት ሲያዘጋጅ (ሲተረጉም) ለራሱም ኾነ ለኅብረተሰቡ የሚሰጠውን ጥቅም መዝኖ መሆን እንዳለበት እኔም ይህ መጽሐፍ የሚከተሉትን ጠቀሜታዎች ያስገኛል በማለት ተርጉሜ ላቀናብረው ችያለሁ፡፡
1. በአጠቃላይ ጉዳይ አመለካከቱ የሰፋ፣ ከስሜታዊነት የፀዳና ከግላዊ ዕይታ ወሳኝነት የተጠበቀ ዜጋን ለመቅረፅ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብዬ በመገመት፡- በዚህም ‹ሀይ!› ሲሉት ‹ወይኔ!› ወይም ‹ሆ!› ሲሉት ‹ሆ! ሆ!› የሚል ዜጋን ሳይሆን የትኛውንም ነገር በገለልተኝነትና በምክንያታዊነት (በተጠየቅ ዕይታ) እየጠየቀና እያረጋገጠ የሚቃወምና የሚደግፍ ኅብረተሰብን ለመቅረፅና ለመገንባት አስተዋጽኦው ከፍተኛ ይሆናል በማለት፡-
2. ለማንኛውም ዜጋ የክርክርና የውይይት ክህሎትንና ስልትን ለማዳበር ይረዳል፡- ነገሮችንም በጥልቀትና በአስተውሎት ለመመርመር ያግዛል የሚል እምነትን በመያዝ፡- በተለይም ለተማሪዎች በትምህርት ቤታቸውና በተለያዩ መድረኮች በሚያደርጓቸው ውይይቶችና ክርክሮች በልጅነታቸው የተጠየቃዊ አቀራረብ ስልትን (የአስተሳሰብ፣ የአነጋገርና የመከራከር ፍሰትን) ለማዳበር ይረዳቸዋል በሚል እምነት፡-
3. የሥነ-አመክንዮ ትምህርትን ምንነትና ይዘት ለማወቅ (ለመረዳት) ዕድሉ ላልገጠማቸው ሰዎችም ይህንን የዕውቀት ዘርፍ በቀላሉ ማግኘትና መረዳት እንዲችሉ ያደርጋል፡- በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ትምህርቱን እየተማሩት በቋንቋ ችግር የተነሳ መሠረታዊ ይዘቱን ቶሎ መረዳት ለሚቸግራቸው በሚረዱት ሀገራዊ ቋንቋና ምሳሌዎች በቀላሉና በአጭር ጊዜያት ውስጥ እንዲገነዘቡት ያግዛቸዋል በሚል ግምት፡-
4. ይህንን የዕውቀት መስክ ተምረውት ላለፉትም መጽሐፉን ቢያነቡት በቀላሉ በማስታወስና ዕውቀታቸውን በማዳበር እንዲጠቀሙበት ያስችላቸዋል ብዬ በመገመት (ፈተና ካለፈ በኋላ ዕውቀቱም ተኖ የሚጠፋ መሆን ስሌለበት) ነው መጽሐፉን ተርጉሜ ያቀረብኩት፡፡

 

ተጨዋቹ ዳኛ

ተጨዋችም ዳኛም ኾኖ የሰው ልጅ፣

ኳሷን ምድራችንን ቢይዝ በራሱ እጅ፣

ጨዋታው አልጣመም

ማንቀርቀብ!

ማንቀርቀብ!

ማንቀርቀብ ኾነ እንጂ!

 
Quote

‹የጨው ተራራ ሲናድ ፣ ሞኝ ይስቃል ብልህ ግን ያለቅሳል›

ፀጋየ ገ/መድኅን

‹ኑቢያም ፣ ጥንታዊ ጥቁር ግብፅም፣ የዛሬይቱ ጅቡቲም፣ ጥንታዊቱ ሳቢያም፣ ልክ እንደ ኢትዮጵያ የዘር ግንድ ምንጫችን፣ የነሱም መነሻቸው የኩሽ ነገድ ነው፡፡ በኋላ ግን ሁላችንም ከሞላ ጎደል ከሴም ነገድ ጋር ተቀይጠናል፡፡ ቋንቋዎቻችንም፣ ባህሎቻችንም፣ ሥልጣኔዎቻችንም፣ ተወራራሾች ሆነዋል፡፡ አንዲት ምሳሌ ልጥቀስ ክርስቶስ በሰበከበት በአራማይክ ወይም አረማዊኛ ቋንቋ ውስጥ ብዙ የጥንታዊት ኢትዮጵያ ቋንቋዎች ግሦች ይገኙበታል፡፡ ይኸ ሊሆን የቻለው በታሪክ ሂደት ነው እንጂ፤ በሥነ ብዕር ረጅም መተሳሰር ነው እንጂ እንዳው በአቦ ሰጡኝ አጋጣሚ አይደለም፡፡

የዓባይና የአትባራ ወንዞች ለየብቻቸው ከጣና ሐይቅ ወጥተው፣ በጥንታዊት ኑቢያ አትባራ (አድባራ) ከተማ እንደገና በሚገናኙበት ወረዳ ውስጥ ከነባለቅኔው ተዋናይ ኤኬራ ኔፍራት (ውሂብ ነፍስ) ጀምሮ እስከ ነቢዩ ሄኖክ (የአምላክ ተምሳል) ድረስ፣ በኋላም ከእነ ቅዱስ ያሬድ (የፀሐይ ንጉሥ እጅ)፣ እስከ ሊቁ ቅኔ በጉንጬ ድረስ፣ ከዚያም ከደራሲው ንጉስ ከቅዱስ ላሊ በላ (የፀሐይ ፀሐይ ዙፋን) እስከነ ሊቁ ገብረ ክርስቶስና ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ድረስ፣ ዛሬም ከነቀኝ ጌታ የፍታሔ ንጉሤ እስከነ ክቡር ባለቅኔ ከበደ ሚካኤል ድረስ፣ በተለይ ውድ ሕይወታቸውን ለአገር አንድነት መስዋዕት መክፈል ላይ እስካሉት ነፃ ጋዜጠኞች ድረስ፣ የብዕር ሀረግ የሚመዘዘው ከጥንት ኢትዮጵያዊነት የዘር ግንድ ነው፡፡ ከበደ ሚካኤል ‹እኛ የምንጽፈው በቀለም ሳይሆን በደማችን ነው › ያሉት ይህንኑ የብዕር ደም ሥር የዘር ሀረግ ነው፡፡

አዎን፣ ያልዘሩት አይበቅልም፡፡ የብዕር አባቶቻችን  የጨው ተራሮቻችን ናቸው፡፡ ‹የጨው ተራራ ሲናድ ፣ ሞኝ ይስቃል ብልህ ግን ያለቅሳል› መባሉ፣ አንድ ነገር ተገነጣጥሎ ሲሞት የተሰባበረ አጥንቱን መልሰው የሚገጣጥሙት፣ የጨው ተራሮቻችን፣ የብዕር አባቶቻችንና ወራሾቻቸውና ወጣት የብዕር  ልጆች ስለሆኑ ነው፡፡ ያልዘሩት አይበቅልም ማለታችን ለዚሁ ነው፡፡›

  ጦቢያ ጋዜጣ ጽቅ11፣ ቁ.9 1996

‹የጨው ተራራ …

 

እግዚአብሔር ለምን ሰው ኾኖ መገለጥ አስፈለገው?

ለአዳም ካሣ በመክፈልና የእግዚአብሔርን ትክክለኛ ፍትሕ በመጠበቅ ሞትን ለመሻር የተደረገ መገለጥ

* * *

የተወለደ ከአዳም፣

መሬት ያልገዘ የለም፡፡

ግብሩን መገበር አቅቷቸው፣

ገና ብዙ ዕዳ አለባቸው፡፡[1]

* * *

ለክርስቶስ በስብዕና መገለፅ ዋና ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው በአዳም መሳሳት የተነሳ በሰው ልጆች ላይ ያረፈውን የሞት ፍርድ በመሻር ለማስቀረት ሲኾን በሞት መሻርም የእግዚአበውሔር ትክክልኛ ፍርድ ሳይዛባ እንዲፈፀም ለማድረግ ነው፡፡ ምክንያቱም አዳምና ሔዋን በገነት በነበሩ ጊዜ እግዚአብሔር እንዳይበሉ ያስጠነቀቃቸውን ዕፀ በለስ በመብላት ትዕዛዙን በመሻራቸው ሞት የሚባል ዕዳ በሰው ልጆች ኹሉ እንደመጣባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ የኦሪት ዘፍጥረት ታሪክ ተገልፆ ይገኛል፡፡ ምናልባት እዚህ ላይ ‹የተሳሳቱት አዳምና ሔዋን ለምን ልጆቻቸው የሞት ቅጣት ተቋዳሽ ይሆናሉ?› የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ Read the rest of this entry »

 
 

ሀልዎተ እግዚአብሔር (Existence of God)

ሀልዎተ እግዚአብሔር (Existence of God)

መግቢያ

የ20ኛው መ/ክ/ዘ ከየትኛውም የታሪክ ጊዜ በበለጠ ሳይንሳዊ ዕውቀት የመጠቀበት ክፍለ ዘመን እነደነበር ይታወቃል፡፡ ዘመኑ ሳይንሳዊ አስተሳሰብ የመጠቀበት ብቻ አልነበረም፤ በተቀራኒውም ዓለም በጦርነት የታመሰችበትና በኢ-ሞራል አስተሳሰብ የዘቀጠችበትም እንጂ፡፡ በተለይ ኢ-ሞራላዊነት ያደረሰው ጥፋት ወደርና ልክ የለውም ሊባል ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የዘመኑ ፍልስፍናዊ አስተሳሰብ በቁሳዊ አመለካከት ላይ መመሥረቱና መንፈሳዊ የሚባሉትን የሰው ልጆች ሀብታት መሰረዙ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፡፡ ይህ መንፈሳዊ አመለካከትን በሐሣባዊነት ቅርጫ አጉሮ የተመሠረተ ፍልስፍናም የሣይንስን ዕድገት በቁሳዊነት መርህ ብቻ እንዲመራ አድርጎታል፡፡ በዚህ የተነሣ ሃይማኖትም ተጠራርጎ በሐሣባዊነት መርህ በመፈረጅ የሳይንስ ፀር ተደርጎ ሊወሰድ ችሏል፡፡ ይህ መርህ በተለይ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ዓለም በሶሻሊዝም አስተምህሮ ተጠምቃ አዲስ የ‹እግዚአብሔር የለም› ትምህርትን ‹ክርስትና› እንድትነሣ አድርጓታል፤ ‹አዲስ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል› እንደሚባለውም በአዲሱ አስተሳሰብ ተጠምቀው ሳይንቲስት የኾኑት የቁሳካላዊያን ልጆችም በ‹እግዚአብሔር የለም› አስተምህሯቸው ውጥንቅጧን አውጥተዋታል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያም የገፈቱ ቀማሽ በመኾን አዲሱን ሃይማኖት ተቀብላ እንዲትጠመቅ የተማሩት ‹ምሁር ልጆቿ› በግልፅም በሥውርም ጥረውላታል፡፡ በዚህ ጥረታቸውም የሀገሪቱን ትምህርት በቁሳዊ ሳይንስ የአስተምህሮ መርህ በመቅረጽ፣ የሃይማኖትን የሥልጣኔ ፀርነት በሥርዓተ-ትምህርቱ በማራገብና የመንግሥት ተቋማትን ተቆጣጥረው በማስተማር ወትውተዋል፡፡ በዚህም ያልገባቸውን አዲስ የቁስአካላዊ አስተምህሮ በትውልዱ አዕምሮ አጭቀው አጭቀው ግራ ገብ ስላደረጉት ጭራሽ ለባሰው ለ‹ምንፍቅና›፣ ለ‹እኔ አምላክነት› ትምህርተ ዕምነት ሰለባ አድርገውታል፡፡ በዚህ የተነሣ እነ ኦሾ እንኳን እንደ ‹ፈጣን ሎተሪ› በነፃነት እየፋቁት ይገኛሉ፡፡ ከዘመኑ ትውልድም ብዙ ወጣት ‹ኒቼ እንዲህ ብሏል› ሲሉት የእሱ አቀንቃኝ፣ ኦሾን ሲሰማም የእሱ ደቀ መዝሙር፣ ሪቻርድ ዳዊኪንም ‹እግዚአብሔር ቅዠት ነው› ሲለው ቅዠታም፣ የእስጢፋኖስ ሃውኪንግን አዲስ የሳይንስ ግኝት ሲሰማ ወይም ሲያይም ኢ-አማኝ ሳይንቲስ ይኾናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይኾን የቁሳካላዊ ዝግመተ ለውጥ አስተምህሮ የፈጠረበት የሥነ ምግባር አልባነት ተፅእኖም ኢ-ሞራላዊ ‹ሙሱን› እንዲኾን አድርጎታል፡፡

ይህ በአንድ በኩል ሲኾን በሌላ በኩል የዘመኑን መንፈሳዊ ጦርነት ተቋቁመው የሚገኙት የ‹አባቶች ልጆችም› ዘመናዊ መሣሪያ በማጣት ወደ መማረክ ወይም ‹አትከራከሩ ሳይንስና ሃይማኖት፤ ፍልስፍና እና ሃይማኖት ተቃራኒ ናቸው› በሚል መርህ ዝምታን መርጠዋል፤ አንዳንዶቹም በጦርነቱ እጅ ሰጥተዋል፡፡ ስለዚህ የዘመኑን መንፈሳዊ ወረራ ለመከላከልና ከመንፈሳዊ ቅኝ ግዛት ጭቆና ነፃ ለመውጣት ዘመናዊ መሣሪያ ታጥቆ መዋጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህ መጽሐፍም ለዚህ የተወሰነ አስተዋፅኦ ይኖረዋል በሚል የተዘጋጀ ነው፡፡

መጽሐፉ በአጠቃላይ በሦስት ዕይታዎች የተቃኘ ነው፡- በፍልስፍና፣ በሳይንስና በሃይማኖት አስተምህሮዎች፡፡ የአቀራረብ ስልቱ በመጀመሪያ የፍልስፍና ዕይታን በተጠየቅ ሙግት አስቀምጦ ያብራራል፤ በአብዛኛው የፍልስፍና ሙግቶች የቀረቡት በዚህ መልክ ነው፡፡ ይሁንና በተወሰነ ደረጃ ካልኾነ በስተቀር ጸሐፊው የፍልስፍና አስተምህሮዎችን ማጨቅ አልፈለገም፡፡ ስለኾነም የፍልስፍና ዕይታ አቀራረብን በአብዛኛው አመክንዮአዊ (logical) ለማድረግ ሞክሯል፡፡ ሳይንሳዊ ዕይታዎችን በሚመለከት የተከተለው አቀራረብ መላምቱን በፍልስፍናዊ መሠረቱና አተያዩ በማቅረብና የተወሰነ ትችታዊ አስተያየት በመስጠት ላይ የተወሰነ ነው፡፡ ለዚህም ዋናው ምክንያት ጸሐፊው የሳይንስ ዕውቀት መሠረቱ ፍልስፍና፤ ማጠንጠኛው ደግሞ የእውናዊው ዓለም ሥርዓታዊ ቅንብርና አስተሳሰብ ነው የሚል እምነት ስላለው ነው፡፡ በተቻለ መጠንም ለተነሳበት ርዕስ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ሳይንሳዊ መላምቶች ለማካተት ሞክሯል፡፡ ሃይማኖታዊ አስተምህሮችንም እንደ ፍልስፍናው ተጠየቃዊ ለማድረግ ጥሯል፡፡ ይሁንና የዕይታ አንግልን መስመር ለማስያዝ ሲባል የአቀራረብ ሙግቱ በክርስትና ሃይማኖት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ቢኾንም በዚህ መጽሐፍ በአንድ ምዕራፍነት ሊካተት የነበረ ‹ነገረ ድኅነት ለእግዚአብሔር ሀልዎት› የሚል የክርስትና አስተምሮ ሙሉ ለሙሉ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ለዚህም ኹለት ምክንያቶችን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አንደኛ በመጽሐፉ መነሻነት የትኛውም ሰው ወይም የየትኛውም እምነት ተከታይ በነፃነትና ተፈጥሮን መሠረት አድርጎ ብቻ በመመርመር የእግዚአብሔርን ሀልዎት እንዲረዳ ለማድረግ ሲኾን፤ ኹለተኛም በአንድ ምዕራፍ የተቀመጠው የነገረ-ድኅነት አስተምሮ ሰፋ ተደርጎ በአንድ መጽሐፍነት ቢዘጋጅ የተሻለ ግንዛቤን ይፈጥራል በሚል እሳቤ ነው፡፡

ከአቀራረቡ ጋር በተያያዘ ጸሐፊው በተወሰነ ደረጃ ከሚፈለገው ሐሣብ ጋር አብሮ ይሔዳል ብሎ ያሰበውን ግጥም ወይም ቅኔ ወይም አባባል አብሮ ለማቅረብ ሞክሯል፡፡ ይህም መጽሐፉ ከያዘው ሐሣብ ጥንካሬ አንጻር ውበት ለመስጠትና ሐሣቡንም በዚያው ለማጎላመስ፣ እንዲሁም የገጣሚያንና የባለ ቅኔዎንች ዕይታም ለማሳየት ተብሎ የተደረገ ነው፡፡ ይሁንና አንዳንዶቹ ግጥሞች (ቅኔያት)  አጠቃላይ የመጽሐፉን ዓለማ ካልኾነ በስተቀር ከንዑስ አሳቡ ጋር  አብረው የማይሔዱበት ኹኔታ ይኖራል፡፡ እንዲሁም ግጥሞቹ ከተለያዩ ገጣሚያን ወይም ባለቅኔዎች የተሰበሰቡ በመኾናቸው አንዳንዶቹ የተገጠሙበት ዕይታ በዚህ መጽሐፍ በቀረቡበት መልኩ ላይኾን ይችላል፡፡ ለዚህም ለገጣሚዎቹና ለቅኔ ሊቃውንቱ ይቅርታ መጠየቅን ይወዳል፡- ጸሐፊው፡፡ በተጨማሪም ጸሐፊው በእንግሊዘኛ የተጻፉ ግጥሞችን እንደነበሩ ትቷቸዋል፤ አልተረጎመም፡፡ ምክንያቱም ወደ አማርኛ መመለሱ መልዕክታቸውን ስላደበዘዘው እንደነበሩ ቢጠቀሱ ይሻላል ብሎ ስላሰበ ነው፡፡

በአጠቃላይ መጽሐፉ 8 ምዕራፎች አሉት፡፡ በመጀመሪያው ምዕራፍ  ወጣቶች በየሻይ ቤቱና በሌሎችም ሥፍራዎች የሚያደርጓቸውን ኢ-መደበኛ ክርክሮች   የሚያንፀባርቅ ክፍል ቀርቧል፡፡ ይህ ርዕስም በመጀመሪያ የቀረበበት ምክንያት ጸሐፊው ቀድሞ መጽሐፉን ያዘጋጀበት ስልት በውይይት መልክ ስለነበር  ስልቱን ከቀየረ በኋላም ይኸኛው ርዕስ ከዋናው የአቀራረብ ፍሰት በፊት ቢገባ ችግር አይኖርውም በሚል እምነት ሲኾን በተጨማሪም በቀላል ለመጀመር ይረዳል፤ እንዲሁም የወቅቱን የወጣቶች የክርክር ኹኔታም ያንፀባርቃል በማለት ነው፡፡

በኹለተኛው ምዕራፍ በእግዚአብሔር ህልውነት ላይ ያሉ ሦስት አማራጭ የክርክር አቋሞች ቀርበውበታል፡፡ ከአቋሞቹም መካከል የኹለቱን ማስረጃዎች በተጠየቅ  ያቀርባል፡፡ አንደኛውን አቋም ግን በመከራከሪያነት ደግፎ ወደሌሎች ምዕራፎች ያሸግረዋል፡፡ በሚቀጥለው በምዕራፍ ሦስት አጠቃላይ የእግዚአብሔርን ሀልዎት ከጠባያቱ ምንነት አንጻር ያሳይና በዚያ ላይ የኹለት ሰዎች ሙግትን በተቃርኖዊ ዕይታ ያቀርባል፡፡ ይህም በእግዚአብሔር ጠባያት የተለያየ አመለካከት ያላቸውን ሰዎች አቋም ያንፀባርቃል በሚል የቀረበ ነው፡፡

ከምዕራፍ ሦስት በኋላ ያሉት አራት ምዕራፎች ጸሐፊው የእግዚአብሔርን ህልውነት ለማረጋገጥ ያስችሉኛል ያላቸውን ማስረጃዎች ያቀረበባቸው ምዕራፎች ናቸው፡፡ ምዕራፍ አራት ማጠንጠኛው በኹለት ሐሣቦች ላይ ነው፡- የዓለመ-ፍጥረቱ (universe) መገኘትና ፍፅምናን መፈለጉ፡- የእግዚአብሔርን መኖር ያጠይቃል በሚል፡፡ የምዕራፍ አምስት ማጠንጠኛ ሐሳብ ደግሞ በአጠቃላይ በፍጥረቱ ሥነ ሥርዓታዊ አኗኗር ላይ ነው፡፡ በዚህም ከጠቅላላ የዓለመ-ፍጥረቱ አኗኗር ጀምሮ እስከ የሕይወት ትንሽ ሕዋስ ድረስ ፍጥረት እንዴት ሥርዓትን በመጠበቅ እንደሚገኝ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ ያለው ምዕራፍ ስድስት ሕይወት ካላቸው ነገሮች ሰውን ነጥሎ ምን ያህል እንቆቅልሽ እንደኾነ  ማንነቱን ይመረምራል፡፡ ቀጣዩ ምዕራፍ ሰባት ደግሞ በሞራል ላይ የሚያጠነጥን ምዕራፍ ነው፡፡ በዚህም ሞራል የበላይ ኃላፊን እንደሚፈልግ በማሳየት የእግዚአብሔርን ህልውነት ለማረጋገጥ ያለውን ማስረጃነት ይቃኛል፡፡

የመጨረሻው ምዕራፍ ስምንት የማጠቃላያ ነጥቦችን  የያዘ ነው፡፡ በዚህ እግዚአብሔር ‹አለ›ም ኾነ ‹የለም› የሚሉ ተከራካሪዎች የሚያቀርቧቸውን ማስረጃዎች ጥቅል ፐርሰንት ተሠጥቷቸው የሚኖራቸው የማስረጃነት ክብደት ተመዝኗል፡፡ የተሰጠውን ነጥብም ከነባራዊ የማስረጃ እውነታ ጋር በማገናዘብ ለመተንተን ተሞክሯል፡፡ በተጨማሪም በእግዚአብሔር ህልውነት ዙሪያ ያሉ አማራጮችን በተጠየቅ በመመዘን ትክክለኛው መደምደሚያ ላይ ለመድረስ ተጥሯል፡፡ በዚህ መልክም ምዕራፉ ማጠቃላያ በመስጠት ያሳርጋል፡፡

 
 
%d bloggers like this: